የኢትዮጵያውያኑ የገና ጨዋታ – የበረዶ ሆኪ መነሻ

0
208

በሀገራችን ዝነኛ ከሆኑት የባህል ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው የገና ጨዋታ መቼ እንደተጀመረ የሚገልጽ ትክክለኛ የጊዜ ሰሌዳና መረጃ ባይኖርም ከክርስቶስ ልደት በፊት እረኞቹ በተለይ በበጋው ወቅት ከብት እየጠበቁ ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ይጫወቱት እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ይህ ጨዋታ ከሃይማኖታዊ ክንውኖች ጋር ተያይዞ የክርስቶስ ልደትን (የገና በዓልን) ምክንያት በማድረግ እረኞች የገና ጨዋታን ከታህሣሥ ወር ጀምሮ እስከ ጥር እና ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ በሰፊው ይጫወቱት እንደነበር አባቶች ይናገራሉ:: ታዲያ ይህ ጨዋታ አዝናኝ እና ተወዳጅ ከመሆኑም ባሻገር ማህበራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። በጨዋታው ወቅት ዘር፣ የሀብት ደረጃ፣ የሥራ ኃላፊነት እና ሌሎች ልዩነቶች ቦታ የላቸውም። “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እንደሚባለው፤ አሽከር ከጌታው፣ ሎሌ ከንጉሡ ጋር እኩል ተጋፍቶ የሚጫወትበት፤ ማንም በማንም ላይ ሥልጣን የማይዝበት የነፃነት መድረክ ሆኖ ለዘመናት አገልግሏል።

በኢትዮጵያ የገና ስፖርት ጨዋታ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ረቂቅ ደንብ ወጥቶለት ውድድሩ እየተደረገ ይገኛል። በስፖርታዊ ውድድር የተካተተው ዘመናዊው የገና ጨዋታ ከመጫዎቻ ሜዳው ቅርጽ ጀምሮ በዳኞች ብዛት እንዲሁም በሌሎች መስፈርቶች ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋር ተቀራራቢነት አለው። በአጠቃላይም ሰባት ያህል ሕግ እና ደንቦች ተዘጋጅተውለታል። በገና ጨዋታ ላይ ተጠባባቂዎቹን ጨምሮ እያንዳንዱ ቡድን አስራ አምስት ተጨዋቾች ሊኖሩት ይገባል። ወደ ሜዳ የሚገቡት ግን ዐስሩ ብቻ ይሆናሉ፤ ቀሪዎቹ አምስቱ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ይቀመጣሉ። ጨዋታውን የሚመራ የመሐል ዳኛ እና ረዳት ዳኞችም ይኖሩታል። የገና ጨዋታን ለመጫወት “ሩር” እየተባለች የምትጠራ ድቡልቡል መጫዎቻ ኳስ ታስፈልጋለች። ይህች ኳስ ክብደቷ እስከ አምስት መቶ ግራም የሚመዝን ሲሆን በጥንቱ ጊዜ ከእንጨት ወይም በቆዳ ተጠቅልሎ ከሚሰራ ጨርቅ ይዘጋጅ ነበር፤ አሁን ላይ በዘመናዊ መልኩ ከፕላስቲክም ይዘጋጃል። ሩርን ለመምታት እና ወደ ተቃራኒ ቡድን ለማስገባት ልክ እንደ ማንኪያ ቅርጽ ያለው ከታች በኩል ቆልማማ የሆነ እና ገና በመባል የሚጠራ ከአንድ ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው ዱላም ያስፈልጋል። ይህ ዱላ በተለምዶ እንደ ወይራ እና ዶቅማ ካሉ ጠንካራ የእንጨት ዝርያዎች ይዘጋጃል።

የገና ዱላው ለሁሉም ተሳታፊዎች በእኩል ቁመት የሚዘጋጅ ሲሆን ጨዋታው በአጠቃላይ ለስድሳ ደቂቃ ይከናወናል። በጨዋታው አጋማሽ ላይ ተሳታፊዎቹ ለዐስር ደቂቃ እረፍት የሚያደርጉ ይሆናል። ጨዋታው የፍፃሜ ወይም የደረጃ ከሆነ እና ቡድኖቹ ካልተሸናነፉ ተጨማሪ ደቂቃ እና ቅጣት ምት ይሰጣል። ስፖርቱ ልክ እንደ እግር ኳስ ስፖርት በዚህ መልኩ በሕግ እና ስርዓት ይመራል። በ1990 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ ዜጎች በባህላዊ ስፖርት መሳተፍ እንዳለባቸው የሚደነግግ ቢሆንም ዘርፉ ከመንግሥት እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ግን በቂ እንዳልሆነ ይነገራል። የገጠሩ ማሕበረሰብ ክፍል የገና ስፖርት ጨዋታ ዋነኛ ባለቤት እና ጠባቂ ቢሆንም በስፖርቱ ግን ተጠቃሚ አለመሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው። የስፖርት ምክር ቤት በየዓመቱ የስፖርት ሀብት ገንዘብ ሲሰበሰብ ከገጠሩ ማህበረሰብ  ብዙ ገንዘብ ይሰባሰብ እንደነበር ከዚህ በፊት በነበሩት የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤዎች ይገለፅ ነበር። ታዲያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለስፖርቱ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለሚያደርገው የገጠሩ ማህበረሰብ ስልጠና በመስጠት እና ግንዛቤ በመፍጠር በዘርፉ ማሳተፍ ይጠይቃል።

የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነው የገና ስፖርት በቂ ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑ አያጠያይቅም። በየዓመቱ በሚደረጉ የባህል ስፖርቶች ውድድር ምክንያት የገና ስፖርት ትንሽ መነቃቀት ቢያሳይም በተፈለገው ልክ ግን እያደገ አይደለም። ስፖርቱን በተሻለ ለማሳደግ እና ለማስተዋወቅ በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ብዙ ሥራዎች መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያ በዓለም እና አህጉር አቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት የባህል ስፖርቷን ያስተዋወቀችበት እና የተሳተፈችበት ጊዜ እንደ ነበር ታሪክ ያስረዳል። ታዲያ የገና ስፖርትን ለማሳደግም አሁንም ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል እና ስፖርት በዓሎችን በማዘጋጀት ስፖርቱን የማስተዋወቅ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል።

በመላው ጨዋታዎች፣ በትምህርት ቤት ውድድር ተካቶ እንዲካሄድ መደረጉ ስፖርቱን ከማሳደግ አንፃር መልካም ጅምር ቢሆንም አሁንም ግን ብዙ ሥራ ይጠይቃል። የገና ስፖርት የአንድን አካባቢ ባህልና ትውፊት ወደ ሌላው አካባቢ ለማወራረስ እና ያልተበረዘውን የኢትዮጵያውያንን ማንነት ለማንፀባረቅ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል፤ ይህ ደግሞ የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። ለስፖርቱ መወዳደሪያ የሚሆን የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት እና የስፖርት ቁሳቁስ እጥረትም በስፋት ይስተዋላል። ይህንንም ችግር የሚመለከታችው አካለት መቅረፍ ለነገ የማይተው ተግባር ነው።

ማሕበረሰቡ እና በየደረጃው የሚገኙ የስፖርት ባለሙያዎች የባህል ስፖርቶችን ልክ እንደ ዘመናዊ ስፖርቶች እኩል ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። በየአካባቢው የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ስፖርቱን ለማሳደግ መስራት ይጠበቅባቸዋል። የገና ስፖርት በስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ ከታች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ቢሰራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችንን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ብቁ ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል። ይህን ለማደረግ የሚቻለው ግን ስፖርቱን በተሻለ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ብቁ እና የሰለጠኑ ዳኞች፣ አሰልጣኞች እና ባለሙያዎች ሲኖሩን መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የገና ስፖርት እንደ ሌሎቹ የስፖርት ዓይነቶች የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትን በማጠናከር የአካባቢውን ባህል እና ወግ በማስተዋወቅ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።

በተለይም በዘመናዊ ስፖርቶች የሚታየው የሥነ ምግባር እና ሥነ ስርዓት ግድፈት በገና ስፖርት ጨዋታ እንደሌለ መረጃዎች ያመለክታሉ። ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር የሚጠይቅ እና አልፎ አልፎም አካላዊ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም በጨዋታ ወቅት ተጫዋች ቢጎዳ መክሰስ፣ መካሰስም የተከለከለ ነው። “የገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” ተብሎ እንደሚተረተው ሁሉ በጨዋታው ሜዳ ላይ የሚደርስ ጉዳት እንደ “የገና ቁስል” ተቆጥሮ በይቅርታ ይታለፋል። ማን እንደጎዳውም ማረጋገጥ አይቻልም፤ ተሸናፊው ቡድንም ውጤቱን በፀጋ ይቀበላል። ይህም ለሌሎቹም ስፖርቶች አስተማሪ መሆኑ በብዙዎቹ ዘንድ ተመስክሮለታል።

የገና ስፖርት ጨዋታ በይበልጥ መዘውተር የጀመረው በተለይ በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይገለፃል። በወቅቱ ብዙ ዓይነት ውድድር ይደረግበት ነበር፤ ለአብነት ቁርቁዝ፣ ሙጭ፣ ቀልቦ መለጋት እና አፍሶ መለጋት የመሳሰሉት ይገኙበታል:: ከገና ጨዋታቸው በኋላ ጐልማሶች በምሽት በየቤቱ በመዟዟር ይጨፍሩ እንደነበር ተነግሯል::

የገና ጨዋታ ዛሬ በዓለም ዘንድ በጣም ተፈላጊ ከመሆን ደረጃ አልፎ ተርፎ በኦሎምፒክ ከሚደረጉት ውድድሮች አንዱ ለመሆን በቅቷል:: ባህላዊው የገና ጨዋታ ለዘመናዊ ስፖርትም መነሻ እንደ ሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያውያኑን የገና ስፖርት ካናዳውያን በዘመናዊ መንገድ በማሻሻል “የበረዶ ሆኪ” (Ice Hockey) በሚል ስያሜ እ.አ.አ 1875 ገደማ በሀገራቸው አስተዋውቀውታል። የበረዶ ሆኪ ስፖርት ከገና ስፖርት ጋር ተመሳሳይ ነው። ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በካናዳ ክለብ ተቋቁሞ የሊግ ጨዋታዎች መደረግ እንደጀመረ ብሪታኒካ ዶት ኮም ያስረዳል። ከዛ በኋላም በእንግሊዝ፣ በአየርላንድ እና በሌሎችም የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ስፖርቱ ሊስፋፋ ችሏል። እ.አ.አ ከ1920 ጀምሮ ስፖርቱ በኦሎምፒክ ተካቶ እየተካሄደ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በፓራለምፒክም ውድድር በመካተቱ ተወዳጅ ስፖርት ለመሆን በቅቷል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ይህንን ጥንታዊ የገና ስፖርትን በማዘመን እና በመጠበቅ ለዓለም ማስተዋወቅ ይጠበቅባታል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here