የትውልድ  ቅብብሎሹ ፈተና

0
152

የአማራ ክልል ያለፉትን ከ2 አመት በላይ በሰላም እጦት የነገ ሀገር ተረካቢዎች በሚወጡበት የትምህርት ዘርፍ ላይ አደገኛ ስብራትን ፈጥሯል። ችግሩ በየዓመቱ በነበረው የትምህርት ዘርፍ ላይ ምን ያህል ጫና እንዳሳደረ ለመረዳት በ2016 ዓ.ም 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ዉጭ ሆነዋል። በ2017 ዓ.ም ደግሞ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች በር አልደረሱም፤ ከመምህራን ጋር አልተገናኙም።

የሰላም እጦቱ ሦስተኛ ዓመቱን በያዘበት 2018 ዓ.ም ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ታሳቢ ያደረገ 7.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ምዝገባ እንደሚከናወን ትምህርት ቢሮ እቅዱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። የሰላም መደፍረሱ ግን አሁንም ተማሪዎችን ከትምህርት፣ መምህራንን ከሙያቸው፣ ባለድርሻ አካላትን ከድጋፍ እና ክትትል ውጪ እንዲሆኑ አድርጓል። በተጨማሪም የትምህርት ተቋማትን ለጉዳት እየዳረገ ያለው የሰላም እጦት መፍትሄ ያገኝ ዘንድ የክልሉ ምክር ቤት ሳይቀር ዋና አጀንዳው አድርጎታል።

ምክር ቤቱ 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን ታኅሳስ 16 እና 17 ሲያካሂድ ከያዛቸው  ጉዳዮች መካከል የትምህርት ዘርፉ አንደኛው ነው።  የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆኑት አቶ ጥላሁን ወርቅነህ እስካሁን አራት ሚሊዮን 306 ሺህ 273 ተማሪዎች መመዝገባቸውን አሳውቀዋል። የምዝገባው አፈጻጸም በትምህርት ቤቶች ደረጃ የተለያየ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም በቅድመ አንደኛ 85 በመቶ፣ በአንደኛ ደረጃ 58 በመቶ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 36 በመቶ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የተማሪ ምዝገባው እና የመማር ማስተማር ሁኔታው ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ መሆኑንም አስታውሰዋል። ሕጻናትን ከትምህርት የማራቅ ዝንባሌ በተለይ በጎጃም ዞኖች የከፋ መሆኑን ነው ሃላፊዉ የጠቆሙት። በእነዚህ ዞኖች ያለው የምዝገባ አፈጻጸም ከ18 በመቶ የበለጠ እንዳልሆነ ገልጸዋል፤ ይህም በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል። እንደ ቢሮ ኃላፊው አሁንም ወደ ትምህርት ያልመጡ ተማሪዎች፣ ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አስታውሰው ርብርብ እንዲደረግ ምክር ቤቱን ጠይቀዋል።

የምክር ቤት አባላትም መነሻ ጽሁፉን መነሻ አድርገው የችግሩን አሳሳቢነት እና ለተሻለ የትምህርት ሥራ የቢሆን ሐሳቦችን ሰንዝረዋል። ከአብዛኛው አባላት ለተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መነጠል ግጭቱን ጨምሮ ስደት፣ የቀን ሥራ፣ በትምህርት ተስፋ መቁረጥ እና ሌሎችም ተነስተዋል።

የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ በበኩላቸዉ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ትምህርት ያልተመለሱ ተማሪዎች አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንኳን መረጃ እንደሌለ በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ገልጸዉ መረጃ ከሌለ ደግሞ እንዴት ነው እነዚህን ተማሪዎች መመለስ የሚቻለው? ሲሉም ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ከዚህ ቀደም የፍልሰት ልማድ የሌለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አሁን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ መፍለስ የሁልጊዜ ተግባር  ሆኗል ። ይህ ልምምድም በጣም አደገኛ ነው ያሉት የምክር ቤት አባሉ ከክልሉ በስፋት እየወጡ ያሉት ዕድሜያቸው በአሥራዎቹ ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። የምክር ቤት አባሉ አክለዉም ደጀን ከተማ ላይ “ለሁለት ሶስት ቀናት ባደረግነው ምልከታ ባየነው ቁጥር በጣም ደንግጠናል” ብለዋል። በመሆኑም ትምህርት ላይ የሚሠራው ሥራ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ጠቁመዋል።

ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ከትምህርት የራቁ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ርብርብ የሚፈልግ መሆኑን አረጋግጠው ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች የመጠገን ሥራ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል። የትምህርት ተቋማት የመሠረተ ልማት ሥራዎች ትኩረት እንዲያገኙም ጠይቀዋል። በትምህርት ላይ የሚገኙትን ብቁ ለማድረግ ግብዓት የማሟላት እና የምገባ ተግባሩ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል። የትምህርት ቤቶችን የደረጃ ማሻሻል ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው

“በዚህ ዘመን የሥራ ገበያውን መሠረት ያደረገ ጥራት ያለው የሰው ኃይል እያቀረብን ነው ወይ በሚለው መነጋገር ሲኖርብን፤ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ አሁናዊ ትኩረታችን ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዴት እናምጣቸው በሚለው ሆኗል ነው” ያሉት።

ትምህርት የሁሉም የልማት ሥራዎች መሪ ተግባር መሆኑን የገለጹት አቶ አረጋ፣ ነገር ግን ዘርፉ በጸጥታ እና ከጸጥታ ውጭ ባሉ ምክንያቶች እየተፈተነ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የትምህርት ዘርፉን ቸንክረው የያዙ የጸጥታ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አሳስበዉ ከትምህርት የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስም ሰፊ ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

 

መረጃ

  • ሐሳዪ – ወጌሻ
  • ሐራሲ – ገበሬ
  • ሐኪመ ስን – የጥርስ ሐኪም
  • ሐዳፍ -መምህር
  • መሠንየ ጸጉር-ጠጉር አስተካካይ
  • መሠግረ ዓሣ – ዓሣ አጥማጅ
  • መዐቅብ – ዘበኛ
  • መንግድ -ነጋዴ

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here