የኢንቨስትመንቱ መልካም አጋጣሚዎች

0
104
  • በበጀት ዓመቱ ከ670 በላይ ቢሊዮን ብር መዋለ ነዋይ ወደ ክልሉ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል

ምጣኔ ሀብታዊ መረጃዎችን በብዛት የሚያስነብበው ዓለም አቀፉ ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ኢንቨስትመንትን እና ቱሪዝምን ፍጹም ሰላምን የሚሹ ዘርፎች መሆናቸውን ያስገነዝባል። ዘርፎቹንም የሀገራት ሁለንተናዊ ዕድገት እስትንፋስ ይላቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገራችን የሚታየው ግጭት ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ኢንቨስትመንት አንዱ ነው። የአማራ ክልል ደግሞ በዚህ ተጠቃሽ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱ ደግሞ ዘርፉ እንዲነቃቃ አድርጎታል።

ዘ ኢኮኖሚስት እንዳስነበበው በአንዲት ሀገር የሰላም እጦት ካለ ኢንቨስትመንቱ በእጅጉ ይጎዳል፣ ሙሉ ለሙሉም ሊጠፋ ይችላል። በተለይ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) በእጅጉ ይጎዳል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት እና በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት የክልሉን ኢንቨስትመንት ጎድቶታል። በችግር ውስጥም ሆኖ ግን ስኬቶች እንደተገኙ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግኙነት ባለሙያ ወ/ሮ ውብነሽ ዱቤ ተናግረዋል። ለአብነት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን፣ ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ምርት (ኤክስፖርት) መጠን መጨመርን፣ በተኪ ምርት (Import Substitute) የተመዘገበውን ውጤት እና በማምረት አቅም የተመዘገበውን አበረታች ዕድገት ጠቅሰዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ካለባቸው አካባቢዎች መካከል ትጠቀሳለች። የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ሁሴን ሙሄ በ2018 በጀት ዓመት የ25 ዓመቱን አሻጋሪ እና ዘላቂ የልማት ዕቅዱን መሠረት በማድረግ የትኩረት ተግባራትን እንደለዩ ተናግረዋል፤ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን ማጎልበት፣ ውጤታማና አዋጭ ፕሮጀክቶችን መገምገም፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማሟላት፣ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እና ምርታማነትን ማሳደግ ደግሞ የተለዩት ተግባራት ናቸው::

እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ በግማሽ ዓመቱ ለ46 አዳዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል:: ይዘውት የመጡት ካፒታል ደግሞ ስምንት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ነው::

በከተማዋ በዝቅተኛ፣ በመካከለኛ፣ በከፍተኛ ደረጃ በምርት ላይ ያሉ 127 ፕሮጀክቶች (ፋብሪካዎች) እንደሚገኙ አቶ ሁሴን አንስተዋል፤ እነዚህም እርስ በእርሳቸው እና ከሌላም ጋር የግብዓት ትስስር ያደርጋሉ፤ በዚህም ፋብሪካዎች 694 ሚሊዮን ዶላር የእርስ በርስ ትስስር አድርገዋል ነው ያሉት:: በዕቅድ የተያዘው 94 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደነበር ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል::

በተመሳሳይ ምርታማነትን ለማሳደግ “ውሎዬ በኢንዱስትሪ መንደር” በሚል የዐሥር ቀናት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ሙሉ ለሙሉ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን የማዳረስ ሥራ ተሠርቷል:: ይህም የማምረት አቅማችንን አሳድጎታል ብለዋል:: የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 62 በመቶ መድረሱንም አንስተዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከውጪ ለሚገቡ ምርቶች ሀገራችን የምታወጣው ምንዛሪ ከፍተኛ ነው፤ ይህን ለማስቀረት ታዲያ አበረታች ሥራ መሠራቱን አቶ ሁሴን ሙሄ ተናግረዋል፤ 26 ፋብሪካዎች ተኪ ምርቶችን እያመረቱ እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊው በዚህም 23 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል ነው ያሉት::

አቶ ሁሴን እንዳሉት ስምንት ፋብሪካዎች የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ኤክስፖርት ያደርጋሉ:: በዚህም በግማሽ ዓመቱ 40 ነጥብ አራት ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል::

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አንድም ባለሀብት አጥሮ የተቀመጠ አለመኖሩ ለዘርፉ ዕድገት መልካም አጋጣሚ ነው፤ ነገር ግን በተሰጣቸው ጊዜ እና በውላቸው መሠረት ወደ ምርት ያልገቡት ላይ በሁለት ዙር መሬታቸው ተነጥቋል:: በእነሱ ምትክ ሌሎች አልሚ ባለሀብቶችን በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ በማወዳደር እናስተላልፋለን ነው ያሉት::

በተለያዩ ምክንያቶች ማምረት ባቆሙ ኢንዱስትሪዎች ላይም የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አስታውቀዋል::

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ወ/ሮ ውብነሽ ለባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ነግረውናል። ማነቆ የሆኑ መመሪያዎችንና ደንቦችን ማሻሻል፣ መሠረተ ልማቶችን መሟላት፣ የአካባቢ ፀጋን በመለየት ወደ ሥራ መግባት፣ ለገንዘብ አቅርቦት (ብድር) ከአበዳሪ ተቋማት (ከባንኮች) ጋር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ፣ የመሬት አቅርቦት ሥርዓቱ መሻሻሉ እና አስፈላጊውን መስፈርት ለሚያሟሉ ባለሀብቶች ዕቃዎችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ገቢ እንዲደረጉ መፈቀዱ ከተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች መካከል ዋናዎቹ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል፤ ለአብነትም በ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ስድስት ሺህ 317 ቋሚ እና አንድ ሺህ 852 ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል:: ይህም በዕቅድ ከተያዘው በላይ ነው:: በሩብ ዓመቱ ለስድስት ሺህ 207 ቋሚ እና ለ607 ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እንደነበር ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል::

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት ደግሞ ክልሉ በተለይ ለአምራች ኢንዱስትሪው የተመቸ ነው፤ ኢንዱስትሪው የሚጠቀምባቸው ጥሬ ዕቃዎች አብዛኛዎቹ በክልሉ ይገኛሉ:: ሰፊ ሰፊ የሚታረስ መሬት ያለው ክልሉ በተለይ የግብርና ምርትን በመጠቀም ሊያቀነባብሩ የሚችሉ በርካታ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን ማስተናገድ የሚችል አቅም ነው::

እንደ ሀገር የተጀመረው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መድረክ ዘርፉ እንዲነቃቃ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል:: ለዚህም አቶ እንድሪስ አብነት ያነሳሉ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ ሲጀመር የክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች አጠቃላይ የማምረት አቅም 46 በመቶ አካባቢ ነበር፤ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አማካይ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 59 ነጥብ ሁለት በመቶ ከፍ ብሏል::

በተመሳሳይ የ25 ዓመቱ አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው በዚህም አራት መሠረታዊ ጉዳዮች ትኩረት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፤ እነዚህም ምርታማነትና ቅልጥፍና፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የቴክኖሎጂ ልማት እና መዋቅራዊ ሽግግር ናቸው::

ወደ ዘርፉ የሚመጣውን መዋለ ነዋይ ማሳደግ ደግሞ በትኩረት እየተሠራበት ያለ እና ጥሩ ውጤት የታየበት መሆኑን ቢሮ ኃላፊው ያነሳሉ፤ “በዚህ በጀት ዓመት ወደ 670 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር መዋለ ነዋይ ወደ ክልላችን እንዲፈስ ወይም ኢንቨስትመንት እንዲመጣ በትኩረት መሥራት አለብን፤ እስከ አሁን ድረስ በክልሉ ታሪክ ይህን ያህል ዕቅድ ታቅዶ አይታወቅም:: ስለዚህ ከፍተኛ መዋለ ነዋይ ወደ ክልሉ እንዲመጣ ማድረግ አለብን:: ይህን ለማድረግ ደግሞ የክልሉን ኢኮኖሚ የበለጠ ሊቀይሩ የሚችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን” ብለዋል::

ይህን ዕቅድ ለማሳካት ምን ታስቧል? ለሚለው ጥያቄም ከምንም በላይ የክልሉ መንግሥት ዘርፉን ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኛ አቋም ነው ያነሱት፤ ለዚህም ዘርፉ እንዴት መመራት አለበት በሚል የአሠራር ማዕቀፎችን አሻሽሏል፤ መዋቅራዊ አደረጃጀቶችንም አስተካክሏል::

አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳብራሩት በክልላችን ቀደም ሲል ኢንቨስትመንቱ በተበታተነ ሁኔታ ሲመራ ነበር፤ አዲሱ ማቋቋሚያ አዋጅ ግን በተለይ የባለሀብቶችን እንግልት (ከቦታ ቦታ እየሄዱ ወይም በየተቋማቱ የነበረውን ድካም) ያስቀራል፤ ይህም ለዕቅዱ መሳካት እንደ መልካም አጋጣሚ ነው::

በሌላ በኩል ወደ ክልሉ በሚመጡ ኢንቨስተሮች ወይም ባለሀብቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችንም ቢሮ ኃላፊው ያነሳሉ፤ መሬት ከተረከቡ በኋላ ለረጅም ጊዜ አጥሮ ማስቀመጥ እና ላልተፈለገ ዓላማ መጠቀም ይጠቀሳሉ:: እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በዚህ በጀት ዓመት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::

ከኃይል፣ ከገንዘብ እና መሰል አቅርቦቶች ጋር በተገናኘ ችግሮች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፤ ችግሩን ለመፍታት ታዲያ እያንዳንዱ አካል (ተቋም) የዕቅዱ ባለቤት እንዲሆን የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት:: ለምሳሌ ከገንዘብ ተቋማት ጋር በክልሉ ካሉ ሁሉም ባንኮች ጋር፣ ከሁሉም ዲስትሪክት የኃይል አቅራቢ ተቋማት አመራሮች ጋር፣ ከፌዴራል ኃይል አቅራቢ ተቋማት ጋር መግባባት የተፈጠረበት ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል:: የጋራ የስምምነት ሰነድም ተፈርሟል::

አቶ እንድሪስ አክለውም

መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እና የአሠራር ማዕቀፎችን አሻሽሎ ዘርፉን እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል::

ነገር ግን ይህ ሁሉ ድጋፍ ተደርጎ የተሰጣቸውን መሬት በአግባቡ የማያለሙ፣ ላልተፈለገ ዓላማ የሚያውሉ፣ በባንክ አስይዘው የሚጠፉ፣ በባንክ ከተበደሩ በኋላ የተበደሩትንም ሀብት ለሌላ ዓላማ የሚያውሉ ባለሀብቶች እንዳሉ ነው የጠቆሙት፤ ይህን ለማስተካከልና ለማረም መሠራቱን በማንሳት ለአብነትም 2017 መጨረሻ ብቻ ከ986 በላይ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን (መሬት  መነጠቃቸውን) ገልጸዋል::

ተኪ ምርቶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትኞቹን ምርቶች በክልሉ መተካት አለብን ብለን አቅደናል ነው ያሉት::

ተኪ ምርት እንደ ሀገር ራሱን የቻለ ስትራቴጂ አለው:: እንደ ሀገር 93 ምርቶች ተለይተዋል፤ ቀደም ሲል መንግሥት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያወጣባቸው የነበሩ ምርቶች በሀገር መተካት አለባቸው በሚል ተለይተዋል:: ከዚህ ጋር በተያያዘ በክልሉ ማምረት አለብን ብለን የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፤ እነዚህ ተግባራትም ወደፊት “ኢንዱስትሪ በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ በ16 ነጥብ ሁለት በመቶ ማደግ አለበት” ብለን ያስቀመጥነውን የጂ ዲ ፒ (GDP) ድርሻ ሊያሳኩ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ናቸው ብለዋል::

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here