እንግሊዝን የተጋፈጠዉ ንጉሥ

0
163

“ዐፄ ቴዎድሮስ በጣና ሐይቅ ላይ የሚንሳፈፉ ጀልባዎችን ለማሠራት የነበራቸው ምኞት ብርቱ ስለነበር የሌሎችን ትብብር ለማግኘት ሲሉ ራሳቸው ወርደው መርከብ መሥራት ጀመሩ። ሰፋ ያለ ወለልና ከባድ መንኮራኩር ያለው ተንቀሳቃሽ ጀልባ ሠሩ:: በጭስ የሚሰራ ጀልባ ፈልስፈውም ሠርተዋል::… ጀልባዋን በሐይቁ ውስጥ ብዙ ጊዜ እናያት ነበር” ይህን ያለው እውቁ እንግሊዛዊ ተጓዥ ሄነሪ ብላንክ ነው:: ዐፄ ቴዎድሮስ ስልጣን ከያዙ መባቻ ጀምሮ ሀገራቸው በእድገት ጎዳና እንድትጓዝ እና ሕዝባቸውም ስልጣኔ እንዲገባው ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው:: በመሆኑም ከላይ ያየነውን አይነት እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር:: ሌላው ደግሞ የእንግሊዝን እና  ሌሎችን የአውሮፓ ሀገራት ድጋፍ ማግኘት እና መሰልጠን ነበር ውጥናቸው:: ሆኖም እንግሊዝም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ሊተባበሯቸው ፈቃደኛ አልነበሩም:: ይልቁንም ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛታቸው አካል ማድረግ ይፈልጉ ነበር::

እንግሊዝ ዐፄ ቴዎድሮስ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ሎርድ ማኩሌ በተሰኘ ግለሰብ አማካኝነት እ.አ.አ 1835 በፓርላማዋ ኢትዮጵያን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል በጥናት የተመሠረት ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ነበር:: ግለሰቡ የኢትዮጵያን እምቅ ተፈጥሮዋዊ ሀብት ያነሳና ነገር ግን ሕዝቡ የጠነከረ እሴት እና ማንነት እንዳለው ይጠቅሳል:: ይሄን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ እሴቱን ሰባብሮ በቁጥጥር ስር ለማዋል የነበረ እምነቱን እና ማንነቱን በመሸርሸር እርስ በርስ ከፋፍሎ የአውሮፓዊያን ተገዢ ማድርግ እንደሚቻል አስቀምጧል::

በዚህ ምክረ ሀሳብ መሠረት እንግሊዝ ለዓመታት የዘለቀ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ሙከራ ስታደርግ ነበር:: በዚህ ምክንያት ዐፄ ቴዎድሮስ አግዙኝ ብለው በተደጋጋሚ ደብዳቤ ሲልኩ አድበስብሰው ይተዋሉ፤ አሊያም ምክንያት ይፈጥራሉ:: በዚህም ንጉሡ ኢትዮጵያ የነበሩ እንግሊዞችን አሰሩ:: በኋላም ሕዝቡን ጥበብ የሚያሰለጥኑ ሙያተኞች እንደሚላክላቸው በንግሥት ቪክቶሪያ ቃል ስለተገባላቸው እስረኞቹን ፈቱ:: በኋላ ግን መልሰው አሰሯቸው::

ዐፄ ቴዎድሮስ ፈረንጆችን መልሰው ያሰሩበት ምክንያት እየሩሳሌም ደርሰው የሚመለሱም ሆነ በዚያው የሚኖሩ ሰዎች በሚልኩላቸው እና ይዘው በሚመጡላቸው ዜናዎች የተነሳ ነበር::  በዜናው መሰረት “እንግሊዞች ቴዎድሮስ ከተጣሏቸው ቱርኮች ጋር ወዳጅነት ፈጥረዋል፤  ከሱእኪን ከሰላ ድረስም የባቡር መንገድ ዘርግተዋል፤ ተባብረውም ቴዎድሮስን ለመውጋት እየዶለቱ” ነው የሚሉ ወሬዎች ይገኙበታል::  እንግሊዞችም የሚፈልጉት የተያዙባቸውን ሰዎች እንዲለቁላቸው ነው እንጂ ስለእርሶ ጉዳይ ሃሳብም የላቸውም” በማለት ጽፎላቸዋል ሲሉ ጳውሎስ ኞኞ ዐፄ ቴዎድሮስ በሚለው መጽሐፋቸው አንስተዋል:: ምጽዋ ያለው ወዳጃቸው የእውነትም የእግሊዞችን አቋም እና ሁኔታ በትክክል የነገራቸው ይመስላል::

በእንግሊዝ እና ቱርኮች መካከል ግንኙነት እንደተፈጠረ ያወቁት አፄ ቴዎድሮስ ሁሉንም ፈረንጆች አሰሯቸው::

አፄ ቴዎድሮስ ሀገር ለማቅናት ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት ፈተናው እና መሰናክሉ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ሀገር ዜጎች ይመጣ ነበር። በወቅቱ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የነበረው ኋላ ቀርነት እና ስልጣኔን ያለመናፈቅ አባዜ አፄ ቴዎድሮስን ይጎትታቸው ነበር:: እሳቸውም በግልጽ ተናግረውታል:: የመጨረሻዋን ጽዋ ለመጎንጨትም ያበቃቸው የሕዝቡ ከጎን አለመሰለፍ ነበር፤ ሕዝቡ አብሯቸው ቢሆን ኖሮ ቀዳማዊ ዓድዋን እናይ ነበር::

የእንግሊዝ መንግሥት ፈረንጆቹ ዳግም መታሰራቸውን ሲሰማ በፓርላማው ከመከረ በኋላ ለዜጎቹ ደኅንነት በመስጋት አፄ ቴዎድሮስ የጠየቁትን የእጅ ሙያተኞች እና የጦር መሳሪያዎች መልዕክተኛ ከሆነው ፍላድ ጋር ላከ:: ሆኖም እስረኞቹ ተፈተው ምጽዋ እስኪላኩ ፍላድም ሆነ የእጅ ሙያተኞች በምጽዋ ወደብ እንዲቆዩ ለፍላድ ከእንግሊዝ መንግሥት ትዕዛዝ ተሰጥቷል:: ፍላድም ምጽዋ ከደረሰ በኋላ ለንጉሡ ደብዳቤ ሰደደ:: እስረኞቹን ለቀው ወደ ምጽዋ ሲልኩለት እሱም ከእጅ ሙያተኞች ጋር ጎንደር እንደሚገባ በደብዳቤ ገለጸላቸው:: ንጉሡ ሙያተኞቹን ይዞ ምጽዋ መግባቱን ከገለጸበት ከመጀመሪያው ደብዳቤ መልስ በኋላ ለፍላድ አልጻፉለትም፤ ቅድመ ሁኔታውም አልተመቻቸውም ነበር::

ፍላድ ከንጉሡ መልስ ሲያጣ የእጅ ሙያተኞቹን ወደ እንግሊዝ መልሶ ልኮ ወደ መሀል ሀገር ደንቢያ መጥቶ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ተገናኘ:: የእጅ ሙያተኞቹ የት እንዳሉ ሲጠይቁት ከእንግሊዝ መንግሥት በታዘዘው መሠረት ወደ ሀገራቸው እንደላካቸው ገለጸ:: ከንግሥቲቷ የቃል መልዕክት እንዳለውም ተናገረ፤ ንጉሡ ምን እንደሆነ ጠየቁት::

“…በሀገርዎ ውስጥ ያለፈቃዳቸው ያስቀመጧቸውን ሰዎች በችኮላ ከሀገርዎ አስወጥተው ካላኳቸው ለወደፊት ከእኛ ጋር በወዳጅነት ለመኖር የማይቻል ነው” ብለዋል አለ:: አፄ ቴዎድሮስም ትንሽ አስበው “ስማ የወዳጅነት ምልክት እንዲያሳዩኝ ጠይቄ መልስ አልተሰጠኝም፤ መጥተው መዋጋት ከፈለጉ ይምጡ…” አሉ:: ከዚህ በኋላ ፍላድ ራሱ ታሰረ::

እንግሊዞችም በዲፕሎማሲ የጀመሩትን ጥረት ትተው የኀይል አማራጭን ለመጠቀም ወሰኑ:: በወቅቱ ዐፄ ቴዎድሮስ እንግሊዝ የደረሰችበትን የስልጣኔ ደረጃ እምብዛም አላስተዋሉም፤ በዚህም ዳግማዊ ምኒልክ ለዓድዋ ጦርነት በተዘጋጁበት መንገድ ቴዎድሮስ አልተዘጋጁም፤ ሕዝቡንም ከጎናቸው አላሰለፉም ነበር::

እንግሊዞች ፈረንጆቹን ለማስለቀቅ ስለሚወሰደው እርምጃ ሲወያዩ ኮሎኔል ሜርዌዘር የተባለው ግለሰብ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያቀረበው ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ:: ይህም “የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስ በርሱ የተከፋፈለ እና በንጉሡ ላይ የሸፈተ በመሆኑ ሀገሪቱ ብትወረር እንግሊዝን በደስታ ይቀበላል” የሚል ነበር::

የእንግሊዝ ፓርላማ ኢትዮጵያን እንዲወጋ ጀነራል ናፒር የተሰኘውን የጦር መሪ መረጠ:: ጀነራል ናፒር 13 ሺህ ተዋጊ (አራት ሺህ ብቻ ነጮች ናቸው)፣ 19 ሺህ አሽከሮች፣ 55 ሺህ በቅሎዎች እና የማጓጓዣ እንስሶች፣ ብዙ ከፍተኛ መድፎች፣ 280 መርከቦች እና ሌሎች ሎጂስቲኮችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገሰገሰ::  ለእጅ መንሻ እና ማባበያ የሚሆን በዘመኑ የኢትዮጵያ መገበያያ የነበረውን አምስት መቶ ሺህ ማርትሬዛ ገንዘብም ይዟል::

ጀነራል ናፒየር አስቀድሞ ከራስ አሊ ዘመን ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሲሰልል በቆየው እና እያንዳንዷን መውጫ እና መግቢያ በሚያውቃት በኮሎኔል ሜርዌዘር አማካኝነት ከደጃዝማች ካሳ ምርጫ (ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ) ጋር ግንኙነት ፈጠረ:: ይህ አጋጣሚ ነው ካሳ ምርጫን ቴዎድሮስ ወዳለበት የእንግሊዝን ጦር ሰተት አርገው እንዲመሩ ያደረጋቸው::

ዐፄ ቴዎድሮስ የእንግሊዝ ጦር በመጣባቸው ጊዜ ሰራዊታቸው እየከዳቸው፣ ሕዝቡም ፊቱን አዙሮባቸው ነበር:: ንጉሡ የሞት ሽረታቸውን ብቻቸውን ማለት ይቻላል የተፋልሙት፤ ከቁም ውርደት ይሻላል ሞት ብለው የሞት ጽዋቸውንም ጨለጡ:: የኢትዮጵያ አንድነት መፈረካከስ ኢትዮጵጵያን ለባእዳን በግልጽ አጋልጦ ንጉሡን ከእነ ራዕያቸው የቀበረ ሆኗል::

በመጨረሻ  የንጉሡ እስረኞች በሰላም ወደሀገራቸው ተልከዋል::

ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ከሰው በኋላ እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው፡-

“አያችሁልኝ ወይ የአንበሳውን ሞት፣

በሰው እጅ ሞሞትን ነውር አድርጎት፣

እርሳሱን እንደ ጠጅ እርሱ ሲጠጣት”

 

ሳምንቱ በታሪክ

የመጀመሪያው እግር ኳስ ክለብ

የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን  አዲስ አበባ፣ አራዳ አካባቢ ላይ ታህሳስ 28 ቀን በ1928 ዓ.ም ተመሰረተ። ዘጠኝ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በርካታ አሻራ አሳርፈው ያለፉ ታላላቅ የስፖርት ሰዎችን ማፍራቱ አይዘነጋም፡፡

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ክለብ ከመሆኑ ባለፈ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምስረታ ይቀድማል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተመሰረተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተመሰረተ ከስምንት ዓመታት በኋላ በ1936 ዓ.ም ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ መስራቾችም አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ ናቸው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪክ የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው አራራት አርመን ቡድን ላይ ነው ፤ ጨዋታው 2 ለ 0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስን የማሸነፊያ ግቦች ያስቆጠረው በአጋጣሚ የቡድኑ አባል የሆነው ይድነቃቸው ተሰማ ነበር፡፡

ይድነቃቸው በወቅቱ ቡድኑን የተቀላቀለው ጆርጅ እና አየለ ካሰባሰቡት ቡድን ውስጥ አንድ ተጫዋች የጨዋታው ቀን በመቅረቱ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪኩ የመጀመሪያውን ድል ሲያሳካ የቡድኑ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ይድነቃቸው ተሰማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አልፎ የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት እስከመሆን ደርሷል ሲል ሰዋሰው ያትታል፡፡

አስዋን

በግብጽ የአስዋን ግድብ ግንባታ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጋማል አብደል ናስር ታህሳስ 30 1952 ነበር የተጀመረው።

ፕሬዚደንቱ በናይል ወንዝ የግራ-ዳርቻ ላይ የሚገኘውን ወደሃያ ቶን የሚገመት ጥቁር-ዓለት በአሥር ቶን ዲናሚት ፍንዳታ ከስክሰውታል ይላል ናሽናል ጂኦግራፊክ ሶሳይቲ ላይ ያገኘነው መረጃ፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here