አልችልም እና እችላለሁ!

0
206

 

በአንድ ወቅት ታዋቂው አሜሪካዊ ጸሐፊ እና ፈላስፋ ዊሊያም ጀምስ “የእኔ ትውልድ ያገኘው ታላቅ ግኝት የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ዘይቤውን በመቀየር ህይወቱን መለወጥ እንደሚችል ማወቁ ነው” ብሎ ነበር። ይህ አባባል ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በነርቭ ሳይንስ እና በስነልቦና ጥናት ተረጋግጦ “ማይንድ ሴት” በሚል ጽንሰ ሀሳብ ስር የዓለምን ትኩረት ስቧል። ለመሆኑ ማይንድ ሴት ምንድን ነው? አዕምሯችን እንዴት ነው የሚሰራው? ለአንድ ግለሰብ አልፎም ለአንድ ሀገር የብልጽግና ወይም የድህነት ምንጭ ሊሆን ይችላልን?

በቀላል አማርኛ ማይንድ ሴት ማለት “የአስተሳሰብ ማዕቀፍ” ወይም “የአመለካከት ልጓም” ማለት ነው። ይህ ስለ ራሳችን፣ ስለ ችሎታችን፣ ስለ ዓለም እና ስለ ክስተቶች ያለን ጥልቅ እምነት ነው። የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ካሮል ድዌክ “ማይንድ ሴት ዘ ኒው ሳይኮሎጂ ኦፍ ሰክሰስ” በተሰኘውና ዓለምን በለወጠው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ ማይንድ ሴት ማለት ባህሪያችንን፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እና የህይወት ስኬታችንን የሚወስን ድብቅ ሞተር ነው።

ማይንድ ሴት ዝም ብሎ አዎንታዊ ማሰብ ብቻ አይደለም። ከዚያ የጠለቀ ነው። ችግሮች ሲያጋጥሙን እንዴት ምላሽ እንሰጣለን? ውድቀትን እንደ መጨረሻ ወይስ እንደ መማሪያ እንወስደዋለን? የሚሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች የሚመልስ የአዕምሮ ፕሮግራም ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ አዕምሮ እድገት ከተወሰነ ዕድሜ በኋላ ይቆማል ብለው ያምኑ ነበር። ነገር ግን ዘመናዊው የነርቭ ሳይንስ ጥናት ይህንን አስተሳሰብ ገልብጦታል። “ኒውሮ ፕላስቲሲቲ” የሚባለው ሳይንሳዊ ግኝት እንደሚያሳየው፤ አዕምሯችን ልክ እንደ ጡንቻ ነው። በተማርን፣ አዲስ ነገር በሞከርን እና በደጋገምን ቁጥር በአዕምሯችን ውስጥ ያሉ የነርቭ ሴሎች አዳዲስ ግንኙነቶችን ይፈጥራሉ።

ይህ ማለት ማንም ሰው በተፈጥሮ “ጎበዝ” ወይም “ሰነፍ” ሆኖ አይቀርም ማለት ነው። የአስተሳሰብ ማዕቀፋችንን ከቀየርን፣ የአዕምሯችንን ቅርጽ እና አቅም ማሻሻል እንችላለን። ማይንድ ሴት በባዮሎጂያዊ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ዶ/ር ካሮል ድዌክ በአስርተ ዓመታት ጥናት የሰው ልጅን ማይንድ ሴት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍሉታል። ቋሚ/የተገደበ አስተሳሰብ የመጀመሪያው ነው።

በዚህ ምድብ ውስጥ ያሉ ሰዎች “ችሎታ፣ ብልህነት እና ተሰጥኦ በተፈጥሮ የሚሰጡና የማይለወጡ ናቸው” ብለው ያምናሉ። ለእነርሱ ውድቀት ማለት ችሎታ ቢስነት ማለት ነው። ስለሆነም ተግዳሮቶችን ይሸሻሉ። ትችትን አይቀበሉም። እንዲሁም የሌሎችን ስኬት እንደ ዛቻ ይቆጥራሉ። “ይሄ ለእኔ አይሆንም”፣ “እኔ በተፈጥሮዬ የሂሳብ ጭንቅላት የለኝም” የሚሉ አባባሎች የዚህ ማይንድ ሴት መገለጫዎች ናቸው።

ሁለተኛው አዳጊ አስተሳሰብ ነው። እነዚህ ግለሰቦች “ችሎታ እና ብልህነት በጥረት፣ በልምምድ እና በትምህርት ሊዳብሩ ይችላሉ” ብለው ያምናሉ። ለእነርሱ ውድቀት ማለት “እስካሁን አልቻልኩም” ማለት እንጂ “አልችልም” ማለት አይደለም። ተግዳሮቶችን ይወዳሉ፣ ከስህተታቸው ይማራሉ፣ ጥረትን እንደ ስኬት መንገድ ያያሉ።

እድገት ተኮር ማይንድ ሴት ያለው ግለሰብ በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አይሰበርም። ለምሳሌ አንድ ተማሪ በፈተና ቢወድቅ፣ የበለጠ ማጥናት አለብኝ ብሎ ይነሳል እንጂ እኔ ደደብ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቆርጥም። በዚህ ማእቀፍ የሚያስቡ ሰዎች በስራ ዓለምም አዳዲስ ክህሎቶችን ለመማር ዝግጁ ስለሆኑ የፈጠራ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ሁልጊዜ የመውጫ ቀዳዳ እንደፈለጉ ናቸው። ሁልጊዜ ችግሮችን ወደ ማደጊያ እድል የሚለውጡ ናቸው።

በአንጻሩ ቋሚ ማይንድ ሴት ያለው ሰው፣ አቅሙን ራሱ በሰራው የአስተሳሰብ ወሰን ይገድበዋል። ትንሽ እንቅፋት ሲያጋጥመው መንገዱን ያቆማል። በቃ ለትምህርት ወይም ለስኬት አልተፈጠርሁም ብሎ ያስባል። እምነቱን ይቀበለዋል። በሒደት እምነቱ ሕይወቱ ይሆናል። አልችልም እንዳለው የማይችል ይሆናል።  ይህ ደግሞ ለድብርት እና ለዝቅተኛ በራስ መተማመን ይዳርጋል።

የማይንድ ሴት ጉዳይ ከግለሰብ አልፎ የሀገርን እጣ ፈንታ ይወስናል። አንዲት ሀገር በዜጎቿ ድምር ውጤት የምትገነባ ናት። እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ ወይም ሲንጋፖር ያሉ ሀገራት ከዝቅተኛ ደረጃ ተነስተው የለሙበት ምስጢር፣ ህዝቦቻቸው የነበራቸው “እችላለሁ/እንችላለን” የሚል የጋራ ማይንድ ሴት ነው። ሀብት ከተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ከሰው አዕምሮ እንደሚመነጭ ያመኑ ማህበረሰቦች ለትምህርት እና ለቴክኖሎጂ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ።

በቋሚ ማይንድ ሴት የተተበተበ ማህበረሰብ ለችግሮቹ ሁሉ ውጫዊ ምክንያቶችን ብቻ ይፈልጋል። “ድህነታችን የተፈጥሮ ነው” ወይም “ዕድላችን ነው” ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ ፈጠራን አይቀበልም። ለውጥን ይፈራል። ባህላዊ አሰራሮችን ብቻ ሙጥኝ ይላል። ይህ ለሀገር ኢኮኖሚ ውድቀት እና ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት አይነተኛ መንስኤ ነው።

የኒውሮ ሳይንስ ምሁራን እንደሚያረጋግጡት ማይንድ ሴት ሊቀየር የሚችል ነገር ነው። ለዚህም የሚከተሉት ነጥቦች ወሳኝ ናቸው። የመጀመሪያው መፍትሔ ቃላትን መቀየር ነው። “አልችልም” ከማለት “እስካሁን አልቻልኩም” ማለትን መለማመድ። ነገ እለወጣለሁ የሚል እምነት በውስጡ አለ።

ቀጣዩ ጥረትን ማድነቅ ነው። በቤተሰብም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ ልጆችን ስለ ተፈጥሮ ችሎታቸው ሳይሆን ስለ ጥረታቸው እና ስለ ስራ ሂደታቸው ማድነቅ ያበረታታቸዋል። ይህ በራስ መተማመንን ይገነባል። የመጨረሻው ስህተትን እንደ መማሪያ መውሰድ ነው። ስህተት ሲፈጠር መደበቅ ሳይሆን ከስህተቱ ምን እንደተገኘ መተንተን ወደ ፊት ለሚራመድ አዳጊ ሕይወት ይጠቅማል።

ማይንድ ሴት ምርጫ ነው። በቅርጫት ኳስ ዓለም የምንጊዜም ምርጥ ተብሎ የሚጠራውን ማይክል ጆርዳንን እንውሰድ፤ ተራ ሰው ከትምህርት ቤት ቡድን ሲቀነስ “ተሰጥኦ የለኝም” ብሎ ሜዳውን ለቆ ይወጣል። ማይክል ጆርዳን ግን አሰልጣኙ “አትሆንም” ሲለው አልተከፋም፣ ሌሊት እየተነሳ በልምምድ ራሱን አሳደገ እንጂ።

ጆርዳን ግን ውድቀትን በላብ አሸንፎ ስድስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን በመሆን ታሪክ ሠራ። በየቀኑ ከእንቅልፋችን ስንነሳ ዓለምን በምን አይነት መነጽር እንደምናይ መምረጥ አለብን። ሕይወት በሁለት ጽንፎች የተሞላች ናት። ብርሀን አለ፤ ጨለማውም እንዲሁ። በሚሞተው ብናዝንም በሚወለደው ደግሞ እንደሰታለን። ማግኘት ሲያልቅ ማጣት ይገለጣል። ጦርነትም ሰላምም ሁልጊዜ ያሉ ነገሮች ናቸው። ልዩነት የሚፈጥረው እኛ “የትኛውን ነው እያየን ያለነው?” የሚለው ነው።  የዜጎች የአዕምሮ ግንባታ ወሳኝ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ከቋሚ አስተሳሰብ ወደ እድገት ተኮር አስተሳሰብ ከተሸጋገረ፣ የማይቻል የሚመስለው የሀገር እድገት እውን ይሆናል።

ዛሬ ራሳችንን እንጠይቅ። ስለ ራሳችን እና ስለ ሀገራችን ያለን ማይንድ ሴት የትኛው ነው? መልሱ የነገ ህይወታችንን ይወስናል።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታህሣስ  20  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here