አድዋ ለምን አልተደገመም?

0
119

ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ አምስት ዋና ዋና ግቦች ነበሩት:: ኢጣሊያ በአድዋ ጦርነት የደረሰባትን ሽንፈት እና ታሪካዊ ጠባሳ በአዲስ ድል በማደስ የሮማን ታላቅነት መመለስ፣ ሰፊና ለም መሬት በመያዝ የጣሊያንን ኢኮኖሚ ማዳበር፣ ኢትዮጵያን ከጣሊያን ቅኝ ግዛቶች (ኤርትራ እና ሶማሊያ )ጋር በመቀላቀል የጣሊያን የምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት በመመስረት የጣሊያን ህዝብን ማስፈር፣ ለጣሊያን ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ እና ገበያ ማግኘት እንዲሁም ሞሶሎኒ የጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ልዕልና እና መሪነት ብቻ ያለበት ከሊግ ኦፍ ኔሽን የተለየ አዲስ በይነ መንግስት ለመመስረት ያሰበው እቅድ የፈረንሳይን እና ጀርመንን ድጋፍ ካለማግኘቱ በተጨማሪ በጣሊያን የውስጥ ችግር ተፈጥሮ ስለነበር የህዝቡን ትኩረት ለመቀየር፣ ለማደናገር እና በዓለም ህዝብ ዘንድ ዝናን ማትረፍ የሚሉት ግቦቹ ነበሩ።

ከላይ የተጠቀሱትን ግቦች ለማሳካትም ጣሊያን 40 ዓመት ሙሉ የዲፕሎማሲ፣ የስነ ልቦና እና ወታደራዊ ዝግጅት ስታደርግ የቆየች ሲሆን በአንጻሩ ኢትዮጵያ እዚያው አድዋ ላይ ተተክላ እንደቀረች ነበር:: በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ የአድዋ ድል ሳይደገም ቀርቷል:: ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት የታሪክ ጸሐፊዎች ለአብነት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እና ካፒቴን አዶልፍ ፓርላሻክ ያስቀምጣሉ::

አድዋ ላይ ድል የተደረገችው ጣሊያን የወልወል ግጭትን ምክንያት በማድረግ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀች:: በወቅቱ የኢትዮጵያ ገዥ የነበሩት ዐፄ ኃይለሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ መተማመናቸው እና የዓለም ሀገራት ይረዱናል በሚል ጦራቸው ከማጥቃት ይልቅ እዲከላከል ትዕዛዝ መስጠታቸው  ዋና ከሚባሉት ስህተቶች ውስጥ መሆኑን ዘ ሀበሻ ኦዶሴ በሚለው መጽሐፉ ካፒቴን አዶልፍ ፓርላሳክ ይመሰክራል:: አልፍሬድ ፓርለሳክ የራስ ካሳ ኃይሉ የጦር አማካሪ እና በጦርነቱ ተሳታፊ እንደነበር ልብ ይሏል::

በጥቅምት ወር 1928 ዓ.ም የጣሊያን ጦር በዘጠኝ ክፍለ ጦር ተደራጅቶ 250,000 የነጭና 150,000 ከሊቢያ፣ ከሶማሊያና ከኤርትራ የተሰበሰቡ አስካሪዎችን በማሰለፍ በሰሜን በማርሻል ኢሚሎ ደቦኖ፣ በደቡብ ምስራቅ በማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ እየተመሩ ከሁለት አቅጣጫ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ለመያዝ ተንቀሳቀሱ:: የዓድዋን አይነት ሽንፈትም ለማስቀረትና ዘመቻውን በማያዳግም ሁኔታ ለማከናወን በሰሜን 300 በደቡብ ምስራቅ 100 የጦር አውሮፕላኖች በመጠቀም ጥቃቱን ጀመሩ::

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለጦርነት የጠነከረ አቅም አላደራጀችም፤ ጣሊያን ወረራውን እንደ ጀመረች የኢትዮጵያ ጦር መልሶ ከማጥቃት ይልቅ እንዲያፈገፍግ በመታዘዙ ገና ከመነሻው ጦርነቱ ወደ አንድ ወገን ያደላ ነበር:: ይህም ንጉሡ የጣሊያንን ወራሪነት ለዓለም መንግስታት ለማሳየትና ለማስቀጣት ከማሰባቸው የተነሳ ነበር:: ሆኖም ግን ወረራውን ተከትሎ ሊግ ኦፍ ኔሽን በሁለቱም ሀገራት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በመጣል አድሏዊ ውሳኔውን ሲያስተላልፍ፣ አጋዥ እንደሌላት የተረዳችው ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል ጦርነቱን በአዋጅ ጀመረች::

በጦርነቱ የጣሊያን ትልቁ አቅም የጦር አውሮፕላኖቿ ሲሆኑ የመርዝ ጋዝም ጥቅም ላይ ማዋሏ ሌላው ለኢትዮጵያዊያን መጥፎ አጋጣሚ፤ ለጣሊያን ግን ብልጫ መውሰጃ ሆነ። ኢትዮጵያዊያን የጦር አውሮፕላኖቹን ድብደባ፣ የመርዝ ጋዙን ጥቃት እና ሌሎች አደጋዎችን ለመከላከል በቂ እውቀት እና ዝግጅት አልነበራቸውም:: ለአብነት ከአውሮፕላን ድብደባው ለመጠበቅ ምሽግ እንዲቆፍሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሲነገራቸው አሻፈረኝ ይሉ ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ የሚደበቅ ፈሪ ነው በሚል ምክንያት ነበር። ይህ ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ አልነበረም:: ሌላው ከመርዝ ጋዝ ለመጠበቅ ብጣቂ ጨርቅ ላይ መስታውት በመለጠፍ የመርዝ ጋዙን መከላከል የሚችሉ ይመስላቸዋል:: ደረጃውን የጠበቀው የመርዝ መከላከያ ጭምብል ሜካኒካል የሆነ ማጣሪያ እንዳለው እና እንዴት እንደሚሠራ ምንም እውቀት አልነበራቸውም::

በመድፍ እና በዘመናዊ ጠመንጃ ኢትዮጵያዊያን ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር:: አንዳንድ የጦር አመራሮች በአድዋ ድል የማረኩትን መድፍ ይዘው ለሁለተኛው ወረራ ለመሰለፍ የሞከሩ ነበሩ:: መድፎቹ ሙዚየም መቀመጥ የነበረባቸው ናቸው:: ጠመንጃን በተመለከተ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሰራዊት ጠመንጃ የለውም፤ ይልቁንም በጦር እና ጎራዴ ይዋጋ ነበር፤ ይህም ሆኖ ጀግንነት አላነሰውም፤ ታላቅ ጀብዱም ፈጽሟል፤ ነገር ግን የጣሊያን አውሮፕላኖች፣ ታንኮች፣ መድፎች እና የሚጣለው የመርዝ ጋዝ  ለድል አላበቃው አለ።

በወቅቱ በጦር ሰራዊት ደረጃ የኢትዮጵያ ጦር 300 ሺህ የሚደርስ ነበር። ከጥቂቶቹ በስተቀር ጠመንጃ እና ጥይቱን ወታደሮቹ በራሳቸው የሚያመጡት ነበር” ሲሉ ያትታሉ፤ ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1855-1991 በሚለው መጽሐፋቸው:: በወቅቱ ጦሩ በአራት ራሶች የሚመራ ሲሆን የሰሜኑን ራስ እምሩ ኃይለስላሴ፣ በጎጃም እና በጌምድር ራስ ካሳ ኃይሉ፣ ራስ ስዩም መንገሻ እና በመሀከል ራስ ሙሉጌታ ይገዙ በምስራቅ በኩል ተሰልፈው ነበር:: በአራቱ ራሶች መካከል የነበረው የላላ ግነኙነትና ግላዊ ተፎካካሪነት የጣሊያን የጦር መሳሪያና የአየር ላይ የበላይነት ተደምሮበት ጦርነቱ በጣሊያን የበላይነት እንዲካሄድ አደረገው::

ከዚህ ባሻገር አሁን ግምቱ ይውጣ እንጂ በወቅቱ ንጉሡን ጨምሮ ሁሉም የጦር አመራሮች የሰራዊታቸውን ቁጥር አያውቁትም ነበር:: ይህም ሰራዊቱን ለማንቀሳቀስ፣ ለማዘዝ እና ለመምራት ፈተና ፈጥሮ ነበር::

በሌላ በኩል ጣሊያኖች የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገራት ሰላዮችን ሰግስገው በማስገባት የተለያዩ ሚስጥሮችን በብዛት ማግኘት ችለዋል:: በዚህ ስለላቸው ጣሊያኖች የኢትዮጵያን እያንዳንዷን መውጫ እና መግቢያ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር:: ንጉሡ እና ከፍተኛ መኮንኖቻቸው የሚለዋወጡትን የሬዲዮ መልዕክት በቀላሉ ይጠልፉም ነበር:: የራስ ካሳ ኃይሉ አማካሪ ፓርለሳክ፤ ራስ ካሳ-ከንጉሡ ጋር የሚያደርጉትን የመልዕክት ልውውጥ ጣሊያኖቹ ይጠልፉታል፤ ማቆም አለብዎት ሲላቸው “አይዞህ ንጉሤ እና እኔ የምናወራበት የራሳችን ቋንቋ አለን” እንዳሉት እና የኋላ ኋላ የመልዕክት ልውውጣቸው ጣሊያኖች እጅ እንደገባ ማረጋገጡን ጽፏል:: የኢትዮጵያ ጦር ሽንፈት በደረሰበት የማይጨው ጦርነ፤ የጣሊያን ጦር የኢትዮጵያ ሰራዊት መቼ እና እንዴት ጥቃት ለመሰንዘር እንደተዘጋጀ መረጃ ነበረው፤ ይህንንም ንጉሡ ካደረጉት የሬዲዮ እና የደብዳቤ ልውውጥ ያገኘው ነው:: የጽሑፍ መልዕክት ይዘው የሚጓዙትን መልዕክተኞች ባንዳ ሽፍቶችን በማሰማራት መልዕክቱን አስነጥቆ እጁ ያስገባም ነበር::

ጣሊያኖች በተለያዩ የኢትጵያ ከተሞች ቆንጽሎችን በመክፈት በዚያ ሰላዮችን በማሠማራት ሲዘጋጁ ቆይተዋል:: በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት፣ በተቋማት፣ በነጋዴ እና ጋዜጠኛ መልክ እና በሌሎች ሰላዮችን አሰማርተው መረጃ ይሰበስቡ ነበር:: የሁሉም ቆንጽላ ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች ወታደሮች እና የጦር አመራሮች ነበሩ::

ማርሻል ባዶጋሊዮ የማይጨው ድል ከቀናው በኋላ ጉዞውን በደሴ በኩል በመቀጠል ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም  ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ:: ጣሊያን ግንቦት 23 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ግዛት መሆኗን በይፋ አወጀች:: ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥቷ አማካይነት ላቀረበችው የድረሱልኝ ጥያቄ የዓለም መንግሥታት ጆሮ ነፈጓት:: ይባስ ብለው በኢጣሊያ ላይ አስተላልፈውት የነበረውን ማዕቀብ በነሐሴ ወር 1928 ዓ.ም አነሱ:: በዚህም ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል ተቆጣጥራ እንድትቆይ አስችሏታል::

በቤኒቶ መሶሎኒ የተመራው የጣልያን ጦር በዚህ በሁለተኛው የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ወቅት ፈፅሟል የተባለው የጦር ወንጀል፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመ ጥቃትና በሰብዕና ላይ የተፈፀመ ወንጀል ከወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰባት ከመቶው ላይ ጉዳት አድርሷል::

በጦርነቱ ከ250 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ ከወራሪው የጣሊያን ጦር ወገን ደግሞ 208 ሺህ ወታደር ሙትና ቁስለኛ ሆኗል::

 

 

ሳምንቱ በታሪክ

ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት

የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጥር 3 ቀን 1893 ዓ.ም አርፈው በደብረ ማርቆስ ተቀበሩ። ንጉሥ ተክለሀይማኖት ከአባታቸው ተሰማ ጎሹ እና ከእናታቸው ምዕላድ ነገዷ በ1843 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ እንደተወለዱ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡

ንጉሥ ተክለሀይማኖት አብዛኛው ህይወታቸው በጦርነት የተሞላ ነው፡፡ ራስም፣ ንጉስም ሆነው በርካታ ፈተናዎችን አስተናግደዋል፡፡ ራስ እያሉ ከጎጃም የስልጣን ተቀናቃኞቻቸው እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተፋልመዋል፡፡

የቢያፍራዎች ሽንፈት

በናይጄሪያ ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ጥር 4 ቀን 1982 ዓ.ም በቢያፍራ ወገኖች ተሸናፊነት አከተመ።

ናይጄሪያ ከ50 ዓመታት በፊት ነፃነቷን ብትቀዳጅም ብሔራዊ አንድነቷ ስጋት የተደቀነበት ገና 10ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ለማክበር ሳትበቃ ነበር፡፡ የቢያፍራው የመገንጠል ንቅናቄ የቢያፍራውን ጦርነት ወለደ፡፡

ከሦስት ዓመታት ያህል ደም አፋሳሽና እልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ የናይጄሪያ ፌዴራላዊ ኃይል ባለድል ሆነ፤ የቢያፍራ ተገንጣዮች እጅ ሰጡ፡፡

ምንጭ፡- ብሪታኒካ

 

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here