ዓለማችን በ2025

0
157

በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያን 2025 ጦርነቶችና ግጭቶች በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች ቀጥለዋል፤ በበርካታ ሀገራት የሰው ሕይወት እንደ ቅጠል ረግፏል:: የኢኮኖሚ ጫና (የእቃዎች እና የሸቀጦች ዋጋ መጨመር፣ ዕዳ) በርካታ ሀገራትን የፈተነበት ዓመት ነበር:: ቴክኖሎጂ በተለይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) በፍጥነት ተሻሽሏል፤ ሥራና ሕይወትንም ቀይሯል፤ ውጣ ውረድንም አቅልሏል:: የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ሆኗል::

ዓለማችን ካሳለፈቻቸው አንኳር ነገሮች መካከልም አዳዲስ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን መፈጠራቸው ተጠቃሽ ናቸው:: ለአብነትም የካምቦዲያ እና የታይላንድ እንዲሁም የሕንድ እና የፓኪስታን ግጭቶች፣ በአፍሪካ የተደረጉ መፈንቅለ መንግሥቶች ተጠቃሽ ናቸው::

2025 በአፍሪካ፡- እ.አ.አ. በ 2025 አፍሪካ ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ገጥሟታል:: አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው ሁለት የተሳካ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት (ማዳጋስካር፣ ጊኒ-ቢሳው)   ተካሂዶባታል:: እንዲሁም ቀጣይነት ያለው አለመረጋጋት፣ ከከፋ የፀጥታ ቀውሶች ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣው ሽብርተኝነት እና ግጭቶች ሱዳንን፣ የሳህል ሀገራትን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ቀውስ  ውስጥ አስገብቷቸዋል::

የካምቦዲያ እና የታይላንድ ግጭት፡- ሁለቱ ሀገራት የተጋጩት በድንበር ወሰን እና  ጥንታዊ “ፕራሳት ታ ሙኤን ቶም” በተባለው ቤተ መቅደስ የባለቤትነት ጥያቄ ምክንያት ነው::  ሁለቱ ሀገራት በመጀመሪያው ደም አፋሳሽ ግጭታቸው በርካታ ሰዎች ሕይዎታቸው አልፏል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ተፈናቅለዋል:: ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ጣልቃ ገብተው ጦርነቱ ካልቆመ በስተቀር ከካምቦዲያ እና ከታይላንድ ጋር የንግድ ድርድርን እንደሚያቆሙ ዝተው ነበር:: ከዚያም ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በመስማማት በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ኳላላምፑር ውስጥ መደበኛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል::

ሕንድ እና ፓኪስታን፡- በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል ለዘመናት  የነበረው የካሽሚር ግዛት የይገባኛል ጥያቄ ውጥረት ፈንድቶ አምስት አሸባሪዎች በሕንድ በሚተዳደረው ጃሙ እና ካሽሚር ውስጥ በፓሃልጋም አቅራቢያ ሃያ ስድስት ሰዎችን ከገደሉ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጦር ተማዘው ነበር::   ከሦስት ቀናት ውጊያ በኋላም ተኩስ አቁም ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል:: ነገር ግን በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል ያለው መሠረታዊ ጥላቻ አሁንም እንደቀጠለ ነው::

የሱዳን ከባድ የርስበርስ ጦርነት፡- “በምድር ላይ ገሃነም” የሚለው ቃል ለሦስት ዓመታት ያህል የዘለቀውን የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምርጥ መገለጫ ሊሆን ይችላል:: በማለት አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የጦርነቱን አስከፊነት ለመግለጽ ሞክረዋል:: በጄኔራል  አብደል ፋታህ ኣል-ቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦር ኃይሎች (SAF) እና በመሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ  በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) መካከል የሚደረገው ውጊያ በ2025 እንደቀጠለ ነው::

ግሎባል ኮንፍሊክት ትራከር ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ጦርነቱ ከጀመረበት ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ እስከ 400ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በጦርነቱ ሞተዋል:: ከአስራ ሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል:: በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ረሃብ አጋጥሟል:: የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎትም ከፍተኛ ሆኗል:: የርስበርስ ጦርነቱ እንዲቆም የሚያድረግ ተስፋ አሁንም ደካማ ነው::

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፡-  በሩሲያ እና ዩክሬን እየተደረገ የሚገኘው  ጦርነት  አራተኛ ዓመቱን በቅርቡ ያስቆጥራል:: ሩሲያ የሚሳኤል እና የድሮን ዘመቻዎቿን አጠናክራለች:: የዩክሬን ከተሞችንም ደጋግማ ደብድባለች:: በዚህም የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ዋና ዋና መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል:: ዩክሬንም በሩሲያ ላይ የአጸፋ በትሯን እያሳረፈች ነው::

የፖለቲካ ባለሙያዎች ሩሲያ እና ዩክሬን ውጊያቸውን ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥሉ ወይም እንደሚያቆሙ መገመት አልቻሉም::  ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኪየቭ ለማሸነፍ የሚያስፈልጓት  ካርዶች እንደሌሏት አጥብቀው ይናገራሉ:: ሆኖም አሁንም ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው::

የእስራኤል እና የኢራን  ጦርነት፡- እስራኤል እና  ኢራን ከእጅ አዙር ጦርነት ወጥተው በቀጥታ የተፋለሙት በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2025 ነበር::

የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ምክንያት የሆነው ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀው የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ማሳደግ፣ ፀረ እስራኤል የሚያራምዱ ቡድኖችን መደገፏ እና የኢራን መንግሥት በእስራኤል ሕልውና ላይ ያለው መሰረታዊ የርዕዮተ ዓለም ጥላቻ ባለመቆሙ  እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

እስራኤል በኢራን በኑክሌር እና የባለስቲክ ሚሳኤል ተቋማት፣ በወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ድብደባ ፈጽማለች:: የአየር ድብደባዎችን ማካሄድ እና  የፖለቲከኞችን፣ የጦር መሪዎቿን እና የኑክሌር ሳይንቲስቶቿንም  ገድላለች::

ኢራንም በእስራኤል ላይ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን በመተኮስ አጸፋ ሰጥታለች::  ሰኔ 22 /2025 የአሜሪካ ለእስራኤል በመወገን በቢ2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቿ እና በቶማሃውክ ሚሳኤሎቿ የኢራንን የኑክሌር ተቋማት ደብድባለች:: ኢራን በምላሹ  በዶሃ የሚገኘውን የአሜሪካ የጦር ሰፈር በሚሳኤል መደብደቧ የሚታወስ ነው:: ይህ የኢራን ጥቃትም እስራኤል እና ኢራን ሰኔ 24 2025 ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል::

ትራምፕ እና አዲሱ  የአሜሪካ ሕጎች፡- ሌላው በ2025 ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ አዳዲስ ውሳኔዎች እና ሕጎች ናቸው:: ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት በትረ ሥልጣን የጨበጡት የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሸቀጦችን ወደ አሜሪካ በሚያስገቡ ሀገሮች ላይ ከ10 በመቶ  እስከ 50 በመቶ የሚደርሱ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ታሪፎችን መጣላቸው የዓለምን ኢኮኖሚ ያናጋ እና ሀገራትንም ድንጋጤ ውስጥ የጨመረ ነበር::

ቢቢሲ እንደዘገበው ትራምፕ የጣሏቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ቻይናን ጨምሮ በተለይም ታዳጊ ሀገራትን ከመጉዳት ባለፈ የአሜሪካን ሸማቾች እና አምራቾችንም ኪስ አራቁቷል::

ሌላው አዲስ ነገር የትራምፕ አስተዳደር የዳይቨርሲቲ ቪዛ (ዲቪ) ሎተሪ ፕሮግራምን በታኀሳስ 2025 ማገዱ ነው:: እገዳው የወጣው እ.አ.አ በ2017 ዲቪ ሎተሪ ደርሶት ወደ አሜሪካ የገባ  የፖርቹጋላዊው ዜጋ ግሪን ካርድ ባገኘበት ብራውን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተኩስ ልውውጥ ማድረጉን ተከትሎ ነበር::

በአየር ንብረት ምክንያት የደረሱ ጉዳቶች፡- ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ ከደረሱ ከፍተኛ አደጋዎች መካከል አውሎ ንፋስ፣ ጎርፍ እና ሰደድ እሳት ተጠቃሾች ናቸው:: ወርልድ ቪዥን ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው  በእነዚህ አደጋዎች ከ120 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንሹራንስ ኪሳራ ደርሷል:: አልጀዚራ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ እ.አ.አ. በ2025 የተፈጥሮ አደጋዎች 220 ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አስከትለዋል::

በደቡብ ምሥራቅ እስያ በተከሰተው የበልግ አውሎ ንፋስ፣ የካሊፎርኒያ ሰደድ እሳት በርካታ ውድመት አድርሰዋል:: በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉበት የቻይና ከባድ ጎርፍ በሦስተኛ ደረጃ ሞትን ጨምሮ በንብረት ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ ነው::

አዎንታዊ ኹነቶች፡- በ2025 ከተከናወኑ አወንታዊ ክንውኖች መካከልም አሜሪካ የጋዛ የሰላም ዕቅድን ማመቻቸቷ አንዱ መሆኑን ፖዘቲቭ ኒውስ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል:: ለሁለት ዓመታት ጭካኔ የተሞላበት ውጊያ ከተደረገ በኋላ እስራኤል እና ሃማስ  በጥቅምት ወር የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል::

ሌላው በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዘመን በአዎንታዊነት የተገለጸው ሕዳር ላይ  በብራዚል ቤሌም ከተማ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የበለፀጉ ሀገራት ድሃ ሀገራትን ከከባድ የአየር ጠባይ ተጽእኖዎች ጋር እንዲላመዱ ለመርዳት ያለውን የፋይናንስ መጠን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ መስማማታቸው ነው::

እንዲሁም 79 ሀገሮች ዓለም አቀፍ የውቅያኖስ ስምምነትን አጽድቀዋል:: ስምምነቱ መንግሥታት ከብሔራዊ ወሰኖቻቸው ውጭ ያሉትን የውሃ አካላትን ለመጠበቅ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ይሰጣቸዋል ሲል ዘጋርዲያን ዘግቧል::

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ትልቁ የካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) አመንጪዋ ቻይናም  በ2035  የንፋስና የፀሐይ ኃይል አቅሟን ስድስት እጥፍ ለማሳደግ ቃል ገብታለች::

በአፍሪካም አንዳንድ ሴክተሮች እንደ ንፁህ ኢነርጂ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የኢትዮጵያዉ የሕዳሴ ግድብ የአህጉሪቱን  እድገት እና ተስፋ ያሳዩ ልማቶች ነበሩ::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here