ሞሮኮ

0
76

‘እ.ኤ.አ በ1988 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት በሞሮኮ ንጉሥ ሐሰን ዳግማዊ በተሰጠ መመርያ ይህ ስታዲየም ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ይድነቃቸው ተሰማ ሥም እንዲሰየም መጋቢት 1988 ዓ.ም ላይ ተወስኗል።’’ የሚል መልእክት በፈረንሳይኛ እና አረብኛ ቋንቋዎች ተፅፎ በሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ በሚገኝ አንድ የእግር ኳስ ስታዲየም መግቢያ ላይ ይነበባል።

ለአፍሪካ መብት በፊፋ መድረኮች ሁሉ አጥብቆ ለታገለበት አፓርታይድን ከስፖርቱ በማገድ የፀና አቋሙ አደብ ያስገዛ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ሽንጡን ገትሮ የታገለ ቆራጥ የዘመኑን የካፍ ፕሬዝደንት ይድነቃቸው ተሰማን ሞሮካውያውያን “የጅብራልተሩ አለት” እያሉ ያሞካሹታል። የጅብራልተር አለት ማለት በሜዲትራንያን ባህር ላይ ቀጥ ብሎ የቆመ ከ400 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ጠንካራ የአለት ቋጥኝ ነው። የደህንነት እና የጥንካሬ መገለጫም ተደርጎ በስፋት የሚቀኙለት ድንቅ ተፈጥሯዊ ስፍራ ነው።

ለአፍሪካ ስፖርት አባት ተደርጎ ለሚታሰበው ብርቱ እና ታላቅ ሰው ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በአለም ዋንጫ አፍሪካ ብቻ ኮታ አልባ የነበረችበትን ታሪክ ያስቀየረ ብርቱ ተሟጋች፣ ለአቋሙ እስከ ጥግ የሚታገል ደፋር እና አስተዋይ ታጋይ ስለነበር በዚህ ቅፅል ስሙ ይጠሩት እንደነበር ይነገራል። አሁን ደግሞ 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገር ሞሮኮ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ለሽርሽር መርጠናታል። እነሆ ሞሮኮ!

የሞሮኮ ታሪክ ከበርበር ወይም ከአማዚግ ሕዝቦች ዘመን ይጀምራል። ከዚያ በኋላ ፊንቄያውያን፣ ሮማውያን፣ አረቦችና አንዳንድ የአውሮፓ ኃይሎች ተጽዕኖ አሳድረዋል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሞሮኮ በፈረንሳይና በስፔን ግዛት ስር ቆይታ ካደረገች በኋላ 1948 ዓ.ም ነፃነቷን አገኘች። ዛሬ ንጉሳዊ ሥርዓት ያላት ዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ናት።

ሀገረ ሞሮኮ በሰሜን በኩል የሜዲትራኒያን ባህር እና የጅብራልታር የባህር ወሽመጥ ያዋስኗታል፤ በደቡብ ከሞሪታኒያ፣ በምስራቅ ከአልጄሪያ እና በምዕራብ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ትዋሰናለች። ሞሮኮ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥዋ ምክንያት በታሪክ ጉልህ የንግድ ማዕከል ሆና ቆይታለች።

ሞሮኮ በታሪክ የከበረች እና በባህላዊ ቅርሷ የምትታወቅ፣ የበርካታ ታሪካዊ ከተሞች መኖሪያ ናት። በታሪካዊ ከተሞች ውስጥ ያሉ የስነ-ህንፃ መዋቅሮች የጊዜያቸውን ውበት እና የምህንድስና ስኬቶች ያንፀባርቃሉ። በሞሮኮ ያለው የአየር ንብረት በአጠቃላይ በሜዲትራኒያን ተጽዕኖ ስር ነው፣ ነገር ግን የተለያዩ የአየር ንብረት ዓይነቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሊታዩ ይችላሉ። በሰሃራ በረሃ በተጎዱት ደቡባዊ ክልሎቿ ላይ ሞቃታማ እና ደረቅ የአየር ንብረት አለ፤ የአትላስ ተራሮች በረዶም ቀዝቃዛማ ክረምትን ያመጣል።

ሞሮኮ በታሪካዊ ቅርሶቿ፣ በሰማያዊ ቀለም የተዋቡ ከተሞች፣ ባልተለመዱ ገበያዎቿ እና ጣፋጭ ምግቦቿ ትታወቃለች፣ ይህም ለጎብኝዎች ተወዳጅ መዳረሻ ያደርጋታል። ታዲያ እነዚህን ታሪካዊ እና ባህላዊ ከተሞቿን በጥቂቱ እንመልከት።

ካዛብላንካ

ካዛብላንካ በተንጣለለው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ በኩል የምትገኝ ውብ የሞሮኮ ድምቀት የሆነች ከተማ ናት። በሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎቿ፤ በአለም ትልቁ የንጉሥ ሀሰን ዳግማዊ መስጅድ አስደማሚ ገፅታ በአንድ ድንጋይ…እንዲሉ የካዛብላንካን ታሪክ እና ባህል ፍንጭ ከመስጠት በተጨማሪ የጎብኝዎቹን ቀልብ ይገዛል። የካዛብላንካ ጎዳናዎች የድሮውን እና የዘመኑን እንዲሁም ባህላዊውን እና ዘመናዊውን ነገሮች በአንድ በማዋሃድ ልዩ ሁኔታን ይፈጥራሉ። በታሪካዊ ባህሪዋ እና በዘመናዊ መዋቅሮቿ ካዛብላንካ ለእያንዳንዱ ጎብኝዎቿ ልዩ ትዝታን የምትተክል እስከዛሬ ቱሪስቶችን እያስተናገደች የቀጠለች የሞሮኮ ማራኪ ከተማ ናት።

ማራኬሽ-”ቀይዋ ከተማ”

በሞሮኮ ሁለተኛዋ ትልቅ እና ዝነኛ የቱሪስት ከተማ የሆነችው ማራኬሽ በመሃል የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ የምትገኝ ሌላኛዋ የሞሮኮ ታሪካዊ ከተማ ስትሆን “ቀይዋ ከተማ” እየተባለችም ትጠራለች። ማራኬሽ በሞሮኮ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑ ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ናት። ይህች ከተማ የአፍሪካ ባህል እና የስነ-ህንፃ ቅርስ ጎልታ የምትታይ ሲሆን በቅርብ ዓመታት ውስጥ የቱሪስቶችን ትኩረት መሳብ ችላለች። በመዲናዋ በቀይ ድንጋይ የተገነቡ ቤቶች እና ግድግዳዎች በስፋት የሚታዩ በመሆኑ “ቀይዋ ከተማ” ልትባል እንደቻለች ይነገራል። የሞሮኮ የኪነ ጥበብ እና የስነ-ህንፃ ዋና ከተማ ተደርጋም ትቆጠራለች። በከተማው ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ እና ባህላዊ መዋቅሮች የተለያዩ ባህሎችን መስተጋብር ያንፀባርቃሉ። ጠባብ ጎዳናዎች፣ ጫጫታ ያላቸው ሱቆች፣ ጥንታዊ ሕንፃዎች እና አስደናቂ የማራኬሽ ስነ ሕንፃ በጎብኚዎች ልብ ውስጥ የማይረሳ ትዝታን ይተክላሉ። ደማቅ ገበያዎቿ፣ የአካባቢው የእጅ ጥበብ ስራዎች እና ባህላዊ የሞሮኮ ምግቦች የከተማዋን ተወዳጅነት ያጎሉታል። ከዚህም በላይ ማራኬሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው የፊልም ፌስቲቫሏ ትታወቃለች።

ፌዝ-ነፋሻማዋ ከተማ

ነፋሻማዋ ከተማ እየተባለች የምትታወቀው ሌላኛዋ የሞሮኮ ከተማ ፌዝ ትባላለች። በፋስ ውስጥ ካሉ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ እንደሆነች ተደርጋ ትቆጠራለች። በአትላስ ተራሮች ግርጌ ላይ በቡሁዳ ሸለቆ ውስጥ ትገኛለች። ፌስ የቱባ ታሪክ ባለቤት ስትሆን ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ በርካታ የቀደምትነት መዋቅሮች የምታዩባት ታሪካዊ መዲና ናት። በጠባብ ጎዳናዎቿ እና በባህላዊ ገበያዎቿ የምትታወቅ አስደናቂ ቦታ ናት። የፌዝ መመስረት ምክንያት ከነቢዩ ሙሐመድ የዘር ሐረግ የሚመነጨው የኢድሪስ ሥርወ መንግሥት ነው። ከተማዋ የተሰየመችው ይህንን ሥርወ መንግሥት በመሠረተው የመጀመሪያው ገዥዋ ኢድሪስ በተባለው ስም ነው። በዚያ ዘመን ለነበሩት ታሪካዊ ሕንፃዎች ምስጋና ይግባውና ፌዝ ለጎብኚዎች ጥልቅ ታሪካዊ ልምዶችን ታጎናፅፋለች። ፌዝ ወይም የእውቀትና የሃይማኖት ማዕከል እየተባለች በምትታወቀው መዲናዋ እንጀምር እና ፌዝ በ9ኛው ክፍለ ዘመን የተመሰረተች ሌላኛዋ የሞሮኮ ታሪካዊ ከተማ ናት።  ይህ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ላይ እስካሁን ስራቸው ቀጥለው ከሚገኙ እድሜ ጠገብ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የአል-ካራዊይን ዩኒቨርሲቲ መገኛ ናት። በተጨማሪም ፌዝ ያላት ባህላዊና ታሪካዊ ጠቀሜታ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ አስመዝግቧታል። በዚህም ምክንያት ፌዝን የሚጎበኙ ሰዎች ታሪካዊ ጨርቆቿን ወይም አልባሳትን እና የተፈጥሮ ውበቷን የመመርመር እድል ያገኛሉ።

ራባት

የሞሮኮ ዋና ከተማ እና ትልቋ ከተማ ራባት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ክልል ውስጥ ትገኛለች። ራባት የሀገሪቱ የፋይናንስ ማዕከል ሆናም ትታወቃለች። በአትላንቲክ የባህር ዳርቻ ላይ እንደመገኘቷ አስደናቂ ውበትን ደርባለች። በከተማዋ ከአረብኛና ከፈረንሳይኛ በተጨማሪ እንግሊዝኛ በስፋት ይነገራል፤ ንጹህ ጎዳናዎችና ሰማያዊ ቀለም የተቀቡ ቤቶች ታዋቂ ገጽታዎቿ ናቸው። ራባት ዘመናዊ የሥነ ሕንፃና ባህላዊ ዲዛይኖችን አክብራ የምትጠብቅ ስትሆን፣ ይህም ለጎብኚዎች የበለፀገ ታሪካዊና ባህላዊ ልምድን ይለግሳል። ከሌሎች የሞሮኮ ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ከተማዋ የበለጠ የተረጋጋችና ሰላማዊ ከባቢ አየር አላት። በሙዚየሞች፣ በታሪካዊ ቦታዎች እና ጣፋጭ ምግቦች አማካኝነት ራባት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ይስባል። የከተማዋ ታሪካዊ ሀብትና የተፈጥሮ ውበት ለጎብኚዎች የማይረሳ ተሞክሮ ይሰጣቸዋል።

መክነስ

ብዙውን ጊዜ የሞሮኮ ድብቅ ዕንቁ በመባል የምትታወቀው መክነስ ከተማ ለጎብኚዎች አስደናቂ ድባብን የመጎብኘት እድል ይሰጣል። ዜሊጅ በመባል በሚታወቁ ባህላዊ የሞዛይክ ንጣፎች የተጌጠው ታላቁ የባብ ማንሱር በር በከተማው ላይ ካለው ከፍ ያለ ቦታ በኩራት ቆሞ ሲታይ ትኩረትን ይስባል። ይህ አስደናቂ መግቢያ የመክነስን ኦሪዮናዊ እሴት እና የበለፀገ ታሪክ ያንፀባርቃል። የመክነስ ጎዳናዎች በታሪካዊ እና ባህላዊ ሀብቶቿ አሸብርቀው መታየት የሞሮኮ ቨርሳይለስ የሚል መጠሪያ አሰጥቷታል። ጎብኝዎች የከተማዋን አስደማሚ ገፅታዎች አድንቀው ሳያበቁ በአስደማሚው ታሪካዊ ሕንፃዎቿ እና በባህላዊ ገበያዎቿ መደሰት ይችላሉ። የመክነስ መዲና በዩኔስኮ እውቅና የተሰጣቸው በርካታ ታሪካዊ ስፍራዎችን ይዛለች።  በመሆኑም መክነስ ለጎብኝዎቿ ልዩ የሆነ የሞሮኮን ታሪካዊ እና ባህላዊ ልምዶችን በመስጠት የምታስደምም የሞሮኮ እንቁ ከተማ ናት።

በአጠቃላይ ሞሮኮ ታሪክን ከዘመናዊነት፣ ባህልን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር በሚያጣመር ሁኔታ የተገነባች ሀገር ናት። ታሪካዊ ከተሞቿ የአፍሪካና የአረብ ሥልጣኔ ሕያው ምስክሮች ሲሆኑ፣ ዛሬም በቱሪዝም፣ በኢኮኖሚና በስፖርት ዓለም ላይ ተጽዕኖዋን እየጨመረች ትገኛለች።

 

አጫር እዉነታ

የሞሮኮ እውነታዎች

  • ሞሮኮ በሰሜን አፍሪካ ትገኛለች።
  • ከአትላንቲክ ውቅያኖስና ከሜዲትራኒያን ባሕር ጋር ዳርቻ አለው።
  • ዋና ከተማዋ ራባት ናት፤ ትልቋ ከተማ ደግሞ ካሳብላንካ ናት።
  • ሞሮኮ ንጉሳዊ መንግሥት (Monarchy) ናት።
  • ዋና ቋንቋዎቿ አረብኛና አማዚግኛ (በርበር) ናቸው።
  • ህዝቧ አብዛኛው ሙስሊም ነው።
  • የሳሃራ በረሃ ክፍል በደቡብ ሞሮኮ ይገኛል።
  • የአትላስ ተራሮች ሀገሪቱን ይቆራረጣሉ።
  • ኩስኩስና ታጂን ታዋቂ ምግቦቿ ናቸው።
  • ፌዝ፣ ማራኬሽና መክኔስ ታሪካዊ ከተሞቿ ናቸው።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የታህሣስ  20ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here