በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት ስብራት በአግባቡ ሳያገግም ለዳግም ግጭት የተጋለጠው አማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች ክፉኛ ተጎድቷል፣ ሁለት ዓመታትን የተሻገረው በክልሉ ውስጥ የተከሰተው ግጭት ደግሞ ክልሉን ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሎበታል።
ግጭቱን ተከትሎ የተከሰቱ ከዕሴት ያደነገጡ ድርጊቶች እየተስፋፉ ነው። ለአብነትም ወጥቶ ለመግባት ከመቸገር ባለፈ እገታ ብዙዎችን አንገት አስደፍቷል። ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ በማራቅ የክልሉን አለፍ ሲልም የኢትዮጵያን ነገ ጥያቄ ውስጥ እንሲገባ እያደረገው ይገኛል።
የተራራቀው ወዳጅ ዳግም ያለ ስጋት እንዲገናኝ፤ እገታ፣ ዝርፊያ እና ተራ ውንብድና ወጥቶ የመግባት ሥጋት እንዳይሆኑ፣ ሕጻናት የነገ ሕይወታቸውን በዕውቀት እንዲሠሩ ሕዝብ እየተማጸነ ነው። አርሶ አደሩም በስጋት ውስጥ ሆኖም ያዘመረውን ሰብሉን በተሻለ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ “ሰላም ሆይ የት ነህ”? እያለ ነው። በየቤቱ የገባው ሀዘን ከዚህ በላይ እንዳይሆን ታጣቂ ኃይሉ ሰላምን እንዲያስቀድም፣ መንግሥትም የጀመረውን ሰላምን የማስፈን ጥረት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ሕዝቡ በየመድረኩ እየጠየቀ ነው።
“የሰላም እጦት የሚያስከፍለውን ዋጋ ባለፉት ሁለት ዓመታትን በተሻገሩ ጊዜያት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት በቃን” የሚሉ ድምጾች ደግሞ ከሰሞኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች በስፋት ተስተጋብተዋል።
በተመሳሳይ የክልሉ ምክር በለት አባላትም አሉ የሚባሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ክልሉን ወደተሟላ ሰላም መመለስ እንደሚገባ ጠይቀዋል። ምክር ቤቱ 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከሰሞኑ አካሂዷል። የክልሉን ሰላም የተመለከተው ደግሞ አንደኛው የጉባዔው ዐቢይ ጉዳይ ነበር።
ሐሳባቸውን ከሰጡ የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ቀለመወርቅ መንግሥቴ ይገኙበታል። የሰላም እጦቱ በፍጥነት መፍትሔ ካላገኘ የክልሉ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ማሳያዎችን እያነሱ አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም በክልሉ የስደት ልማድ የሌለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አሁን ስደት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን አብነት አንስተዋል። የችግሩ ዋነኛ ሰለባዎች ደግሞ በዕሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች መሆናቸው ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት።
በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ደግሞ አምራች መሆናቸውን በማንሳት “እነዚህ ወጣቶች እየተሰደዱ ያሉት ስለ ቸገራቸው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ይህ በዚህ ከቀጠለም አደገኛ ነው” ብለዋል።
“ክልሉን ለቆ እየወጣ ያለው አምራች የሆነው ኃይል ነው” ያሉት የምክር ቤት አባሉ “ደጀን ከተማ ላይ ለቀናት በነበረን ቆይታ በተመለከትነው በጣም ደንግጠናል” ሲሉ አደገኛነቱን ተናግረዋል።
ግጭቱ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች 36 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አንስዋል። በሁሉም የክፍል ደረጃ መመዝገብ የተቻለውም 58 ነጥብ ሁለት በመቶ ብቻ ነው ብለዋል።
ድርድር እና ውይይት ክልሉን ከገጠመው የቀውስ አዙሪት የሚያዋጡት ዋና መፍትሔዎች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የምክር ቤት አባል መሠረት ደሳለኝ ናቸው። አማራቮቹም ሁሉንም አሸናፊ እና ሕዝብንም ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል። ለሰላም አማራጩ ፈጥኖ ምላሽ አለመስጠት ደግሞ ለከፋ ውድቀት እንደሚዳርግ የሀገራት ተሞክሮ ዋቢ አድርገው አንስተዋል።
በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም እጦትም የሥራ እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን እና ለኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል። ግጭቱ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ፣ በተለይ ደግሞ ሴቶችን እና ሕጻናትን ለከፋ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም ማንኛውም አካል አሉኝ የሚላቸውን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍታትን እንዲያስቀድም ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ የጸጥታ ችግሩ አዳዲስ የልማት ሥራዎች እንዳይሠሩ፣ የተሠሩትም እንዲወድሙ ማድረጉን የምክር ቤት አባላት አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝብ የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ የተሠራው ሥራ እና የታጠቁ ወገኖች የሰላም አማራጭን መከተላቸው በቀጣይ ክልሉን ከቀውስ ለማውጣት ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑንም ተናግረዋል፤ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም የጀመሩትን አባታዊ ምክር አጠናክረው እንዲቀጥሉ የምክር ቤት አባላቱ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ማንኛውም የሐሳብ ልዩነት በጦርነት መፍትሔ አግኝቶ እንደማያውቅ የዓለም ሀገራት ተሞክሮን በማሳያነት አንስተዋል። ስልጣንን በኃይል ለመያዝ መፈለግ ከፍላጎት ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ በክልሉ ባለፉት የሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።
“የሰላምን አማራጭ አለመቀበል እና ጦርነትን መምረጥ ለክልሉ ሕዝብ ያተረፈው ወደ ኋላ መቅረትን፣ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን ነው። እስካሁን የተደረጉ ውይይቶች እያረጋገጡ ያሉትም ሕዝቡ ግጭቶች እየፈጠሩት ያለውን ጫና መቋቋም የሚችልበት አቅም ማጣቱን ነው” ብለዋል።
ዋና አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያደረገ ያለው ሕዝብ በጦርነት እየተሰቃየ በመሆኑ፣ ለዓመታት የመማር መብታቸውን የተነፈጉ ሕጻናትን ሕልም ለማስቀጠል፣ በሰቆቃ እና በስጋት ኑሮን እየገፋ ያለው ሕዝብ ንጹህ ጥያቄ በመሆኑ፣ በጉሊት ገበያ ልጇን ለመመገብ ደፋ ቀና የምትለው እናት ጩኸት ምላሽ ለመስጠት ነው።
በመሆኑም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ሰላማዊ የትግል አማራጭን እንዲከተሉና እንዲቀበሉ ጠይቀዋል። የሕዝቡን ድምጽ ማጤን፣ ፍላጎቱን መረዳት እና ማክበር የሰላማዊ ትግል አካሄዶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በጦርነት አሸናፊ እና ተሸናፊ የለም። መፍትሔ ደግሞ ምክክር ነው።
የጦርነትን አስከፊነት የሚረዳው እና የሰላምን ዋጋ ውድነት የሚረዳው የግጭቱ ገፈት ቀማሽ የሆነው ማኅበረሰብ እንጂ በምቾት ቀጣና የሚኖረው አራጋቢ አይደለምና ሀገራት የወጡበትን መንገድ እኛም በአጽንኦት በመመርመር መከተል ይገባል።
ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያና ለሌላውም በግጭት አዙሪት ውስጥ ላለ ሀገር ተሞክሮ የሚሆን ልምድን ከገነቡ ሀገራት መካከል ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ከሩዋንዳ ተጠቃሽ መሆናቸውን በአፍሪካ ለሚከሰቱ ግጭቶች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ለማምጣት በመላው አፍሪካ የሚሠራው አኮርዳ (accord.org.za) በዝርዝር ያስረዳል።
እንደ አኮርዳ ቱኒዚያ በገለልተኛ እና ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር ማዕቀፍ ሰላሟን መልሳለች። የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ታዋቂ እና ገለልተኛ የሆኑ ምሁራንን፣ የሃይማኖት አባቶችን እና የሲቪል ማኅበራት መሪዎችን በማካተት ውጤታማ አድርጋለች።
ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የእውነት፣ የእርቅ እና የካሳ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ የባሰ ቀውስ ከሚያስከትለው የከፋ ውጤት በጊዜ መውጣት ችላለች።ግፍ የፈጸሙ ሰዎች እውነቱን እንዲናገሩና ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ ተጎጂዎች ደግሞ በይፋ እውቅና እንዲያገኙ እና የሞራልና የቁስ ካሳ እንዲሰጣቸው በማድረግ የተገኘ የሰላም አየር ነው።
ሩዋንዳም ከ800 ሺህ በላይ ዜጎቿን ያሳጣትን የእርስ በእርስ ጦርነት የቋጨችው የማኅበረሰብ አቀፍ የፍትህና የሰላም ግንባታ ሂደትን ተግባራዊ በማድረግ ነው።ይህም በመደበኛው የሕግ ሥርዓት ብቻ የማይፈቱ የቆዩ ቁስሎችን ለመፈወስ ሩዋንዳ እንደ ጋቻቻ ያሉ ባህላዊ የዕርቅ እና የፍትህ ሥርዓቶችን ተጠቅማለች።
በአጠቃላይ በታሪክ የገጠማቸውን የግጭት አዙሪት የዜጎችን እኩልነት እና ሰብዓዊ መብት የሚያስከብር፣ የሁሉንም ብሔር ተገቢ ፍላጎት የሚያሟላና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ
በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ መገንባት፣ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚያገኙባቸውን የጋራ የልማት ፕሮጀክቶችንም ተግባራዊ በማድረግ የተገኘውን ሰላም አጽንተዋል። ይህም የሰላምን ፍሬ ህዝቡ በኢኮኖሚው እንዲያየው፣ የሥራ ዕድል እና የጋራ ጥቅም ባለበት ቦታም ጦርነት ተቀባይነት እንደማይኖረው ማረጋገጫ ሆኗል። ለተሳካ እና ገቢራዊ ሰላም የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የተፋላሚ ወገኖች ለሀገር ሰላም ሲባል መሸነፍን እንደ ትልቅ ድል ነው ሊወስዱ እንደሚገባ ተሞክሮዎች እማኝ ናቸው።
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


