የአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክን መለስ ብለን ስንፈትሽ የምናገኘው በአቧራማ ሜዳዎች ላይ በባዶ እግራቸው እየሮጡ፣ ከፕላስቲክ በተሰራች ኳስ ተጫውተው ያሰለፉትን እና የተፈጥሮ ተሰጥኦቸውን ብቻ ተማምነው ዓለምን ያስደመሙትን ጀግኖችን ነው። ከካሜሮኑ ሮጀር ሚላ እስከ ላይቤሪያው ጆርጅ ዌሃ፣ ከጋናው አቤዲ ፔሌ እስከ ናይጄሪያው ጄይ ጄይ ኦኮቻ፤ እነዚህ ሁሉ ኮከቦች የተፈጠሩት፣ ያደጉት እና የተቀረጹት በአፍሪካ ምድር ነው። የእግር ኳስ ቋንቋቸው፣ ስልታቸው እና ምታቸውም አፍሪካዊ ነበር። በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫም ሙሀመድ ሳላህ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ቪክተር ኦስሜህን፣ አሽራፍ ሀኪሚ እና የመሳሰሉት ኮከቦች ታሪክ ለመስራት በድግሱ ተሰይመዋል። በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ከ24 ብሄራዊ ቡድኖች 664 ተጫዋቾች በድግሱ እየተካፈሉ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ 191 ተጫዋቾች በአፍሪካ ምድር ያልተወለዱ እና ያላደጉ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቦታል።
የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ጥሬ ዕቃውን ወደ አውሮፓ ከመላክ ይልቅ በአውሮፓ የእግር ኳስ ፋብሪካዎች (አካዳሚዎች) ተመርቶ ያለቀለትን የተዘጋጀ ምርት ወደ አፍሪካ ማስመጣትን ተያይዘውታል። ይህ ሂደት የዲያስፖራ ስትራቴጂ ወይም በውጭ የተወለዱ ድርብ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች (Binationals) መጠቀም በመባል ይታወቃል። የሞሮኮ፣ የአልጄሪያ፣ የሴኔጋል፣ የናይጄሪያ እና የሌሎችም ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖች አብዛኞቹ ተጫዋቾች የተወለዱት በፓሪስ፣ በለንደን፣ በአምስተርዳም ወይም በማድሪድ ነው። ይህም ለአህጉሩ እግር ኳስ አዲስ የጥራት ደረጃ እና ታክቲካዊ ብስለትን ቢያመጣም ከስር መሰረቱ ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ነፍሱን እየሸጠ ነውን? የሚል ከባድ ክርክር ማስነሳቱን ዘ ኮንቨርሴሽን አፍሪካ አስነብቧል።
ለዚህ ክስተት እንደ አብነት የሚወሰደው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ያስመዘገበው ታሪካዊ ውጤት ነው። የአትላስ አንበሶቹ ለአፍሪካ እና ለአረቡ ዓለም የመጀመሪያው የሆነውን የግማሽ ፍጻሜ ታሪክ ሲጽፉ የቡድኑ ስብጥር ለዚህ ክርክር ትልቅ ማሳያ ነው። ከ26ቱ ተጫዋቾች ውስጥ 14ቱ (ከግማሽ በላይ የሚሆኑት) ከሞሮኮ ውጭ የተወለዱ ናቸው። አሽራፍ ሀኪሚ (ስፔን) ፣ ሀኪም ዚየች እና ኑሴር ማዝራውይ (ሆላንድ) ፣ ሶፊያን ቡፋል እና ሮሜይን ሳይስ (ፈረንሳይ) እና ያሲን ቦኖ (ካናዳ) የመሳሰሉት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የዲያስፖራ ስትራቴጂ ውጤቶች ናቸው።
ሞሮኮ ይህንን ያደረገችው በእግር ኳስ ፌዴሬሽኗ አማካኝነት ነው። Royal Moroccan Football Federation (FRMF) የተሰኘው ተቋም መልማዮችን (Scouts) በመቅጠር በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ ተሰጥኦ ያላቸውን እና የዘር ሀረጋቸው ከሞሮኮ የሚመዘዙትን ይሰበስባል። ታዲያ በአውሮፓ እጅግ ዘመናዊ አካዳሚዎች ውስጥ የሰለጠኑ፣ ጥሩ የስነ ምግብ (Nutrition)፣ የስነ ልቦና እና የታክቲክ ትምህርት የቀሰሙ ተጫዋቾችን ማግኘት ቡድኑን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን አድርጎታል።
ነገር ግን የሞሮኮ የስኬት ሚስጥር ዲያስፖራዎችን መሰብሰብ ብቻ አልነበረም። ሞሮኮን ልዩ የሚያደርጋት ከሀገር ውስጥ ልማት ጋር ማጣጣሟ ነው። በንጉሡ ስም የተገነባው መሀመድ ስድስተኛ የእግር ኳስ አካዳሚ (Mohammed VI Football Academy) በሀገር ውስጥ ያሉ ምርጥ ተጫዋቾችን አፍርቷል። በ2022ቱ የኳታር የዓለም ዋንጫ ድንቅ ሆነው የታዩት ኤዘዲን ኦናሂ፣ ዩሴፍ ኤኔሲሪ እና ናይፍ አጉርድ የአካዳሚ ፍሬዎች እንደሆኑ መዘንጋት የለብንም። እናም ሞሮኮ ዲያስፖራውን ከሀገር ውስጥ ተሰጥኦ ጋር በማዋሃድ (Hybrid Model) ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በትምህርትነት የሚወሰድ መንገድ ማሳየቷን ዴይሊ ማቭሪክ በዘገባው ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ የሞሮኮን አይነት ሚዛናዊ አካሄድ መከተል የቻሉ ሀገራት ጥቂት ናቸው። ለአብዛኞቹ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ዲያስፖራዎችን መመልመል እንደ አቋራጭ መንገድ (Shortcut) ነው የሚታየው። እግር ኳስን ከታች ለመገንባት፣ ታዳጊዎችን ለመመልመል፣ ማሰልጠኛዎችን ለመክፈት፣ አሰልጣኞችን ለማብቃት እና ውድድሮችን ለማዘጋጀት ቢያንስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ይፈጃል። ሂደቱም ትዕግስት፣ ገንዘብ እና ግዙፍ እቅድ ይጠይቃል። በአንጻሩ ግን አንድ የፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወደ ለንደን በረራ አድርጎ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወትን የዘር ሀረጉ ከናይጀሪያ የሚመዘዝን ተጫዋች አግባብቶ ዜግነቱን አስቀይሮ ለብሄራዊ ቡድን ማሰለፍ የሚፈጀው ጊዜ ከሦስት እስከ ስድስት ወር ብቻ ነው።
ይህ የተዘጋጀን ችሎታ የመጠቀም (Importing Ready made Talent) ባህል የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖችን እና ባለሙያዎችን ወደ ስንፍና እየወሰዳቸው እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል። ለምን እደክማለሁ? የሚል አደገኛ አስተሳሰብ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እየተፈጠረ መሆኑን መረጃው ይጠቅሳል። ይህ አካሄድ መዝራት ሳያስፈልግ ማጨድ (Harvesting without sowing) ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ውጤቱም የሀገር ውስጥ ሊጎች እንዲዳከሙ ያደርጋል። በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ወጣቶች ወደ ብሄራዊ ቡድን የመግባት እድላቸው እየጠበበ ሲሄድ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይፈጥርባቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ የማንነት ቀውስ (Identity Crisis) በቡድኖች ውስጥ እየተፈጠረ ነው። በውጭ የተወለዱ ተጫዋቾች እና በሀገር ውስጥ ያደጉ ተጫዋቾች በአንድ የመልበሻ ክፍል (Dressing Room) ውስጥ ሲገናኙ የባህል እና የቋንቋ ልዩነት ይፈጠራል። ዲያስፖራዎቹ ብዙውን ጊዜ የአውሮፓ ቋንቋዎችን ብቻ ነው የሚናገሩት፤ የአኗኗር ዘይቤያቸው እና አስተሳሰባቸውም አውሮፓዊ ነው። በሀገር ውስጥ ያሉት ደግሞ የአካባቢውን ቋንቋ እና ባህል ይዘው ነው ያደጉት። ይህ ክፍተት በቡድን መንፈስ (Team Spirit) ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥር ይስተዋላል ሲል የካፍ ኦንላይን መረጃ አስነብቧል።
ይህ ማለት ዲያስፖራዎቹ ለአፍሪካ እግር ኳስ ያመጡት ጥቅም በቀላሉ የሚገመት አይደለም ማለት እንዳልሆነ የካፍ ኦንላይን መረጃ ያመለክታል። የአፍሪካ እግር ኳስ በተፈጥሮ ተሰጥኦ እና በግል ብቃት (Flair and Individual Skill) ላይ የተመሰረተ ነው። የታክቲክ ዲሲፕሊን፣ የቦታ አያያዝ እና የመከላከል ጥበብ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት በስፋት ይነገራል።
በአውሮፓ አካዳሚዎች ያደጉ ተጫዋቾች ግን እነዚህ ክፍተቶች በአብዛኛው አይስተዋልባቸውም። እነዚህ ተጫዋቾች ስለ አመጋገብ፣ ስለ እረፍት፣ ስለ ህክምና እና ስለ ትጥቅ ጥራት ያላቸው እውቀት ከፍተኛ ነው። ወደ ብሄራዊ ቡድን ሲመጡ ፌዴሬሽኖች አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ፣ ሆቴሎች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ እና የህክምና ቡድኖች ብቁ እንዲሆኑ ጫና ይፈጥራሉ። ይህ ታዲያ የአፍሪካ እግር ኳስ የፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እንዲያዳበር ያስችለዋል ተብሏል።
ግብጽ ደግሞ ከሞሮኮ ለየት ያለ መንገድ እንደምትከተል መረጃዎች ያመለክታሉ። ግብጽ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ስኬታማዋ ሀገር ስትሆን እስካሁን ድረስ የብሄራዊ ቡድኗ የተመሰረተው በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ላይ ነው። ከሞሀመድ ሳላህ (እሱም ቢሆን ከሀገር ውስጥ ሊግ ነው የወጣው) እና ከጥቂት ተጫዋቾች ውጭ አብዛኞቹ የፈርኦኖቹ ተጫዋቾች የሚጫወቱት ለ አል አህሊ ወይም ለ ዛማሌክ መሆኑን የካፍ ኦንላይን መረጃ ያስነብበናል። ይህ ለምን ሆነ? መልሱ የግብጽ ሊግ ጥንካሬ ነው። የግብጽ ክለቦች በገንዘብ አቅማቸው ጠንካራ ስለሆኑ ተጫዋቾች የግድ ወደ አውሮፓ መሰደድ አይጠበቅባቸውም። ተጫዋቾች በሀገራቸው ተከብረው እና ተከፍሏቸው መኖር ይችላሉ። ለዚህም ነው ግብጻውያን በዲያስፖራ ተጫዋቾች ላይ ያልተንጠለጠሉት። ይህ ሞዴል ኢትዮጵያን በመሰሉ ደሀ ሀገራት ለመተግበር ሰፊ ሀብት እንደሚያስፈልግ ካፍ ኦንላይን አስነብቧል።
አፍሪካውያን በዲያስፖራ ተጫዋቾች ላይ ያላቸው ጥገኝነት አንድ ትልቅ አደጋን ይዟል። በሌላ በኩል የፊፋ ሕግ ተጫዋቾች ዜግነት እንዲቀይሩ መፍቀዱ ለአፍሪካ ትልቅ እድል ፈጥሯል። ነገር ግን የአውሮፓ ሀገራት (ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ) በራሳቸው አካዳሚ ያወጡትን ገንዘብ እያሰቡ ወደፊት ሕጉ እንዲቀየር ወይም ጫና እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።
ማሪዮ ባሎቶሊ እና አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኖ ይህን የፊፋ ሕግ በጽኑ ከመደገፋቸውም በተጨማሪ የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ ምድር የሚመዘዙ ኮከቦች ለአፍሪካውያን ብሄራዊ ቡድኖች መጫወት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
ፌዴሬሽኖች በዲያስፖራ ስካውቲንግ ላይ የሚያወጡትን ጉልበት ያህል በሀገር ውስጥ አካዳሚዎች ላይ ማውጣት አለባቸው። የሀገር ውስጥ ሊጎች የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው፣ ስታዲየሞች እንዲዘምኑ እና ተጫዋቾች ወደ ውጭ ከመውጣታቸው በፊት በሀገራቸው በቂ ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚስፈልግ ዘ ኮንቨርሴሽን አፍሪካ ይጠቁማል። የአፍሪካ እግር ኳስ እውነተኛ ሃያልነት የሚረጋገጠው በፓሪስ ወይም በለንደን በሚገኙ አካዳሚዎች ሳይሆን በሌጎስ፣ በአክራ፣ በዳካር እና በአዲስ አበባ ሜዳዎች ላይ በሚፈስሰው ላብ እና በሚገነባው ጠንካራ መሰረት ላይ ነው። የአፍሪካ እግር ኳስ አመራሮች ከአቋራጭ መንገድ ወጥተው ወደ ትክክለኛው የግንባታ መንገድ የሚመለሱበት ጊዜ መሆኑን የካፍ ኦንላይን መረጃ አስነብቧል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታህሣስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


