በተንጣለለው ሰላማዊ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉ አራት አባት ደሴቶች እና 14ሺህ 121 የሚሆኑ ትናንሽ ደሴቶች ተሰናስለው ህልው ያደረጓት የሩቅ ምስራቃዊቷ ኮከብ፣ ሀገረ ጃፓን በተፈጥሮ ውበት እና በዘመናዊ ስልጣኔ የደመቀች ናት። ጃፓን ከዋናው የእስያ ምድር በምስራቅ ጠረፍ በኩል ጥቂት ፈንጠር ብላ ለብቻዋ ተገልላ በውሃ ተከብባ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ከ123 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ይህች ሀገር፣ በዓለም በህዝብ ብዛታቸው ከሚጠቀሱ አስር ቀዳሚ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች ። የሀገሪቱ የልብ ትርታ የሆነችውና ከ37 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የምታስተናግደው ዋና ከተማዋ ቶኪዮ ደግሞ የዘመናዊነት እና የባህል ውህደት መገለጫ ሆና ትታያለች። እናም የበኩር የሽርሽር ዓምዳችን አድረገናታል። መልካም ንባብ።
ቶኪዮ በሆንሹ ደሴት ላይ በካንቶ ሜዳ ውስጥ ትገኛለች። ከተማዋ በጃፓን ደሴቶች መልክዓ ምድራዊ ማእከል ላይ ትገኛለች ። የከተማዋ ማዕከላዊ ቦታ ሃያ ሶስት ልዩ ወረዳዎችን (special wards) ያካትታል ። የታላቋ ቶኪዮ አካባቢ በዙሪያዋ ያሉትን የሳይታማ፣ ካናጋዋ እና ቺባ ክልሎችንም ያካትታል ። ከተማዋ አራት ግልጽ ወቅቶች ያሉት የአየር ንብረት አላት። በበጋ ወቅት ሞቃታማ እና እርጥበት አዘል ሲሆን፣ በክረምት ደግሞ መጠነኛ ቅዝቃዜ ይኖራል። ከሰኔ መጀመሪያ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ መጠነኛ የዝናብ ወቅት አለ።
የታላቋ ቶኪዮ ሜትሮፖሊታን አካባቢ ከ37.1 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች አሏት። ቶኪዮ በዝቅተኛ የወንጀል መጠን እና በደህንነቷ ትታወቃለች። አብዛኛው የሀገሪቱ የውጭ ሀገር ነዋሪዎች በቶኪዮ ውስጥ ይገኛሉ። እንደ ቺዮዳ፣ ቹኦ፣ ሚናቶ፣ ሺቡያ እና ሺንጁኩ ያሉ ወረዳዎች ለንግድ፣ ለግብይት፣ ለምግብ እና ለመዝናኛ የታወቁ ማዕከላት ናቸው ።
የአሁኗ ቶኪዮ የምትገኝበት አካባቢ በጥንት ዘመን አነስተኛ ጎሳዎች ይኖርበት ነበር። በ1457 የኤዶ ግንብ (Edo Castle) ተገነባ። እ.ኤ.አ. በ 1603 ኤዶ የጃፓን ትክክለኛ (de facto) ዋና ከተማ ሆነች። በ1869 በሜይጂ ተሃድሶ ወቅት ኤዶ ስሟ ወደ ቶኪዮ ተቀየረ፣ ትርጉሙም “የምስራቅ ዋና ከተማ” ማለት ነው። ከተማዋ በ 1923 በታላቁ የካንቶ የመሬት መንቀጥቀጥ እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቦምብ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል ።
ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት አመታት ፈጣን እድገት በማስመዝገብ በ 1964 የበጋ ኦሊምፒክ ጨዋታዎችን አስተናግዳለች። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቶኪዮ መስፋፋቷን ቀጥላለች፣ በዓለም ላይ ተደማጭነት ካላቸው እና በኢኮኖሚ ከበለጸጉ ከተሞች አንዷ ሆናለች።
ታሪካዊ ውጣ ውረዶች እና ትንሳኤ የቶኪዮ ታሪክ በአሸናፊነት የተሞላ ነው። ከተማዋ እ.ኤ.አ. በ1923 በታላቁ የካንቶ የመሬት መንቀጥቀጥ 400,000 ህንፃዎቿን አጥታለች ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም በደረሰባት የቦምብ ጥቃት ከግማሽ በላይ ህዝቧ አልቆባትና አብዛኛው የከተማዋ ክፍል ወድሞ ነበር ። ሆኖም ጃፓን በመልሶ ግንባታ ላይ ባደረገችው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ቶኪዮ በ1964 የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን እስከማስተናገድ የደረሰ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ችላለች ።
ቱሪዝም
ጎብኝዎችን የሚማርኩ የቱሪዝም መስህቦች ቶኪዮ ለጎብኝዎች በርካታ ታሪካዊ እና ባህላዊ መስህቦችን ታቀርባለች ። ከእነዚህም መካከል፦ የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት (Imperial Palace): የታሪክ እና የህንፃ ጥበብ መገኛ የሆነው ይህ ስፍራ የከተማዋ ዋነኛ መለያ ነው።
የሂዬ መቅደስ (Hie Shrine) ሌላኛው የቶኪዮ አሻራ ሲሆን በ14770 ዓ.ም የኤዶን ቤተ መንግስት ለመጠበቅ የተገነባ ነው። ይህ መቅደስ፣ በየሁለት ዓመቱ የሚከበረው የሳኖ ማትሱሪ ፌስቲቫል መከወኛ ነው። ሦስተኛው ኮይሺካዋ ኮራኩዌን (Koishikawa Korakuen) ሲሆን በ1621 ዓ.ም የተመሰረተና የጃፓን እና የቻይናን መልክዓ ምድር በትንሹ የሚመስሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛፎችን የያዘ ጥንታዊ የአትክልት ስፍራ ነው።
ጊንዛ (The Ginza) ደግሞ 1917 ዓ.ም ቶኪዮ ከገጠማት የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ በዘመናዊ መልኩ የተገነባውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀው የግብይት፣ የምግብ እና የመዝናኛ ማዕከል ነው። እዚህ አካባቢ ጥንታዊውን የካቡኪዛ ቲያትር ቤትን መጎብኘት ይቻላል። ብሔራዊ ዲየት ሕንጻ (National Diet Building): የጃፓን ፓርላማ የሚገኝበትና የሀገሪቱን የሕግ አውጭ ሂደት ለመመልከት ለጎብኝዎች ክፍት የሆነ ታሪካዊ ሕንጻ ነው ።
የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ ማዕከሏ ቶኪዮ የዓለም ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ከሆኑ ከተሞች አንዷ ናት። በኤሌክትሮኒክስ፣ በብረት እና በአውቶሞቢል ማምረቻ ዘርፎች ትታወቃለች ። ይህን ግዙፍ የንግድ ማህበረሰብ ለማገልገልም ከተማዋ በዓለም እጅግ ሰፊና ቀልጣፋ የተባለለትን የባቡር እና የሜትሮ ትራንስፖርት ስርዓት ዘርግታለች ።
ሩቅ ምስራቋ የደሴት ሀገር ጃፓን፣ የልብ ትርታ የሆነችው ቶኪዮ፣ ዛሬ ላይ ከ37 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን በማስተናገድ በዓለም ካሉ ግዙፍ የሜትሮፖሊታን አካባቢዎች ቀዳሚነቱን ይዛለች ። ከተማዋ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ በሰላም እና በሥርዓት ማስተናገድ እንዴት ቻለች የሚል አሰደናቂ እንቆቅልሽ አእምሮን ወጥሮ መያዙ አይቀሬ ነው። ስለሆነም በብዙ ፈተናዎች መሀል በፅኑ የአሸናፊነት መንፈስ የተገነባው የከተማዋ መዋቅራዊ ስርዓት እና ቴክኖሎጂ ነው። በዋናነት ከተከተለችው ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ቴክኖሎጂ ጋር የተቆራኘ ነው።
ቶኪዮ ይህን ግዙፍ ሕዝብ ማስተናገድ የቻለችው በዓለም እጅግ ሰፊና ቀልጣፋ የተባለለትን የሕዝብ ትራንስፖርት ሥርዓት በመገንባቷ ነው ። የከርሰ-ምድር ባቡሮች (subways)፣ አውቶቡሶች እና የከተማ ውስጥ ሞኖሬይሎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የየዕለቱን ተጓዥ ያለምንም መጨናነቅ ያጓጉዛሉ። በተለይም በማዕከላዊ ወረዳዎች የቀንና የሌሊት የሰው ቁጥር በእጥፍ የሚጨምር ቢሆንም፣ ይህ የመጓጓዣ ሥርዓት ከተማዋን ሕያው አድርጓታል።
ዘመናዊ የመልሶ ግንባታ እና የከተማ ፕላን ከተማዋ እ.ኤ.አ. በ1923 በታላቁ የካንቶ የመሬት መንቀጥቀጥ እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በደረሰባት የቦምብ ጥቃት አብዛኛው ክፍሏ ወድሞ ነበር። ሆኖም ይህ ውድመት ከተማዋን በዘመናዊ መንገድ እንደገና ለመገንባት እንደ ዕድል ተወስዷል። ሰፋፊ መንገዶች፣ የተሻሻሉ ወደቦች እና የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ቶኪዮ ለከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት ዝግጁ እንድትሆን አድርጓታል ።
ደህንነት እና ማህበራዊ መረጋጋት ያለባት ከተማ መሆኗንም ተደጋግሞ እውቅና ያገኘ ሀቅ ነው። ምንም እንኳን የሕዝብ ብዛቷ እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ቶኪዮ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የወንጀል መጠን ከሚታይባቸው እና ደህንነታቸው ከተጠበቁ ከተሞች አንዷ ናት። ይህ የደህንነት ስሜት እና የኢኮኖሚ ብልጽግና ከተማዋን ለነዋሪዎችም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎች ተመራጭ መኖሪያ አድርጓታል ።
የወደፊት ፈተናዎች ምንም እንኳን ቶኪዮ በጥንካሬ ብትቀጥልም፣ እንደ ህዝብ ቁጥር ማርጀት እና የመንግስት እዳ ያሉ ተግዳሮቶች ከፊቷ ተጋርጠዋል። ይሁን እንጂ ከተማዋ ካሳለፈችው ታሪካዊ የጥንካሬ ጉዞ አንጻር፣ እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁማ የዓለም የባህልና የኢኮኖሚ ማዕከል ሆና እንደምትቀጥል ይታመናል።
አጭር እውነታ
ጃፓን ከ6,800 በላይ ደሴቶች አሏት
ንጉሳዊ ሥርዓቱ በዓለም ላይ እጅግ አሮጌ ነው።
- ሮቦቶች በሆቴሎች፣ ሆስፒታሎች እና መደብሮች ይሰራሉ።
- የ“ሺንካንሰን” ባቡር እጅግ ፈጣን ነው
ከ300 ኪ.ሜ/ሰ በላይ ፍጥነት ይጓዛል።
- ፉጂ ተራራ የተከበረ መለኮታዊ ምልክት ነው
በጃፓን ባህልና ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው።
- ምግብ እንደ ስነ-ጥበብ ይቆጠራል
- ሱሺ፣ ራመን እና ቤንቶ እጅግ የተወደዱ ናቸው።
- 24 ሰዓት የሚከፈቱ መደብሮች (Konbini) ምግብ፣ መድሃኒት እና ክፍያ አገልግሎት ይሰጣሉ።
- ረጅም ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው::
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


