ብሔራዊ ፓርኩ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ በዳውሮ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ መካከል ነው የሚገኘው፡፡ የፓርኩ ጠቅላላ ስፋት 1215 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡ መገኛ ቀጣናው ከአዲስ አባባ 460፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ሀዋሳ 330 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡
በመልካምድራዊ አቀማመጡ ዝቅተኛው 500 ከፍተኛው 2000 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ተለክቷል፡፡ ቀጣናው ኮረብታማ፣ በደን የተሸፈነ ሳር ለበስ ተዳፋታማ መሬት፣ ወንዞች የተሸረሸሩ ሸለቆዎች መለያዉ ናቸው፡፡
ከአጠቃላይ የፓርኩ ቀጣና 62 በመቶ ቁጥቋጦ የሚታየበት የሳር ምድር እና ደን ለበስ ነው፡፡ በውስጡም 106 የእፅዋት፣ 137 የዓዕዋፍ ከነዚህም መካከል የስድስት ብርቅዬ ዝርያዎች መገኛ ነው፡፡ ከዱር እንስሳት 57 ዝርያዎች ከነዚህ መካከል የአንበሳ፣ ነብር፣ ዝሆን፣ ጐሽ፣ ጐማሬ ዝንጀሮ፣ ጉሬዛ መገኛኘታቸው ተረጋግጧል- በፓርኩ፡፡
በቀጣናው ከሚገኙ እፅዋት ዝንጅብል፣ የቡና ተክል፣ ኮረሪማ፣ እንሰት፣ የእጣን እንጨት፣ ጌሾ በገቢ ምንጭነት ከሚያገለግሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የፓርኩን ክልል 40 ያህል ወንዞች በየአቅጣጫው እየፈሰሱ ያረሰርሱታል፡፡ የፓርኩ ቀጣና ለጐብኚዎች የተመቸው ወቅት ከህዳር እስከ ጥር ያሉት ወራት ናቸው፡፡ ርጥበታማው ወቅት ከመጋቢት እስከ መስከረም ወር ያለው ሲሆኑ ለጐብኚዎቹ ለመንቀሳቀስ የማይመቹ የማይምከሩ ናቸው፡፡ በዓየር ንብረቱ ከዝቅተኛው 10 እስከ ከፍተኛው 29 ዲግሪ ሴል ሺየስ ተለክቷል የፓርኩ ቀጣና፡፡
ወደ ፓርኩ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ – ጂማ – አመያ ወይም ሻሸመኔ፣ ሰዶ ዋካ ቶቻን ተከትሎ መድረስ ይቻላል፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት አክሽንቱር ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ኤሌፋንት፣ ሳፊሪ ቡኪንግ እና ናሽናል ፓርክ አሶሴሽን ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


