
ከምድር ወደ ህዋ የሚወነጨፉ “ሮኬቶችን” ወደ ማስፈንጠሪያ ማማ ለማጓጓዝ ታልሞ ሁለት የአውሮኘላን አካል ወደጐን ስፋቱ 117 ሜትር በተለካ ክንፎች ተገናኝቶ የተመረተው የአየር ላይ በራሪ በስፋቱ የዓለማችን ትልቁ አውሮኘላን ሊሆን መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
አውሮኘላኑ “ስትራቶላውንች” ወይም ሁለት የአውሮኘላን አካልን አንድ ላይ ባገናኘ ክንፍ የሚበር በቅፅል ስሙ (አርኦሲ) በሚል እንደሚታወቅ ነው የተገለፀው፡፡
ሁለቱ በክንፍ የተያያዙት የአውሮኘላን አካላት እያንዳንዳቸው 73 ሜትር ርዝመት፤ ለማረፍ እና አኮብኩቦ ለመነሳት እያንዳንዳቸው 14 በድምሩ 28 ጐማዎች ተገጥመውለታል፡፡
የክንፎቹ ስፋት 117 ሜትር ሲሆን ይህም ከአሜሪካ የእግር ኳስ ሜዳ ስፋት በ26 ሜትር ይበልጣል፡፡ የግዙፉ አውሮኘላን ንድፍ አውጪ የማይክሮ ሶፍት ኮምፒውተር መስራቹ ፖውል አለን መሆኑም ነው የተጠቀሰው፡፡ ከንድፉ ወጣኝ ፖውል አለን ህልፈት በኋላም በርካታ መሻሻሎች ተደርገውበት ባለሁለት አካል ክንፈ ረጂም አውሮኘላን ሊሰራ መቻሉን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
ከባለሁለት አካሉ አውሮኘላን አብራሪው፣ ረዳቱ እና የበረራ ኢንጂነሩ በቀኝ በኩል ያለውን፤ በስተግራ ያለው የአውሮኘላኑ አካል ግን ሰው አልባ ሆኖ ጠቅላላ የበረራ መረጃ ስርዓት መቆጣጠሪያ ሰሌዳ መገኛ ነው፡፡
አውሮኘላኑ ስድስት ሞተሮች አሉት፤ 250,000 ኪሎግራም ክብደት የመሸከም አቅምም አለው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታህሳስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

