የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና

0
108
African Continental Free Trade Area

በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ግዙፍ ቢሆንም ለአንድ ወገን ያጋደለ ነው:: አፍሪካ ወደ  አውሮፓ ጥሬ ዕቃዎችን ማለትም ማዕድናትን እና የግብርና ምርቶችን ማሽነሪዎችን፣ ኬሚካሎችን፣ ያለቀላቸው ምርቶችን… ታስገባለች:: ይህንንም ከሌሎች  የውጭ ሀገራት የንግድ አጋሮቿ (ቻይና፣ አሜሪካ ሩሲያ…) ጋር የምታከናውነው ነው:: ይህም  ሚዛኑን የተዛባ አድርጎታል::

የአፍሪካ ሀገራት  የእርስ በርስ የንግድ ግብይት ደግሞ 15 በመቶ ብቻ ነው:: ይህም ለከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ሲዳርጋቸው ይታያል:: ታዲያ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተመሥርቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው::

የአፍሪካ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) አፍሪካን ወደ አንድ የጋራ ገበያ ለማሸጋገር  የተጀመረ ታላቅ ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክት ነው:: በርካታ ሀገራትን የሚያካትተው ይህ ስምምነት የጉምሩክ ግብር በመቀነስ እና የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ የአፍሪካ ውስጣዊ ንግድን ለማጠናከር ያስችላል:: ይህ ቀጣና በተለይ ለኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ ለወጣቶች  ሥራ ፈጠራ  አዲስ መንገድ ሊከፍት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል::  ይህም አፍሪካ ከጥሬ እቃ ላኪነት ወደ አለቀለት ምርት ሻጭነት እንድትሻገር ዕድል ይፈጥራል::

ይህ ቀጣና አፍሪካን ከተከፋፈለ ትንንሽ ገበያዎች ወደ አንድ የጋራ ገበያ ለመቀየር ያለመ ታላቅ ኢኮኖሚያዊ ራዕይ ያለው ነው:: ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብን እና ከ50 በላይ ሀገራትን በአንድ የንግድ መድረክ ያገናኛል።

በርካታ ዓላማዎች ያሉት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በዋነኛነት አጀንዳ 2063(እ.አ.አ) ለማሳካት ያለመ ነው:: አጀንዳ 2063 የተሳሰረች፣ የበለጸገች እና ሰላማዊ አፍሪካን” ለመፍጠር የፓን አፍሪካ ራዕይን መሰረት ያደረገ ነው:: “የአፍሪካን አህጉር ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያስፋፉ በሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ የሚታገዝ የእቃዎች እና አገልግሎቶች አንድ ውህድ ገበያን መፍጠር” የሚል የመጀመሪያው ዓላማው ነው::

ነፃ የንግድ ቀጣናው ለካፒታል እና ለሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ አስተዋፅኦ ማድረግ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ ለወደፊቱ አህጉራዊ የጉምሩክ ሕብረት ምስረታ መሰረት መጣል፤ የስምምነቱ አባል ሀገራት ቀጣይነት ያለው እና ሁሉን አቀፍ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የፆታ እኩልነትና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያገኙ ማስቻል፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ገበያ የስምምነቱ አባል ሀገራት የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል:: በአጠቃላይ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና ለአፍሪካ ታላቅ ዕድል ቢሆንም ስኬቱ በወረቀት ሳይሆን በተግባር ላይ የሚታይ ይሆናል::

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና መቼ ተጀመረ ?

በ2018 (ማርች) በሩዋንዳ ኪጋሊ  የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ስምምነቱ የተካሄደው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA)  ሕጋዊ እውቅና ያገኘው እ.አ.አ በ2019 (ሜይ 30) ነው::  በይፋ ሥራ የጀመረው  ደግሞ በ2021 ጥር ላይ ነበር::

ምቹ መንገድ አለመኖር፣ የጉምሩክ ዝግጅት ድክመት እና የኢንዱስትሪ አቅም ልዩነት ቀጣናውን በፍጥነት  ሥራ እንዳይጀምር አድርጎታል::

 

ሌሎች የንግድ ቀጣናዎች

ልብ ሊባል የሚባለው ጉዳይ አፍሪካ ብቻ አይደለችም፤ ብዙ ክልሎች በንግድ ዘርፍ  በመቀላቀል ኢኮኖሚያቸውን አጠናክረዋል:: ለአብነትም  27 አባል  ሀገራት ያሉት የአውሮፓ ሕብረት (EU) ከነጻ ንግድ በላይ የጋራ ገንዘብ (ዩሮ) እና የጋራ ፖሊሲዎች አሉት:: በዓለም ላይ በጣም የተጠናከረ ክልልም ነው::

አሜሪካን፣ ካናዳን እና ሜክሲኮን ያጣመረው (USMCA) የሰሜን አሜሪካ ንግድን ማቀላጠፍን ዓላማ አድርጎ የተነሳ ነው::

የእስያ ነጻ የንግድ አካባቢ (ASEAN Free Trade Area AFTA) 10 የደቡብ–ምሥራቅ እስያ ሀገራትን ያካተተ ሲሆን በክልሉ የምርት እና የኢንዱስትሪ ትስስርን አጠናክሯል::

ሌላው የደቡብ አሜሪካው ሜርኮዥር (MERCOSUR) ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ፓራጓይ እና ኡሩጓይን ያካተተው ይህ የክልል ኢኮኖሚ አንድነት መፍጠር ዓላማው ነው::

በተጨማሪም 15 የእስያ–ፓስፊክ ሀገራትን  ቻይናን፣ ጃፓንን፣ ደቡብ ኮሪያን…ያጣመረው የክልላዊ አጠቃላይ የኢኮኖሚ አጋርነትን (Regional Comprehensive Economic Partnership RCEP) መጥቀስ ይቻላል::

ለአብነት የአፍሪካን እና የአውሮፓን ስናነጻጽረው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና  ልዩነቱ በመጠን ታላቅ እና በእድገት ደረጃ ላይ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል:: የአፍሪካ የንግድ ቀጣና  እና የአውሮፓ ሕብረት ተመሳሳይ ራዕይ፣ የተለያየ እውነታ አላቸው:: ክልላዊ ንግድን ማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ አንድነትን መገንባት በሚለው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና የአውሮፓ ሕብረት በመርሀ ግብር ደረጃ ተመሳሳይ ራዕይ አላቸው:: ነገር ግን በትግበራ ደረጃ ሁለቱ በተለያዩ ሁኔታ ላይ  ይገኛሉ።

የአውሮፓ ሕብረት እ.አ.አ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ብዙ ተግዳሮቶቹን ተሻግሮ የተገነባ ሲሆን ዛሬ ነጻ ንግድ፣ የጋራ ጉምሩክ፣ የሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ እና  የጋራ የመገበያያ ገንዘብ (ዩሮ) በመፍጠር አንድነት ላይ ደርሷል:: ይህ የተጠናከረ ተቋማዊ መዋቅር የአባል ሀገራትን ፖሊሲ በአንድ አቅጣጫ እንዲጓዝ አድርጎታል::

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በተቃራኒው አዲስ ነው:: እ.አ.አ በ2018 ተፈርሞ በ2021 ተግባራዊ የሆነ እና  አሁንም በጅምር ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው:: ሀገራቱ የጋራ ጉምሩክ ወይም የመገበያያ ገንዘብ የላቸውም:: የኢኮኖሚ አቅም ልዩነት፣ የመሰረተ ልማት እና የሎጂስቲክስ እጥረት፣ የጉምሩክ ድክመት፣ በሀገራት መካከል ያለው የፖለቲካ አለመተማመንና በመሳሰሉት ችግር ሊፈጥርበት እንደሚችል ይነገራል::

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለኢትዮጵያ ዕድል ወይስ የሚጠበቅ ፈተና?

ኢትዮጵያ መስከረም 29 ቀን 2018 እ.አ.አ ነበር የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን በይፋ የጀመረችው:: ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ በተጨማሪ በየብስ መጓጓዣም/ትራንስፖርትም/ የማስጀመሪያ ጭነት ሽኝትን ተከናውኗል:: በዚህመሰረት  ወደ ጎረቤት ሀገራት ኬንያ የበቆሎ ምርት፣ ሶማሊያ የአንስሳት ሥጋ አንዲሁም ወደ ደቡብ አፍሪካ ቦሎቄ ልካለች:: የአፍሪካ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ኢትዮጵያን ወደ ትልቅ የአፍሪካ ገበያ ለማገናኘት የሚያስችል አስፈላጊ ኢኮኖሚያዊ እድል ነው:: የኢትዮጵያ ምርቶች (ቡና፣ ቆዳ፣ ተልባ እና ሌሎች  የግብርና ምርቶች) ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ሕዝብ ያለው የአፍሪካን ገበያ መድረስ ይችላሉ:: የንግድ ክፍያ (tariff) መቀነስ ምርቶችን በዋጋ ተወዳዳሪ ያደርጋል:: ኢንዱስትሪና የውጭ ንግድን/ኤክስፖርት/ን ያበረታታል፣ የማንፋክቸሪንግ ዘርፉን (ልብስ፣ ጫማ፣ ምግብ) ማምረት ይጠናከራል::

ኢትዮጵያ እሴት ጨምራ ምርቶቿን እንድትሸጥ ያስችላታል:: በተጨማሪም የሥራ እድል ፈጠራን ያበረታታል:: ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ተጠቃሚ ይሆናሉ:: ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድሎች መጨመር ያስችላል:: የውጭ ኢንቨስትመንትንም ያጠናክራል::

 

ስጋቶች

አጠቃላይ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና  ሀገራት የውጭ ውድድር ጫና ይፈጥርባቸዋል:: ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ያሉ ሀገራት ገበያውን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ::

በኢኮኖሚ ደከም ያሉ ሀገራት የጠንካራዎቹን ሀገራት ምርቶች የሚገዳደር ምርት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል:: አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ካልተዘጋጁ ሊጎዱ ይችላሉ:: የመሠረተ ልማት እጥረት፣ የሎጂስቲክስ፣ የኀይል እጥረት ሌላው ለቀጣናው ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል::

የንግድ ደንቦች፣ የጉምሩክ ሂደቶች እና የጥራት መመዘኛ (standards) ማሻሻያ  ካልተደረገባቸው ችግሮች ሊፈጥሩ ይችላሉ:: ታዲያ እነዚህን ተግዳሮቶች የሚያስቀሩ ሥራዎች በፍጥነት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ሊከናወኑ ይገባል::

አፍሪካ ሕብረትን፣ ኢትዮ ቻምበርን፣ የዓለም ንግድ ድርጅትን በዋቢነት ተጠቅመናል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here