ጥበብ አድናቂዉ ዐፄ ዳዊት

0
147

አድባር ሰገድ (ተራራ የሚሰግድላት)   በሚለው ስመ መንግሥታቸው ይታወቃሉ:: የዐፄ አድያም ሰገድ እያሱ ልጅ ናቸው፡- ዐፄ ዳዊት ሦስተኛ፤ ከ1708 እስከ 1713 ድረስ ኢትዮጵያን  አስተዳድረዋል::

በአቡነ  ማርቆስ  እና  በእጨጌ  ዘሚካኤል ተቀብተው ዘውድ ጭነዋል:: በንግሥናቸው የመጀመሪያ ዓመት የሚደነቅ ቤተ ተውኔት በማሠራታቸው ይታወቃሉ:: ለኪነ ጥበብም ልዩ ፍቅር ከነበራቸው ነገሥታት መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው::

እውቁ ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ቲያትር (ድራማ መቼ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተጀመረ ሲገልጽ በዛጉዌ ዘመነ መንግሥት ነገሥታት በቤተ መንግሥታቸው አጫዋች እንደነበራቸው እና በተለያዩ ሙዚቃዊ ድራማዎች ይዝናኑ እንደነበር ይጠቁማል:: ነገር ግን በሳልሳዊ ዳዊት ጊዜ ዘመናዊ ቲያትር)ድራማ ይሠራ እንደነበረ ፍንጭ እንዳለ ይገልጻል:: በዐፄ ዳዊት ዘመን ወጣ ያለ ባሕሪ የነበረው ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ የሚባል  ካህን ነበር:: ይህ ካህን ከሌሎች ካህናት ጋር አይስማማም ነበር:: ሌሎቹ ይኮራል፣ በእውቀቱም ከልክ በላይ ይታበያል ይሉታል:: በፍጥነት በሚቀኛቸው ቅኔዎችም ድባቅ ስለሚመታቸው የጎንደር ሊቃውንት ይፈሩታል::

አንድ ቀን ዐፄ ዳዊት ካህናቱን እና ሊቃውንቱን ጠርተዋቸው በፈረስ እና በበቅሎ ወደ ቤተ መንግሥት ሲጓዙ፣ ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ ኮራ ብሎ በእግሩ ይሄዳል:: በዚህ ጊዜ በእግሩ በመጓዙ ካህናቱ ሊዘባበቱበት ሞከሩ::እሱም በፍጥነት

“ብዙሃን አይዱግ በላእለ አይዱግ ሆሩ፣ ከረፈረለ ዮሐንስ ሊቅ እነዘ ይሐውር በእግሩ፤”

አላቸው:: ትርጉሙም “ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ በእግሩ ሲሄድ፣ ብዙ አህዮች ግን በአህዮች ላይ ይሄዳሉ” ማለት ነው::

ዐፄ ዳዊት  ካህናቱ በተለያዩ ክንዋኔዎች ላይ ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን እንደሚያገሉት ሲያውቁ ሊቁን ጠርተው “ሰው የሚኖረው ተመሳስሎ ነው፤ ካህናት ደግሞ መላዕክት ናቸው፤ ስለዚህ አብሮ ተከባብሮ መኖር ይሻላል” አሉት:: እሱም ግዕዝ አስደማሚ ቅኔ ተቀኘ፤ በግዕዝ የተናገረውን እንተወውና የአማርኛ ትርጉሙ እንዲህ ይላል፡- “በረጅም ቁመቱ ክንፍን ቢያክል እና በክንፍ ቢሠፈን መላዕክን አናከብረውም፤ ወፎች እና ትንኞችም ክንፍ አላቸውና፤ ሰውን በሽበቱ አናከብረውም፤ ድንጋይ እና እንጨትም ነጭ ሽበት ያወጣሉና፤ ሰው በእውቀቱ እንጂ በሽበቱ አይከበርም ( ሰው ሊከበር የሚገባው ከምንም ነገር በላይ በጥበቡ እና በእውቀቱ ነው)” አላቸው::

በንግግሩ ጠምደው የያዙት  ካህናቱ ደነገጡ፤ ዐፄ ዳዊት ግን ንግግሩ በክብር መዝገብ እንዲመዘገብ አደረጉ:: ወርቃማ ንግግር ጥበብ ነው፤ ይህን መሰል ነገር ደግሞ ዐፄ ዳዊት እጅግ ይወዱ ነበር:: ዐፄ ዳዊት ከአብዛኞቹ የጎንደር ነገስታት በተለየ ከአደን ይልቅ ጥበብ ይስባቸው እንደነበር ዜና መዋላቸው ይመሰክራል::

እውቁ ጥበበኛ ተዋናይ በእሳቸው ዘመን  እንደነበር አንዳንድ መዛግብት ይጠቁማሉ::ነገር ግን ከእሳቸው ጋር የተያያዘ ቀጥተኛ መረጃ አልተገኘም፤ ነገር ግን ከእሳቸው በኋላ የነገሡት ዐፄ በካፋ ከተዋናይ ጥበብ ተቀብለው በአየር ላይ ሲበሩ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ ባለማክበራቸው አለት ላይ ወድቀው እንደሞቱ ፍስሃ  ያዜ  ታሪካቸውን ባነሳበት ጽሑፍ ጠቅሷል::

በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የሃይማኖት መከፋፈል አንዱ ችግር ነበር:: ይህ ጉዳይ ቤተ መንግሥቱ ድረስ ዘልቆ በመግባት አለመረጋጋቶችን ፈጥሮ ነበር:: ንጉሥ ዳዊትም በእናታቸው አማካኝነት ራዕይ ታይቷል በሚል ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወደ ቅብዓት በመቀየራቸው በዙሪያቸው ባሉ ካህናት እና በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታን ፈጠረ:: ሊቃውንቱ እና ካህናቱ ተሰብስበው በሁለቱ እምነቶች መካከል ክርክር እዲደረግ ጠየቁ፤ ዐፄ ዳዊትም ፈቅደው ክርክሩ ተደረገ በዚህም ቅብዓቶች በክርክሩ ተረቱ ይላል ፍስሃ ያዜ:: ቀጥሎም የቅብዓት እምነት በመንግሥት እውቅናን አለማግኘቱን ከተረዱት ተከራካሪዎች መካከል  ዲዮስቆሮስ የተባለ ሰው ቀድሞ ወደ ውጪ ይወጣል:: ከወጣ በኋላም ጃዊ የተባለውን የቤተ መንግሥት ጠባቂ ጠርቶ “ንጉሠ ነገሥቱ ሁሉንም የተዋህዶ ካህናት እና ሊቃውንት ሲወጡ ጠብቀህ እርምጃ ውሰድ ብለውሃል” ይለዋል::

ጃዊ ካህናቱ እና ሊቃውንቱ ክርክሩን ጨርሰው  ሲወጡ  ጠብቆ   እንደተባለው  አደረገ:: የሰው  ደም  እንደ  ጎርፍ ወረደ፤ በክስተቱ ጳጳሱ አቡነ  ክርስቶዶሉ ብቻ ተረፉ:: ደም የፈሰሰበት ቦታ ፀበል ፈልቆበት እነደነበር እና የአካባቢው ሰው “ዋሾ ሜዳ” እያለ እንደሚጠራው   በትውፊት   ተቀምጧል:: ንጉሡም ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ በሁለቱ ጥፋተኛ ሰዎች ላይ እርምጃ አስወሰዱባቸው:: ሊቃውንቱ በጉባኤ በወሰኑት መሠረትም የተዋህዶ እምነት በነበረበት እንዲቀጥል ተወሰነ:: ዐፄ ዳዊት የገነቡት የጥበብ አዳራሽ አሁንም ድረስ በጎንደር ከተማ ይገኛል::

የአካባቢው ሰው የአድባር ሰገድ የሙዚቃ አዳራሽ እያለ ነው የሚጠራው:: ንጉሡ ለጥበብ በነበራቸው ፍቅር ለኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገትም መሠረት እንደጣሉ ይታወሳል::

ምክንያቱም አዝማሪዎች በአዳራሹ ሙዚቃቸውን  እና እስክስታቸውን ያቀርቡ ነበር:: በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ እንደ ሌሎች ንጉሠ ነገሥቶች ሁሉ አንበሶችንም በግቢያቸው ውስጥ ያረቡ ነበር:: አንበሳ የዘር ግንዳቸው ምልክት እና ለቤተ  መንግሥቱ አንዲሁም ለንጉሠ ነገሥቶቹ ግርማ ነው ተብሎ ይታሰባል:: ይህ ባሕል እስከ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ  መንግሥት ድረስ  ቀጥሎ ነበር:: የተለያዩ ድርጅቶች እና ተቋማት መለያቸው አንበሳ ነበር::

ዐጼ ዳዊት ሀቀኛ እና የሚመሩትን ሕዝብ የሚወዱ መሆናቸውን የሚቀጥለው ገጠመኝ ያሳያል:: ዐፄ ዳዊት ፀበል/ማህበር መጠጣት ይወዱ ነበር:: አንድ ጊዜ ሰውን ሰብስበው “የሰው ገንዘብ ሳይበላ በላቡ ጥሮ ግሮ የሚኖር ማነው?” ብለው ጠየቁ:: ግማሹ ዳኛ አለ፤ “ዳኛማ የሚፈርደው በመጣለት መረጃ ነው” አሉ፤  ነጋዴ አለ ሌላው- “ነጋዴ ባልገዛበት ገንዘብ ገዛሁ እያለ ይዋሻል፤ ለገንዘብም ይሳሳል” አሉ:: በዚህ ጊዜ አንዱ ተነስቶ ገበሬ ነው አለ::

“መልካም ብለሃል፤ ገበሬ መሬት የምትሰጠውን በላቡ ነው የሚበላው፤  ስለዚህ ማህበሬን ከገበሬ ጋር እጠጣለሁ፤ ከገበሬ ጋር ፀበል መጠጣት ነው የሚያጸድቀው አሉ”::

በዚህም የዙፋናቸውን ክብር ትተው እና ከገበሬዎቹ እኩል ዝቅ ብለው ፀበል መጠጣት ጀመሩ:: ዐፄ ዳዊት ሀገራቸውን በበሳል አስተዳደር ሲመሩ፣ በሕግ እና በሽምግልና ፍትህ ሲያሰፍኑ፣ የተበደለውን ሲክሱ፣ ያጠፋውን ሲቀጡ ለአምስት ዓመታት ብቻ ቢሆንም በስልጣን ኖረዋል:: ዐፄ ዳዊት በሥልጣን ላይ እያሉ በጽኑ ታመሙ:: ግንቦት 12 ቀን 1713 ዓ.ም ሕይወታቸው አለፈ::

ንጉሡ ከአለፉ በኋላ ወንድማቸው ዐፄ በካፋ በትረ ስልጣኑን ወረሱ፤ ዐፄ በካፋም ከ1713 እስከ 1723 ኢትዮጵያን መርተዋል::

ሳምንቱ በታሪክ

 

መረብ ምላሽ

ታህሳስ 24 1882 ዓ.ም የኢጣልያ መንግሥት መረብ ምላሽ ይባል የነበረውን የኢትዮጵያ አካል በኃይል ተቆጣጥሮ ኤርትራ ብሎ ሠይሞ የቅኝ ግዛት አደረገው። ከአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ፣ ኮሎኒያሊስት ጣልያን በመጀመሪያ አሰብን፤ ቀጥሎም ምፅዋን፣ ከዚያም ቀስ በቀስ አየተጓዘ አስከ መረብ ወንዝ ድረስ ያሉትን አውራጃዎች « ኤርትራ » ብሎ በመሰየም ቅኝ ግዛቱ አድርጐ ከማወጁ በፊት፡ ይህ ክፍለ ሀገር « መረብ ምላሽ ወይም ምድረ-ሀማሴን » እየተባለ ይጠራ እንደነበረ ጥንታዊ ታሪኮቹ ያሰረዳሉ።

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ የዚህን ሀገር ኢትዮጵያነት፣ ለአራቱ ኃያላን ሀገሮችና ለዓለም መንግሥታት ማህበር አመልክቶ ሲሟገት፣ መረብ ምላሽ ወይም ምድረ ሀማሴን ይባል የነበረውን የጥንቱን የሀገሩን መጠሪያ አልተጠቀመም፡፡ ማመልከቻውን ያቀረበው ኮሎኒያሊስት ጣልያን እንደሰየመው « ኤርትራ » ብሎ ነው:: በ1993 ዓ.ም እነዚህ የጥንት የመረብ ምላሽ ወንድሞቻችን ነፃነታቸውን ሲያውጁ፤ በዚሁ ጣልያን በስየመው « ኤርትራ በተባለው መጠሪያ ቀጥለዋል።

ምንጭ፡- የኤርትራ ጉዳይ፡- ፕ/ር ዘውዴ ረታ

 

ቼኮዝሎቫኪያ

የቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ በሰላማዊ ስምምነት ለሁለት ተከፍላ የቼክ ሪፑብሊክ እና ስሎቫኪያ በተባሉ ሉዐላዊ ሀገራት ተተካች። መገናኛ ብዙሀን ይሄንን ከፈላ ‘የሐር ፍች’ (Velvet Divorce) የሚል ሥያሜ ሰጥተውታል። ቼኮዝሎቫኪያ በናዚ ጀርመን የከፋፍለህ ግዛ ትርክት እና በጨቋኝ ተጨቋኝ የፈጠራ ትርክት መከፋፈሏን የዎርልድ አትላስ መረጃ ያሳያል፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የታህሣስ  20  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here