በአማራ ክልል በተከሰተዉ የጸጥታ መደፍረስ እና ግጭት ምክንያት በክልሉ ነዋሪወች ላይ በርካታ ሰብኣዊ፣ ማህበራዊ፣ ቁሳዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራወችን አስከትሏል፡፡ ይህም በክልሉ ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍን፣ ተማሪወች እንዳይማሩ፣ ህዝቡም ስለ ነገው ህይወቱ እንዳያቅድ ብሎም በተረጋጋ እና በተስፋ የየእለት ስራውን እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በክልሉ ከሁለት አመት በላይ በቆየው ግጭትም የበርካታ ሰወች ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል የግለሰብም ሆነ የመንግስት ተቋማት ንብረቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወድመዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተው የሰላም መጓደልም ለህገወጥ ተግባራት መንገድ ከፍቷል፡፡ እገታ፣ ዝርፊያና ህገወጥ ተግባራት ተበራክተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ማህበረሰቡ በሰላም ወጦ በሰላም ስለመመለሱ ስጋት እንዲያድርበት በማድረግ ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ጤና ጫና አስከትላል፡፡
የሰላሙ መደፍረስ በተለይም በመማር ማስተማሩ ላይ ያሳደረው ጫና የከፋ ሲሆን የነገ ሃገር ተረካቢ ህጻናትም መጻዒ እድላቸዉን የሚያጠለሽ ተግባር ተደቅኖባቸዋል፡፡ታዳጊወቹ የነገ ህይወታቸውን በእውቀት እንዳያበለጽጉ እና ለሃገርና ለቤተሰብ ማበርከት የሚገባቸውን እውቀት እና ክህሎት እንዳያገኙ ሆነዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ የትውልድ ክፍተትን እንዳይፈጥር ስጋት አሳድራል፡፡ የክልሉ እርሶአደሮች በብዙ ድካምና ወጭ ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ወስደው እንዳይሸጡ እና እንዳይለውጡ፣ ነጋዴው እና ሸማቹም በአግባቡ እንዳይገበያዩ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን አባብሷል፣ ወላዶች እና ህሙማን በወቅቱ ወደ ህክምና ተቋማት ደርሰው አስፈላጊውን ህክምና እና ድጋፍ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል። ጦርነት የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ችግር ሲሆን ከዚህ መረዳት የሚቻለው ግን የሰላምን አስፈላጊነት እና አይተኬነት ነው፡፡
ከጦርነት የምናተርፈዉ ሰቆቃ፣ መከራ፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ እገታ፣ የአካል እና የህይወት ማጣትን፣ የንብረት ውድመትን እና የአእምሮ ጤና እክልን እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌለዉ ማህበራዊ ቀውሶችን ነው፡፡ በመሆኑም ስለሰላም ስንል ሁላችንም ስለሰላም ማቀንቀንና መስበክ የየእለት ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ ስለሰላም ማሰብና መስራት የሚገባንም የጦርነትን አሰቃቂነት እና አውዳሚነት ስለተረዳንና ከሰላም የምናተርፈዉ ጉዳይ የበዛ ስለሆነ ነው፡፡ የሰላምን ዋጋ ለማወቅም የጦርነትን አስከፊ ገጽታወች ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም በዋጋ የማይተመን የብዙ ችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ነውና ሰላም በክልላችን ይሰፍን ዘንድ ከሁላችንም ብርቱ ስራን ይጠይቀናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ሰላም አበክረን የምንጨነቅና የምንፈልግ ስለመሆናችን የሚያስረዱ በርካታ መገለጫወች ያሉን ሲሆን ከሰላምታ አቀራረባችንም ሆነ ምላሾቻችን ጭምር ሰላምን ናፋቂወች ስለመሆናችን ነው፡፡ ሰላም አደራችሁ፣ ሰላም ሁኑ፣ ሰላም ግቡ፣ በሰላም አውለን፣ ሰላም ጊዜ አምጣልን በማለት የምንመኘው እንዲሁ በዘልማድ ሳይሆን የሰላምን አይተኬ ዋጋ በማወቃችን ነው፡፡
ሰላም የሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ በመሆኑ ስለ ሰላም ሲባል ማንኛውንም የግልም ይሁን የቡድን ፍላጎትን እና ጥቅምን በመተው ለሰላም ሲሉ መሸነፍ የአዋቂነት እና የአሸነናፊነት መገለጫ ነውና፡፡ የትኛውም የሃሳብ ልዩነቶች ወደ መፍትሄ የሚደርሱትም በሰላማዊ ውይይት እና ድርድር ብቻ መሆኑን በርካታ አለማቀፍ ተሞክሮወች ያሳያሉ፤ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በክልሉ በርካታ ቦታወች የተጀመሩ ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጡ ብሎም ወደቀደመው የክልላችን ገጽታ ይመለሱ ዘንድ ለሰላም ውይይቱ የየበኩላችን ድርሻ ማበርከት ለነገ የማይባል ቁልፍ ተግባር ነውና ዛሬውኑ እንተግብረው፡፡
የሰላም ውይይቶችን በማገዝ እና የማስቀጠል ተግባራችንም የተስተጓጎለውን የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ህዝቡም ያለስጋት የየእለት ተግባሩን እንዲያከናውን ብሎም የሰላም አየር እንዲሰፍን ያስችላልና ሁላችንም ስለ ሰላም አበክረን እንስበክ፡፡
በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


