የወባ በሽታ በአማራ ክልል

0
148

“ለወባ የነበረኝ አመለካከት ዝቅተኛ ስለነበረ በበሽታው ላላመያዝ መደረግ የነበረባቸውን  ጥንቃቄዎች ችላ በማለቴ( አጎበር ስለማይወድ አይጠቀምም ነበር) በአንድ አመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ለወባ በሽታ ተዳርጊያለሁ”ያለን አንዱ የሥራ ባልደረባችን ነው፡፡ ከሱም አልፎ የሁለት ዓመት እድሜ ያላት ልጁም በበሽታው ተይዛ ነበር፡፡ አሁን ግን በኬሚካል የተነከረ አጎበር መላው ቤተሰቡ እንዲጠቀም አድርጓል፡፡ ይህንን እንደማሳያ አነሳንላችሁ እንጂ  በአማራ ክልል የወባ በሽታ የበርካቶች ችግር ነው፡፡ ከአንድ የቤተሰብ አባላት መካከልም ሁለት ሦስት ሰው በአንድ ጊዜ ሊታመም ይችላል፡፡ በዚህም የሚያስከትለው የጤና እና የኢኮኖሚ ቀውስ ከባድ ነው፡፡

የወባ በሽታ ስርጭት ዓለምአቀፋዊ ገጽታ ያለው ቢሆንም በድሃ ሀገራት ችግሩ የከፋ ነው፡፡ ለአብነትም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በሽታው በገዳይነቱ ከቀዳሚዎቹ መካከል እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡ በአፍሪካም በ2024 (እ.አ.አ) 265 ሚሊዮን ሰዎች ለወባ በሽታ ተዳርገው ነበር፡፡ ከዚህም 579ሺህ ሕይዎታቸው አልፏል፡፡

የወባ በሽታ ምንነት እና መንስኤ

ወባ የሚከሰተው በዓይን በማይታይ ፕሮቶዝዋ በሚባል የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተኅዋሲያን ምክንያት  ነው፡፡ በጥገኛ ተህዋሲያኑ በተያዘች “አኖፊለስ ሞስኪቶ” በምትባል ሴት የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ንክሻ አማካኝነትም ወደ ሰዎች ይተላለፋል፡፡ ጥገኛ ተውሳኩም በጉበት ውስጥ ተባዝቶ ወደ ደም ውስጥ ይሰራጫል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የወባ ትንኟ የምትነክሰው በምሽት እና ጠዋት ሊነጋ ሲል ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ሰዎችን ሊበክሉ የሚችሉ አምስት ዓይነቶች የፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች አሉ፡፡ እነሱም ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም፣ ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ፣ ፕላዝሞዲየም ማላሪዬ፣ ፕላዝሞዲየም ኦቫሊ እና ፕላዝሞዲየም ኖሊስ ይባላሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም (Falciparum) እና ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ (Vivax) በጣም የተለመዱ ሲሆኑ ፋልሲፓረም የተባለው ደግሞ ከባድ ሕመምን በማስከተል በገዳይነቱ ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙት ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ እና ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም ናቸው፡፡ 56 በመቶ የፋልሲፓረም፣ 39 በመቶ የቫይቫክስ ዝርያዎች እና ሁለቱም ዝርያዎች የሚገኝባቸው ደግሞ አራት በመቶ ናቸው፡፡

የወባ በሽታ ምልክቶች

ብዙውን ጊዜ በወባ የተያዘ ሰው  የጉንፋን ሕመም  የሚመስሉ  ምልክቶች የሚከሰቱበት ሲሆን ከዚያም እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት (ማንቀጥቀጥ)፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም፣  የመተንፈስ ችግር፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ፣ ተቅማጥ፣ የቆዳ ቢጫ ወይም የዓይን ቀለም ነጭ መሆን ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው፡፡ ከዚያም አለፍ ሲልም ራስን እስከ መሳት የደረሰ ከባድ የሕመም ምልክት ሊከሰት ይችላል፡፡

በፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም ተኅዋስ የተነከሰ ሰው ምልክቶቹን ማሳየት የሚጀምረው ከሰባት እስከ 14 ባሉት ቀናት ነው፡፡  በፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ ተኅዋስ በተያዘች ትንኝ የተነከሰ ሰው ደግሞ ከ12 እስከ 18 ቀን ድረስ ምልክቶቹ ሳይታዩ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ማሕበራዊ ድረገጽ ላይ ያገኘነው  ማብራሪያ እንደሚያመላክተው የወባ በሽታ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ሲሆን  በተለይም ጨቅላ ሕጻናትን፣ ነፍሰ ጡሮችን፣ አረጋዊያንን እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች ላይ ሲከሰት ሕመሙ ይበረታል፤ ለሞትም ያበቃል፡፡ ሁሉም የወባ ተኅዋሲያን  ተመሳሳይ ምልክቶችን የሚያመጡ እና አፋጣኝ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በምልክቶች ብቻ በየትኛው የወባ አይነት እንደተያዙ ማወቅ ስለማይቻል የወባ በሽታን ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡

በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለአሚኮ እንደገለጹት  በክልሉ የወባ ስርጭት ከባለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቀንሷል፡፡ ከሐምሌ 2017 ዓ.ም እስከ ተኀሳስ 2018 አጋማሽ ድረስ 2ሚሊዮን 563ሺህ 863 ሰዎች ተመርምረው 836ሺህ 866 የሚሆኑት ወባ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ34 በመቶ (በ440ሺህ ሕሙማን) ቀንሷል፡፡

አቶ ዳምጤ እንዳሉት የወባ በሽታ አሁናዊ ሁኔታ ከ2017 ዓ.ም ጋር ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ከ2016፣ 2015፣ እና 2014 ተመሳሳይ ወቅቶች ጋር ሲነጻጸር ግን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡  በአሁኑ ወቅት አዊ ዞን በወባ ስርጭት ቀዳሚ ሲሆን በዞኑ 169ሺህ 339 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡ ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ  ሰቲት ሁመራ በቅደም ተከተል የወባ ስርጭት የተስፋፋባቸው የክልሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ አቶ ዳምጤ እንደገለጹት ምዕራባዊው የክልልሉ ክፍሎች 91 በመቶ የወባ ስርጭት አላቸው፡፡ 68 ወረዳዎችም አጠቃላይ የክልሉን የወባ ጫና ሲወስዱ እንደ ደራ ወረዳ፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ ጓንጓ ወረዳ እና የቻግኒ ከተማም የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክር በላይ በዛብህ መስከረም ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት በአንድ ሳምንት ብቻ እስከ 80 ሺህ የወባ በሽታ እንዳለባቸው የሚጠረጠሩ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርት ይደረግ እንደነበር መስከረም ላይ ባወጣነው የጤና ዘገባችን መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

እንደ አማራ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ የወባ በሽታ ስርጭት የሚጨምርባቸው ሁለት ወቅቶች ሲሆኑ እነሱም የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታኀሳስ እና የበልግ ዝናብን ተከትሎ ግንቦት እና ሰኔ ላይ ነው፡፡ ወጥነት የሌለው ዝናብ መኖር፣ የሕብረተሰቡ በጸረ ወባ ኬሚካል የተነከረ የአልጋ አጎበር የመጠቀም ፍላጎቱ ዝቅተኛ መሆን፣ ክረምቱን ተከትሎ የትንኝ መራቢያ ስፍራዎች (ውሃ የሚያቆሩ ) መበራከት ለወባ በሽታ መሰራጨት እና መዛመት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፡፡

የወባ በሽታ እና ሕክምናው

የወባ በሽታ በቀላሉ መዳን የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም እላይ የተጠቀሱት የወባ ምልክቶች የተሰማዉ ሰዉ በአፋጣኝ በአቅራቢያዉ ወደ ሚገኝ የሕክምና ተቋማት ሂዶ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ እና መታከም ያስፈልገዋል፡፡ የወባ በሽታ በጊዜው ሳይበረታ ከታከመ በቀላሉ ይድናል፡፡ ነግር ግን ሕክምና ሳያገኙ ብዙ ጊዜ ከወሰደ ለሞት ሊያበቃ ይችላል፡፡ በዚህም እ.አ.አ በ2024 ብቻ በዓለም ላይ 610ሺህ ሰዎች በወባ በሽታ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በአማራ ክልልም ከሐምሌ 2018 እስከ ተኀሳስ 2018 ድረስ 19 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ልብ ይሏል፡፡

አቶ ዳምጤ እንደሚሉት የወባ በሽታ መድኃኒትን መውሰድ ያለበት በምርመራ ተረጋግጦ በሽታው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ያለ ሀኪም ፈቃድ በራስ ተነሳሽነት መውሰድም ሆነ  ተመርምሮ በሽታዉ ላልተገኘበት ሰዉ የጤና ባለሙያም ቢሆን  መድኃኒትን ማዘዝ ከሕክምናው ስነ-ምግባር ውጭ መሆንና ለሌላ የጤና እክል የሚዳርግ ነው፡፡

ወባን ለመከላከል ምንተሠራ? ምንሥ መሠራት አለበት?

ወባን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት በ18 ወረዳዎች በሚገኙ 230 ቀበሌዎች  ተከናውኗል፡፡ በዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ምንም እንኳ ክልሉ የሚያስፈልገው አራት ሚሊዮን አጎበር ቢሆንም  ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአጎበር ስርጭት ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው 26 ወረዳዎች እየተከፋፈለ ይገኛል፡፡ ቀጣይ ባሉ ጊዜያትም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን አጎበር ወደ ክልሉ ይገባል ተብሎ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡ እስካሁንም ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብአቶች እና መድሃኒቶች ያለምንም እንቅፋት እየተከናወኑ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡

አስተባባሪው እንደገለጹት የወባ በሽታን ለመቆጣጠር ጤና ጣቢያዎች የሚመሩት “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባን በሽታ ይገታሉ” በሚል ሁሌም አርብ አርብ የወባ ጫና ያለባቸው ቀበሌዎች ማሕበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የወባ በሽታን ለመከላከል ሚያስችሉ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡   የጤና ልማት እና የጸረ ወባ ማሕበር ጋር በመተባበርም በ34 ወረዳዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎችን ያሳተፈ ማሕበረሰብ ተኮር ወባን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

አያይዘውም የበሽታውን አስተላላፊ የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢ ማጽዳት፣ ኬሚካል የተነከረ የአልጋ አጎበር በአግባቡ መጠቀም፣ የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት የተከናወነባቸውን ቤቶች ግድግዳቸውን ቀለምም ሆነ እበት አለመቀባት፣  የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢን በተለይም ረግረጋማ ቦታዎችን ማስወገድ፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስ፣ ጉድጓዶችን ማዳፈን  ውጤታማ የመከላከል ስልቶች በመሆናቸው ሁሉም አካል በየአካባቢው ሊተገብረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ጤና አዳም

*ወባ  በእርግዝና ወይም በወሊድ እንዲሁም በደም ልገሳ ወቅት ወደ ሌላ ሰው ሊሰራጭ ይችላል፡፡

*47 ሀገሮች በዓለም ጤና ድርጅት መሥፈርት መሠረት ከወባ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

 

* እ.አ.አ በ2024  ወደ 282 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘው ነበር፤ 610ሺህ  ሰዎችም  ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

* በየዓመቱ ወደ 290 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በወባ ይያዛሉ፣ ከ400ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በዚህ በሽታ ይሞታሉ፡፡

*አፍሪካ የዓለማችን ትልቋ የወባ በሽታ ስርጭት ያለባት አህጉር ናት፡፡

*ወባ መከላከል እና ሊታከም የሚችል ነው፡፡

 

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት::

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here