አንዲት የዋልታ ድብ በዱር እንስሳት ዝርያ ባልተለመደ መልኩ ወላጅ አልባ ግልገልን በ “ጉዲፈቻ” ወይም በ”ማደጐ” ከራሷ ግልገል ጋር አስከትላ በማሳደግ ላይ መሆኗን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የካናዳ ተመራማሪዎች ቡድን በምዕራባዊ ሁድ ሰን ባህረ ሰላጤ ባለፈው 2024 የአውሮፓውያኑ ዓመት መጋቢት ወር የዋልታ ድቧ አንድ ግልገል ብቻ አስከትላ እንደነበር በካሜራ ከተቀረፀ ምስል አረጋግጧል፡፡ ከሰባት ወራት በኋላ በህዳር ወር 2025 ደግሞ ቡድኑ እናት ድቧ ሁለት ግልገሎችን አስከትላ ማግኘቱን አስረድቷል፡፡
በ2024 እ.አ.አ አንድ ግልገል አስከትላ የተመዘገበችው እና መገኛ አመላካች (ጂፒ ኤስ) የተገጠመባት እናት ድብ እና ግልገሏ ብቻ ሲሆኑ አዲሱ ግልገል መለያም ቁጥርም ሆነ መከታተያ መሣሪያ የሌለው መሆኑን አረጋግጠዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት በቀጣናው ከተመዘገቡት እና ክትትል ከተደረገባቸው 4600 ድቦች ያልወለደችውን ግልገል ስታሳድግ የተገኘች 13ኛዋ እናት ድብ መሆኗንም ነው ያሰመሩበት፡፡
በዋልታ ድቦች “ጉዲፈቻ” በጣም ብርቅዬ እና ያልተለመደ ለምን? እና እንዴት? እንደሚከሰት በውል አለመታወቁን የዓለም አቀፉ የዋልታ ድብ ጥበቃ ተቋም ሥራ አስኪያጅ አሊሳ ማክካል ባሰራጩት የቪዲዮ መልዕክት ጠቁመዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በካናዳ የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪው ኢቫን ሪቻርድሰን እንስት ድቦች ግልገሎቻቸውን በመንከባከብ በመጠበቅ እና በመደገፍ በኩል ጠንካራነታቸውን ከዓመታት የክትትል ስራቸው መገንዘባቸውን አስረድተዋል፡፡
ካናዳዊው የዋልታ ድብ ጥበቃ እና የአካባቢ እና የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተመራማሪው ኢቫን ሪቻርድሰን የእናት ድቧ እድሜ አምስት ዓመት፣ የግልገሎቹ ደግሞ ከ10 እስከ 11 ወራት ሊሆናቸው እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በመጨረሻም እናት ድቧ በበረዶ ላይ ብቻውን ቆሞ የሚጮኸውን ግልገል አይታ በ”ጉዲፈቻ” ለማሳደግ ከግልገሏ ጋር ሳታስከትለው እንደማትቀር ነው በማደማደሚያነት ያሰፈሩት -ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታህሳስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


