የተጽዕኖ ሁለት ሰይፍ

0
118

ከአስር ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ ሰው የሚባሉት በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ጋዜጠኞች፣ የፊልም ተዋንያን ወይም ድምጻዊያን ነበሩ። ዛሬ ግን ይህ ትርጉም ተቀይሯል። በመኝታ ቤታቸው ሆነው በሚቀረጹት የቲክቶክ ቪዲዮ ወይም በዩቲዩብ ቻናላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን ያፈሩ ወጣቶች የአዲሱ ዘመን “ኮከቦች” ወይም “ኢንፍሉዌንሰሮች” ሆነዋል።

ለተጽዕኖ ፈጣሪዎች መብዛት ዋናው ምክንያት የኢንተርኔት ተደራሽነት መስፋፋት ነው። ዳታ ፖርታል እ.አ.አ 2024 ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ30 ሚሊዮን በላይ አልፏል። የኢትዮ ቴሌኮም የ4G ኢንተርኔት ሽፋን መስፋፋት እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ገበያ መግባት ዳታ በቀላሉ እንዲገኝ እና ስማርት ስልኮች እንዲበራከቱ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ያለው የኢንፍሉዌንሰር ዘርፍ በዋናነት በሦስት ሊከፈል የሚችል ነው። ቀልድ እና መዝናኛ በቲክቶክ እና ዩቱዩብ የሚሰሩት የመጀመሪያውን መስመር ይይዛሉ። ፋሽን እና አኗኗርን ደግሞ በማሳየት ዝነኞች የሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሁለተኛው ምድብ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። በዚህ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የውበት እና የኑሮ ዘይቤያቸውን ለሌሎች በማሳየት የሚሰሩ ናቸው።

በዩቲዩብ እና በፌስቡክ ትንታኔ የሚሰጡ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች የፖሊቲካ እና ወቅታዊ ጉዳዩን በመተንተን የሚሰሩት ስራ ሦስተኛውን ዘርፍ ይይዛል። ይህ ዘርፍ አሁን ከመዝናኛነት አልፎ ወደ ሙያ እና ስራ ተቀይሯል። ተቋማት አሁን የድሮ መስመራቸው ብቻ እንደማያስቀጥላቸው የተገነዘቡበት ጊዜ ነው። ድሮ ማስታወቂያ የሚያሰሩት ቴሌቪዥን ላይ ብቻ ነበር። አሁን ባንኮች እና ትልልቅ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እነዚህን የዲጂታል ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን እየተጠቀሙ ነው።

የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተጽዕኖ በሁለት መልኩ የሚታይ ነው። አሉታዊ እና አዎንታዊ ውጤቶች አሉት። በበጎዎቹ ስንጀምር የዲጂታል ግብይት አንዱ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የባንኮች፣ የቴሌኮም እና የኮንስትራክሽን፣ የሪልስቴት እና ሌሎች ኩባንያዎች የማስታወቂያ በጀት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ዞሯል።

ይህ ዘርፍ ለወጣቶች ራሱን የቻለ የስራ መስክ ሆኗል። ዩቲዩብ ለይዘት ፈጣሪዎች የሚከፍለው ክፍያ ብዙዎችን ከድህነት አውጥቷል። በኢንስታግራም እና በቴሌግራም የሚደረጉ የታዋቂ ሰዎች ማስታወቂያዎች፣ ትናንሽ የልብስ እና የጫማ ሻጮች ምርቶቻቸውን ለብዙ ህዝብ እንዲያደርሱ ረድቷቸዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ በጎ አድራጎት ተግባራት ሳይጠቀሱ ከማይታለፉት ጉልህ ሚናዎች አንዱ ነው። ታዋቂ ወጣቶች የማህበረሰብን ችግር በማጋለጥ እና መፍትሄ በመፈለግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ለበጎ ተግባር እንዴት እንደሚውል ብዙዎች አሳይተዋል።

ዝነኞቹ በቲክቶክ እና በፌስቡክ በሚደረጉ ጥሪዎች ለህክምና የሚሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ብር በሰዓታት ውስጥ ይሰበስባሉ። ይህም “ጎ ፈንድ ሚ” (ገንዘብ የመሰብሰብ) ባህል እንዲዳብር አድርጓል።

ቀደምት ሚዲያዎች (ጋዜጣ፣ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ) ሊሸፍኗቸው የማይችሏቸውን ወይም የሚተዋቸውን ጉዳዮች ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በነጻነት ያነሳሉ። ይህም ህዝቡ አማራጭ መረጃ እንዲያገኝ አድርጓል። አሁን መረጃን ማፈን የሚቻልበት ዘመን እንዳልሆነ ማህበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙ ዝነኞች አሳይተዋል።

ጥቅሙን እንደዘረዘርን ሁሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተግዳሮቶች እና ቀውሶችም ያሉበት ነው። ምንም እንኳን በጎ ጎኖች ቢኖሩትም፣ በኢትዮጵያ ያለው የተጽዕኖ ፈጣሪዎች እንቅስቃሴ ያለ አቅጣጫ የሚጓዝ ባቡር ይመስላል።

እንደ ዩኔስኮ እና ኢትዮጵያ ቼክ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ ግጭቶች እንዲባባሱ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሚሰራጩ ያልተጣሩ መረጃዎች ናቸው። ብዙ ይዘት ፈጣሪዎች ዕይታ ለማግኘት ሲሉ አርዕስቶችን በማጋነን፣ የሌለ ታሪክ በመፍጠር እና ጥላቻን በመቀስቀስ ህዝብን ከህዝብ ያጋጫሉ። የጋዜጠኝነት ስነምግባር ስለሌላቸው የአንድን ግለሰብ ክብር የሚነኩ እና ህጋዊ መሰረት የሌላቸው ወሬዎችን ያራግባሉ።

የባህል መሸርሸር እና የሞራል ቀውስ ቀጥሎ የሚመጣው ጉዳት ነው። በተለይ በቲክቶክ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ባህል እና እሴት ጋር የሚጋጭ እየሆነ መጥቷል። ታዋቂ ለመሆን ሲባል የሚሰሩ ነውረኛ ተግባራት፣ ስድቦች እና ግጭቶች ለወጣቱ ትውልድ “ታዋቂነት ማለት መሳደብ ነው” የሚል የተሳሳተ ትምህርት እየሰጡ ነው።

ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሚያሳዩት የተጋነነ የቅንጦት ህይወት ተከታዮቻቸው በራሳቸው ህይወት እርካታ እንዲያጡ እና ወደ ጭንቀት እንዲገቡ፤ አንዳንዴም ያንን ህይወት ለማግኘት ወደ ወንጀል እንዲገቡ ይገፋፋል። ወጣቱ የቁስ አምልኮ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ተግባራት በብዛት ይታያሉ።

መንግሥት “የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አዋጅ” ቢያወጣም አፈጻጸሙ ላይ ክፍተቶች አሉ። ከሰሞኑ የጀመራቸው ሕገወጥ ያላቸውን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር ጥሩ ጅምር ነው። ታዋቂዎች እንደ መደበኛ ንግድ ተመዝግበው ግብር አይከፍሉም፤ ተጠያቂነትም የለባቸውም። ማንም ሰው ካሜራ ይዞ ተነስቶ “ጋዜጠኛ ነኝ” በማለት ተቋማትን እና ግለሰቦችን ሲያብጠለጥል ይታያል።

የወደፊቱ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ በርግጥ ለውጦች የሚታዩበት ነው። የኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ በሽግግር ወቅት ላይ ይገኛል። በጊዜ ሒደት ሁሉም መጥራቱ አይቀርም።

ገበያው እያደገ ሲመጣ ተመልካቾች ጥራት ያለው ይዘት መፈለጋቸው አይቀርም። ዝም ብሎ ካሜራ ፊት መጮህ ወይም መደነስ ብቻውን አዋጭነቱ ይቀንሳል። ወደፊት ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እንደ ተቋም ተደራጅተው ኤዲተሮች እና ጽሑፍ አዘጋጆችን ቀጥረው የሚሰሩበት ጊዜ ይመጣል። አሁንም ይህ ተጀምሯል። ድርጅቶችም ዝም ብለው ተከታይ ያለውን ከመምረጥ ከብራንዳቸው ጋር የሚሄድ ስነምግባር ያለውን ይዘት ፈጣሪ መምረጥ ይጀምራሉ።

መንግሥት ይህንን ዘርፍ ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባቱ አይቀሬ ነው። በቅርቡ እንደታየው የዩቲዩብ እና የቲክቶክ ገቢ ግብር እንዲከፈልበት እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል። በዚህም የይዘት ቁጥጥር ይጠነክራል ተብሎ ይጠበቃል። እናም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ሊቀንስ ይችላል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) መምጣት የኢትዮጵያን ይዘት ፈጠራ ይቀይረዋል። AIን በመጠቀም የተሻሉ ቪዲዮዎችን የሚሰሩ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይበልጥ ተቀባይነት ያገኛሉ። ፈጠራ እና ጥራት ላይ መጨነቅ ብዙዎችን ወደ ኋላ ጥቂቶችን ወደ ፊት ሊያደርግ ይችላል። ፍሬ ከገለባው የሚለይበት ጊዜ ይመጣል።

የኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ኢንፍሉዌንሰር እንቅስቃሴ “ሁለት ጠርዝ ያለው ሰይፍ” ነው። በአንድ በኩል ለወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ እና መረጃን ያቀለለ ሲሆን በሌላ በኩል ለሀገር ሰላም እና ለባህል ጠንቅ የሆኑ ተግዳሮቶችን ይዞ መጥቷል። አጠቃቀሙን ማወቅ መውጫ መንገዱ ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታህሳስ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here