አይበገሬዋ

0
107

ጋናዊቷ ፋሪዳ ቤድዌይ የሶፍትዌር መሃንዲስ፣ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕረነር፣ የአካል ጉዳተኞች መብት ተከራካሪ እና ደራሲ ናት፡፡ አፍሪካ ውስጥ በቴክኖሎጂ መስክ ተፅእኖ ከሚያሳድሩ ሴቶች መካከል በዋናነት ትጠቀሳለች፡፡ እ.አ.አ በ1979 ከጋናዊያን እናት እና አባቷ በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ ነበር የተወለደችው፡፡

ፋሪዳ ቤድዌይ አባቷ ዲፕሎማት በመሆናቸው ምክንያት  እስከ ዘጠኝ ዓመቷ በተለያዩ ሀገራት ማለትም በዶሚኒካ፣ ግሬናዳ እና እንግሊዝ  እየተዘዋወረች ነበር የኖረችው፡፡ በኋላም ወደ ጋና ተመልሳለች፡፡ በአስር ዓመቷ ባጋጠማት የእጅ እና የእግር እንቅስቅሴ ችግር (Cerebral Palsy)  ምክንያት እስከ 12 ዓመቷ ድረስ በእናቷ ከፍተኛ እገዛ በመኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር ትምህርቷን ለመማር የተገደደችው፡፡ ከዚያም     ወደ   እንግሊዝ ሀገር  በመጓዝ     የኮሌጅ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡

ከኸርትፎርድሻየር    ዩኒቨርሲቲም (University of Hertfordshire) በኮምፒውተር   ሳይንስ (Computer Science) ዲግሪዋን ይዛለች፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በኋላ በቴክኖሎጂና በፊንቴክ (FinTech) ዘርፍ በራሷ ሙያዊ ስልጠና እውቀቷን አጠናክራለች፡፡

ፋሪዳ ቤድዌይ የትምህርቷን መንገድ በጽናትና በትጋት በመቀጠል የአፍሪካ ታዋቂ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ለመሆን ችላለች፡፡

ፋሪዳ ከምረቃ በኋላ ለማይክሮ ፋይናንስ ኢንዱስትሪ የባንክ ስርዓቶችን የሚያዘጋጅ የሶፍትዌር ኩባንያ  ሎጂሲኤል ጋና ሊሚትድ ተባባሪ መስራች እና ዋና የቴክኖሎጂ ኦፊሰር ሆናለች፡፡ የእሷ ሚና ኢንዱስትሪውን መገምገም እና መደበኛ የባንክ ስልጠና ለሌላቸው ሰዎች ለመጠቀም ቀላል የሆኑ ተግባራዊ መፍትሔዎች ማምጣትን ያካትታል፡፡ በመሆኑም ፋሪዳ ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የባንክ ስርዓቶችን በመገንባት የማይክሮ ፋይናንስ ኢንዱስትሪው ሙሉ አቅሙን ተግባራዊ ማድረግ እና ለደንበኞቻቸው በቂ የባንክ አገልግሎቶች እንዲሰጡ አድርጋለች፡፡ በእሷ መሪነትም ሎጂሲኤል በጋና ውስጥ ከ600 በላይ ለሚሆኑ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሶፍትዌር መፍትሔዎችን ሰጥቷል፡፡

ፋሪዳ ሎጂሲኤልን በጋራ ከመመስረቷ በፊት በቴሌኮም ሶፍትዌር ኢንዱስትሪ ውስጥ ሠርታለች፣ ለሞባይል ኔትወርኮች እና ለይዘት አቅራቢዎች የሞባይል መተግበሪያዎችን እና አገልግሎቶችን በማዘጋጀት ትሠራ ነበር፡፡

ደራሲ እና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች የሆነችው ፋሪዳ በብዙ የሚዲያ መድረኮች ላይ በመቅረብ ልምዷን አካፍላለች፡፡ ከእነዚህም መካከል እ.አ.አ በየካቲት 2015 የሲኤንኤን የአፍሪካ ድምጾች ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በብሔራዊ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና በጋና ራስን የመከላከል እና የነርቭ ሕመም ላለባቸው ሰዎች ግንዛቤን የሚያሰፋ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በቦርድ አባልነት ታገለግላለች፡፡

ፋሪዳ በአፍሪካ የሚገኙ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑ ታበረታታለች፡፡ አካል ጉዳት ያሰቡትን ከማሳካት  እና  ከፈለጉት ቦታ ለመድረስ   ወደ ኋላ እንደማያስቀር ሁሌም ትናገራለች፡፡  በርካታ ወጣቶችን በተለይ ሴቶችን ቴክኖሎጂ እንዲማሩ ትመክራለች፤ ትገፋፋለች፡፡ ፋሪዳ ባድዌይ በሕይወት ውስጥ ችግሮች ቢኖሩም ትልቅ ህልምን መኖር እና ማሳካት እንደሚቻል ያሳየች ጠንካራ ሴት ናት፡፡

ፋሪዳ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች አነቃቂ ንግግሮችን አድርጋለች፡፡ በተለይም “አካል ጉዳት ውስንነት አይደለም” የሚል መልዕክት ሁልጊዜ ታስተላልፋለች፡፡

በአፍሪካ ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ብዙ ጊዜ የታጨችው ፋሪዳ በቴክኖሎጂ እና በማህበራዊ ተፅእኖ ሥራዋ ምክንያት የተለያዩ የክብር ሽልማቶችን ተቀብላለች፡፡ በተጨማሪም በርካታ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አሸንፋለች፡፡  በማይክሮ ፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለኮምፒውተር  እቀውቀት ላበረከተችው አስተዋጽኦ በንግድ እና በአስተዳደር ዘርፍ፣ በፋይናንስ ዘርፍ  ከፍተኛ ተደማጭነት ያላት በሚል እውቅና አግኝታለች፡፡

 

ሴት አካል ጉዳተኞች፡-

አካል ጉዳተኛ ሴቶች የሚባሉት የአካል፣ የስሜት (ማየት/ መስማት)፣ የአዕምሮ ወይም የንግግር ጉዳት ያለባቸው  ናቸው፡፡ ጉዳታቸው ከተፈጥሯዊ ምክንያት፣ ከበሽታ፣ ከአደጋ ወይም ከጦርነት ሊመጣ ይችላል፡፡ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብዙ ጊዜ የተለያዩ ችግሮችን ያስተናግዳሉ፡፡

የትምህርት እና የሥራ እድል መጥፋት፣ የጤና አገልግሎት እጥረት፣ ጾታዊ ጥቃት እና መገለል፣ ድህነት እና ማህበራዊ መነጠል ያጋጥማቸዋል፡፡ ሆኖም ይህንን ሰብረው የወጡ በርካቶች ናቸው፡፡ ብዙ አካል ጉዳተኛ ሴቶች በትምህርት፣ በቢዝነስ፣ በቴክኖሎጂ፣ ስፖርት እና ማህበራዊ መሪነት ተሳትፈው ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ይህም  ተገቢ ድጋፍ ካገኙ ታላቅ ለውጥ እንደሚያመጡ ማሳያ ነው፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ዙሪያ ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች የአዕምሮ እና የአካል ጉዳት አለባቸው፡፡ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ከሚገኙት አካል ጉዳተኞች መካከል ሴቶች 75 በመቶው ናቸው፡፡  በዓለም ዙሪያ ካሉ ሴቶች ደግሞ 10 በመቶውን ይይዛሉ፡፡

ሴቶች በሕይወታቸው ውስጥ ከወንዶች ይልቅ የአካል ጉዳተኛ የመሆን አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም በድሃ ሀገራት ላይ ይጎላል፡፡ ምክንያቱም ውስን ሀብት ባላቸው ሀገራት   እክል ሲያጋጥም እና ከማጋጠሙ በፊት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በቀላሉ ስለማይቻል ነው፡፡

በሚታመሙበት ጊዜም ወጣት ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ከወንዶች  ይልቅ የሕክምና እርዳታ የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡ በተለይም የሕክምና አገልግሎት ተቋም ከአካባቢያቸው ርቆ በሚገኝባቸው ታዳጊ ሀገራት፡፡  እንደ ክትባት ያሉ የበሽታ መከላከያዎችንም የማግኘት ዕድላቸውም አነስተኛ ነው፡፡ በማህበራዊ፣ በባህላዊ እና በሃይማኖታዊ ምክንያቶች  አካል ጉዳተኛ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ነባር ማህበራዊ አገልግሎቶችን  የመጠቀም ዕድላቸውም አነስተኛ ነው፡፡

በዓለም ዙሪያ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ለማገገም የሚያስችላቸውን ህክምና  20 በመቶ ብቻ እንደሚያገኙ ይገመታል፡፡ በእስያ ፓስፊክ ክልል የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ራሳቸውን የሚያስችል የኑሮ ዘይቤ የላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ሙሉ በሙሉ በሌሎች ላይ ጥገኛ ነበሩ፡፡

የአካል ጉዳተኛ ሴቶችና ልጃገረዶች የአካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመሳሳይ ገጽታ ይጋፈጣሉ፡፡ ነገር ግን ማህበራዊ መገለላቸውና ጥገኝነታቸው እነዚህን ጥሰቶችና መዘዞቹን ያጎላል፡፡

የአካል ጉዳተኛ ሴቶች በአብዛኛዎቹ የትምህርት፣ የሙያ፣ የገንዘብ እና የማሕበራዊ ስኬታቸው  ከአካል ጉዳተኛ ካልሆኑ ሴትና የአካል ጉዳተኛ ወንድ አቻዎቻቸው ጋር ሲነጻጸሩ ብዙም ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ በአንዳንድ ሀገራት ሕጎች በአካል ጉዳተኛ ሴቶችና ወንዶች ላይ በግልጽ አድልዎ ያደርጋሉ፡፡ ሕጎቹ አድልዎ ባይደረግባቸውም እንኳ አካል ጉዳተኛ ሴቶች   በቤተሰቦቻቸው፣በማሕበረሰባቸው እና በመንግሥት እጅ ብዙ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስቱ ሴቶች አንዷ የአካል ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ይህም ከ19 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም  ሕዝብ ይወክላል፡፡

 

መረጃ

ሴት  አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ዋና ዋና እውነታዎች

*ሴቶች ከወንዶች የበለጠ የአካል ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡ ሴቶች 19ነጥብ ሁለት በመቶ ሲሆን  ወንዶች ደግሞ 12 በመቶ ነው፡፡

* 80 በመቶ ገደማ የሚሆኑት አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኞች በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ይኖራሉ፡፡

*አካል ጉዳተኛ ሴቶች በጾታቸው እና በአካል ጉዳታቸው ምክንያት በርካታ መድልዎ ይደርስባቸዋል፡፡

*ከዓለማችን ሕዝብ 16 በመቶ ያህሉ የአካል ጉዳተኛ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይህም ከ700 ሚሊዮን በላይ ሴቶችን ያጠቃልላል፡፡

ምንጭ ejscenter.org ፣ https://techherng.com/ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የUN ሴቶች

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here