የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ከውድድርነትም አልፎ የአህጉሪቱ የእግር ኳስ የኃይል ሚዛን የተቀያየረበት፣ የታላላቆች ውድቀት እና የታናናሾች መነሳት የታየበት ታሪካዊ መድረክ እንደሚሆን ከወዲሁ ምልክቶች ታይተዋል፤ እየታየም ነው። የጋቦን ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማለፍ ባለመቻሉ የሀገሪቱ መንግሥት ቡድኑን አግዷል። ሁሉንም የብሄራዊ ቡድኑ የአሰልጣኞች አባላትን አሰናብቷል። የቡድኑ አምበል የነበረውን የቀድሞውን የአርሴናል አጥቂ ኦባምያንግ ከዚህ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑን እንዳይወክል ማገዳቸውም ተሰምቷል።
በ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ለአፍሪካ እና ለአረቡ ዓለም የመጀመሪያ የሆነውን የግማሽ ፍጻሜ ታሪክ ያስመዘገቡት የአትላስ አንበሶቹ በሜዳቸው የሚደረገውን ዋንጫ የማንሳት ግዴታ ውስጥ ናቸው። የአሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉ ቡድን በዓለም ዋንጫው ላይ ያሳየው ጠንካራ የመከላከል መዋቅር (Defensive Block) እና ፈጣን መልሶ ማጥቃት እንደነበር አይዘነጋም። ነገር ግን አሁን በሜዳቸው ሲጫወቱ ይህ ታክቲክ ብቻውን እንደማያዋጣ አምነዋል። አብዛኛዎቹ ተጋጣሚዎች በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ መከላከልን መሰረት አድርገው ስለሚጫወቱ ዋሊድ ሬግራጉ ቡድናቸውን ወደ ኳስ ቁጥጥር እና ፈጠራ (Possession and Creativity) እየቀየሩት መሆኑን ምልክቶች ታይተዋል።
በዚህ አዲስ ፍልስፍና ውስጥ ቁልፍ መሣሪያ የሆነው የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ብራሂም ዲያዝ ነው። ዲያዝ በቡድኑ መኖሩ ለሞሮኮ የፊት መስመር ተለዋዋጭነትን ሰጥቶታል። እንዲሁም ከአሽራፍ ሀኪሚ እና ኖሳይር ማዝራዊ የመስመር ላይ የማጥቃት አቅም ጋር ተዳምሮ ሞሮኮን አስፈሪ አድርጓታል። ነገር ግን በደጋፊ ፊት መጫወት የሚኖረው ጫና እና ተጋጣሚዎች ሞሮኮን የማሸነፍ ጉጉት ለአሰልጣኝ ሬግራጉ ትልቁ የቤት ሥራ ነው።
የአትላስ አንበሶቹ በኳታር ዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ ያሳዩት ብቃት በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያላቸውን ጫና ከፍ አድርጎታል። ነገር ግን ታሪክ እንደሚያሳየው አስተናጋጅ ሀገራት በገዛ ሜዳቸው መጫወት ያለባቸው ጫና ከፈተኛ ነው። ደጋፊው በየጨዋታው ድልን ብቻ ሳይሆን ማራኪ ጨዋታን ይጠብቃል፤ ይህ ደግሞ የተጫዋቾችን የአዕምሮ ዝግጁነትን የሚፈትን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ግን ሞሮኮ ዋንጫውን በቤቷ ታስቀራለች የሚል ከፈተኛ ግምት አግኝታለች።
ዋንጫውን ለማንሳት ከሞሮኮ ቀጥሎ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሴኔጋል እና ናይጄሪያ ናቸው። ሁለቱ ሀገራት ፍጹም የተለያየ የእግር ኳስ ፍልስፍና ይዘው ነው ወደ ውድድሩ የመጡት። ሴኔጋል ባለፉት አምስት ዓመታት የአፍሪካ እግር ኳስን በበላይነት የመራች ሀገር ናት። ምንም እንኳ አሊዮ ሲሴ ከቡድኑ ጋር ቢለያዩም የገነቡት የእግር ኳስ ሥርዓት ግን አሁንም ከነነፍሱ አለ። የሴኔጋል ትልቁ ጥንካሬ በቡድን ጥልቀት (Squad Depth) ላይ የተመሰረተ ነው። ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስመር ድረስ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ ድንቅ ኮከቦች አሏቸው። ታክቲካቸው በአካላዊ ጉልበት እና በመስመር ፍጥነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን እንደ ኒኮላስ ጃክሰን እና ፓፔ ማታር ሳር ያሉ ወጣቶች ለቡድኑ አዲስ ጉልበት እንደሚሆኑ የካፍ ኦንላይን መረጃ አመልክቷል።
እንደ ሳዲዮ ማኔ ያሉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ከወጣት ኮከቦች ጋር መጣመራቸው ደግሞ ቡድኑን ይበልጥ አስፈሪ አድርጎታል። የሴኔጋል ታክቲክ ብዙውን ጊዜ በመሀል ሜዳ የበላይነት እና በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ ፈጣን ሽግግር ላይ ያተኩራል። የቡድኑ ዋነኛ ጥያቄ ከረጅም ዓመታት ስኬት በኋላ የተጫዋቾቹ የማሸነፍ ጥማት እንደቀድሞው ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መሆኑን ሱፐር ሰፖርት አስነብቧል።
ናይጄሪያ የአፍሪካ ብራዚል ለመሆን የምትጥር ቡድን ናት። ቪክቶር ኦሲሜህን፣ አዲሞላ ሉክማን እና ቪክቶር ቦኒፌስን የያዘው አጥቂ ክፍል የትኛውንም የመከላከያ ግንብ ማፍረስ እንደሚችል የሱፐር ስፖርት መረጃ አስነብቧል። ነገር ግን የናይጄሪያ ችግር ሚዛን (Balance) መሆኑን ሱፐር ስፖርት ያስረዳል። አጥቂዎቻቸው ያላቸውን ጥራት ያህል ተከላካዮቻቸው እና ግብ ጠባቂያቸው አስተማማኝ አይደሉም ማለት ይቻላል። የናይጄሪያ እግር ኳስ ፍልስፍና “ከገባብን በላይ ግብ አስቆጥረን እናሸንፋለን” የሚል ነው። ይህ ሀሳብ ምናልባት በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል።
የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ትልቁ ክስተት የሱዳን ብሄራዊ ቡድን (የጄዲያን ጭልፊቶች) ጉዞ ነው። ይህ ታሪክ በእግር ኳስ ሜዳ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የሰው ልጅን ጽናት (Resilience) የሚያሳይ ነው። ሱዳን በከባድ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች። የሀገር ውስጥ ሊግ ውድድርም እየተካሄደ አይደለም፤ በርካታ ስታዲየሞች ፈራርሰዋል፤ ገሚሶች ለወታደራዊ አገልግሎት ውለዋል። ተጫዋቾቹም ቤተሰቦቻቸውን ጥለው በስደት ነው የሚኖሩት። በሜዳቸው ማድረግ የነበረባቸውን የማጣሪያ ጨዋታዎች በሊቢያ (ቤንጋዚ) ማድረጋቸው አይዘነጋም።
በአፍሪካ ዋንጫ ታሪከ በምድብ ጨዋታ ተጫዋቾቿ አንድም ግብ ሳያስቆጥሩ በራስ መረብ ላይ በተቆጠረ ግብ ጥሎ ማለፍ የደረሰች የመጀመሪያ ቡድን ሆናለች። የሱዳን እግር ኳስ ታክቲክ ትዕግስት እና መስዋዕትነት ነው። ተጋጣሚ የኳስ ቁጥጥር እንዲወስድ በመፍቀድ እና የራስን የግብ ክልልን በመዝጋት በተገኘው አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ወይም በቆመ ኳስ ግብ ማስቆጠር ሌላኛው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ታክቲክ ነው። ይህም ፀር እግር ኳስ (Anti-football) ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ለሱዳን ከታክቲክም በላይ ነው። ተጫዋቾቹ የሚጫወቱት ለደሞዝ ወይም ለክብር ብቻ ሳይሆን በጦርነት ለፈራረሰችው ሀገራቸው አንድነት እና ደስታ ለመፍጠር ጭምር ነው። “ለሕዝባችን ፈገግታን እንፈጥራለን” የሚለው መሪ ቃላቸው ሜዳ ላይ ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል። የሱዳን ተጫዋቾች በጋና ላይ ያሳዩት የትግል መንፈስ ዘመናዊ እግር ኳስ በቴክኒክ ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦናም እንደሚወሰን ያስመሰከረ አዲስ ክስተት ነው።
የሱዳን ከምድብ ማለፍ የጋናን ውድቀት አብስሯል። ጋና ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አልቻለችም። ይህ ክስተት ለአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ መልእክት አለው። በማጣሪያው አራት ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን የሆነችውን እና በኮከቦች የተሞላችውን ጋናን ከውድድር ውጪ በማድረግ ያለፉበት መንገድ በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት አስደናቂ ክስተቶች አንዱ ነው። ይህ የጋና ውድቀት እንደ ኮሞሮስ፣ አንጎላ እና ቡርኪናፋሶ ላሉ ሀገራት ትልቅ ተስፋ ሰጥቷል።
የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ በሁለት ተቃራኒ ዋልታዎች መካከል የሚደረግ ፍልሚያ ይሆናል። በአንድ በኩል እንደ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ እና ሴኔጋል ያሉ በከፍተኛ ቴክኒክ እና በኮከቦች የተሞላ ቡድን የማጥቃት እግር ኳስን እያሳዩን ነው። በሌላ በኩል እንደ ሱዳን ያሉ ቡድኖች በታክቲክ ዲሲፕሊን እና በማይበገር የቡድን መንፈስ ታላላቆቹን ከመንገድ ማስቀረት እንደሚችሉ አሳይተዋል።
በወረቀት ላይ ያሉ የእግር ኳስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሞሮኮ በሜዳዋ፣ በደጋፊዋ እና በያዘችው የተጫዋች ጥራት ዋንጫውን ለማንሳት ትልቅ እድል አላት። ይሁን እንጂ የአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ እንደሚያስተምረን በተደጋጋሚ አስተናጋጅ ሀገራት ጫናውን መቋቋም ሲያቅታቸው ይስተዋላል። እናም ይህ ክፍተት ከተፈጠረ ሴኔጋል ባላት ልምድ እና መረጋጋት ዋንጫውን ለመረከብ በተጠንቀቅ እንደምትጠብቅ ይገመታል። ናይጄሪያ የምትታወቀው በማጥቃት ኃይሏ ቢሆንም የመከላከል ችግሯ ዋንጫውን እንዳታነሳ እንቅፋት ሊሆንባት ይችላል- የብዙዎች ግምት ነው። በሞሮኮ እየተካሄደ ያለው የእግር ኳስ ድግስ የቴክኒክ ብቃት እና የስነ ልቦና ጥንካሬ የሚፈተሽበት ምናልባትም የአፍሪካ እግር ኳስ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት የታሪክ መድረክ እንደሚሆን የሱፐር ስፖርት መረጃ አመልክቷል።:
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


