
በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2017 የትምህርት ዘመን አንድ ሺህ 249 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም፤ ከነዚህ ውስጥ 61ዱ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው:: ይህም ትምህርት የወደፊት የሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰንበት፣ በዓለም መድረክ ብቁ እና ተወዳዳሪ ሀገር ወካይ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ ተማሪን በማብቃት ላይ የሚሠራው ሥራ የሁሉም ትኩረት ሊሆን እንደሚገባ የሚያሳይ ነው:: በቂ ዕውቀት ያላቸውን እና ሥራዎችን በተግባር ሊሠሩ የሚችሉ ተማሪዎች ከማፍራት በተጨማሪ የማለፍ ምጣኔን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለይቶ መሥራትም ይገባል:: ተማሪዎችም በተሻለ የጊዜ አጠቃቀምና የጥናት ስልት ውጤታማ እንዲሆኑ የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ በተማሪዎች መካከል እንዲኖር ማድረግ ይመከራል:: በብጹ ገብረሚካኤል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዋ ሰብለድንግል ዘመነ በትምህርቷ የተሻለ ውጤት የምታስመዘግብ ተማሪ መሆኗን ተናግራለች:: ለዚህም በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት መከታተሏ፣ ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜዋንም ፕሮግራም በማውጣት ለጥናት ማዋሏ ለውጤታማነቷ አስረጂ አድርጋ ጠቁማለች::
የቤተ መጻሕፍት አጠቃቀሟም የተሻለ እንደሆነ ተናግራለች:: ሰብለድንግል መምህራን በክፍል ውስጥ ሲያስተምሩ እና በጥናት ወቅት ግልጽ ያልሆኑ ይዘቶችን በዝርዝር ለመረዳት ቤተ መጻሕፍት ትልቅ መፍትሔ መሆኑን ገልጻለች:: ምክንያቱም አጋዥ ማጣቀሻ መጽሐፍቶችን በቀላሉ ለማግኘት የሚያግዝ በመሆኑ ነው ትላለች:: በትምህርታቸው የተሻሉ ከሆኑ ተማሪዎች ጋርም በቡድን የማጥናት ልምድ እንዳላት ተናግራለች:: ይህም አንዳንዶችን እርሷ ባላየችው መንገድ እንድትረዳ ከማድረጉም ባለፈ አይረሴ ዕውቀትን እንድታገኝ እንዳገዛት ነው የገለፀችው::
ሌሎች ተማሪዎችም ብቁ ሊሆኑባቸው የሚችሉ የአጠናን ስልቶችን ይበልጥ አጠናክረው በማስቀጠል ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክሯን ለግሳለች:: የትምህርት ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብም የሚያስረዳው ይህንኑ ነው::የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ቤት ዲን ደረጀ ታዬ (ዶ/ር) ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት መሠራት ያለበት ከመጨረሻው የክፍል ደረጃ ላይ ሳይሆን ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ መሆን እንዳለበት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል:: ተማሪዎች በአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታቸው መያዝ የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት ይዘዋል ወይ? የሚለውን በአግባቡ በመመርመር ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲሸጋገሩ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: ምዘናውም ተማሪዎች በተማሩበት ትምህርት ቤት እና ባስተማሯቸው መምህራን ሳይሆን በገለልተኛ አካል መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል:: ይህም ኩረጃ እና ማጭበርበር የምዘና ሥርዓቱ ፈተና እንዳይሆን ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት::ለመምህራን የሚሰጠውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በትምህርት ቤት ደረጃም ጭምር በመስጠት፣ መሠረታዊ የትምህርት ግብዓትን በማሟላት (መምህራን እና ተማሪዎችን ሊያግዙ የሚችሉ መጻሕፍትን)፣ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የመጠቀም ልምድን በማዳበር፣ ተማሪዎችን የመደገፍ ሥራን በማጠናከር ውጤታቸውን ማሻሻል እንደሚቻልም ጠቁመዋል:: ዶ/ር ደረጀ እንደሚሉት ሪፖርትን ሳይሆን ተማሪዎች እየበቁ መሄዳቸውን የሚያረጋግጥ ሥርዓት መከተል ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት የሚያስችል ዋና መፍትሔ ነው:: ለዚህም የትምህርት አመራሩና የመምህራን ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆን አለበት::
መምህራን ያለፉ ፈተናዎችን በመቃኘት ተማሪዎች በዋናነት ምን ላይ ትኩረት አድርገው መዘጋጀት እንዳለባቸው የማሳወቅ ሥራም መሥራት ይጠበቅባቸዋል:: የተማሪዎችን ሥነ ልቦና መፈተሸ እና ዝግጁነታቸውንም ማረጋገጥ ይገባል:: የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ መረጃ እንደሚያመለክተው በትምህርት ዘመኑ 333 ሺህ 669 ተማሪዎች በመማር ላይ ይገኛሉ:: ይህም ከዕቅዱ አንጻር የ97 በመቶ ድርሻ እንዳለው የመምሪያ ኃላፊው አቶ ሰጠ ታደሰ አስታውቀዋል:: በአሁኑ ወቅትም በትምህርት ላይ ያሉትን የማብቃት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: መምህራን ተከታታይነት ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ተማሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው እየመዘኑ እንዲዘጋጁ የተለያዩ የፈተና ጥያቄዎችን አዘጋጅቶ መስጠት፣ የአዳር ጥናትን ማጠናከር፣ ቤተ መጻሕፍት በሚፈልጉት ጊዜያት እንዲጠቀሙ ክፍት ማድረግ ተማሪዎችን ለማብቃት እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው::
እንደ ሰሜን ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘገባ በቀጣይም ተማሪዎች በእውቀት፣ በአመለካከት እና በክህሎት የዳበሩ እንዲሆኑ በትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ይሠራል::
የሰሜን ሸዋ ዞንም በትምህርት ዘመኑ ለማስተማር በእቅድ ከያዛቸው ተማሪዎች 62 በመቶን ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑን የትምህርት መምሪያ ኃላፊው አቶ ጸጋዬ እንግዳየሁ አስታውቀዋል:: ተማሪዎች ባሉበት የክፍል ደረጃ በቂ ዕውቀት እንዲይዙ የማብቃት እና ውጤታማ የማድረግ ሥራ አሁናዊ ዋና ትኩረት ሆኖ እየተሠራ ነው:: ተማሪዎች የተሻለ አመለካከትና ክህሎት እንዲኖራቸውም የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት:: አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላትም ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል:: የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታው ዓለሙ በበኩላቸው በመማር ላይ የሚገኙትን 284 ሺህ ተማሪዎች ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል:: እያንዳንዱ ተማሪ በሚማርበት የትምህርት ደረጃ ልክ የሚገባውን ዕውቀት እንዲይዝ ማስቻል እና ለፈተና ማብቃት ደግሞ ዋና ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት:: ተማሪ የማብቃት ሥራው ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እየተከናወነ ነው:: ክልላዊ እና ሀገራዊ ተፈታኞችን ማብቃትም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው::
የአዳር ጥናት አንደኛው መፍትሔ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል:: ይህ አካሄድ በተለይም ለገጠር ተማሪዎች ትልቅ ራስን የማብቂያ መንገድ መሆኑን አስታውቀዋል:: እነዚህ ተማሪዎች ከትምህርት መልስ ያለውን ጊዜያቸውን ቤተሰብ በማገዝ የሚያሳልፉ በመሆኑ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ አያገኙም:: በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ለአዳር ጥናት የሰጡትን ትኩረት በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ሊያበቁ እንደሚገባ ጠይቀዋል:: በተጨማሪም ርስበእርስ መረዳዳትን እና መተጋገዝን የሚያበረታታ፣ ማጣቀሻ መጻሕፍቶችን በቅርበት ለማግኘት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ እሳቤውን ተመራጭ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል:: የማጠናከሪያ ትምህርትን ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን መስጠት፣ ከመደበኛው የትምህርት ሥራ ውጪ ያለውን ጊዜ ጨምሮ ቅዳሜ እና እሁድ የትምህርት ጊዜ ማድረግ፣ ቤተ መጻሕፍትን ሙሉ ቀን ክፍት ማድረግ እና ሌሎች መፍትሔዎችም ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንት አደመ በበኩላቸው ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ብቻ ግብ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል:: ተማሪዎች በሚማሩበት የክፍል ደረጃ በቂ እውቀት ይዘው እንዲያጠናቅቁ እና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀጥሉ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል:: ለዚህም በተዋረድ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል::
መረጃ
የሌሊት ጥናት አስፈላጊነት
ከትምህርት መልስ በቂ የጥናት ጊዜ ለሌላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የተለያየ የትምህርት አቀባበል ያላቸውን ተማሪዎች በአንድ የሚያገናኝ በመሆኑ እርስ በርስ መረዳዳትን እና መተጋገዝን ያበረታታል፡፡
የአጠናን ስልቱ ተሞክሮ ልውውጥ እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ማጣቀሻ መጻሕፍቶችን በቅርበት ለማግኘት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ይረዳል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የታህሳስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

