የትንሿ ሀገር ስኬታማ የትምህርት ሥርዓት

0
145

ትንሿ ሀገር ሲሼልስ በሞቃታማ የአየር ንብረቷ፣ በበርካታ ደሴቶቿ፣ በተለያዩ የባሕል ስብጥሮቿ፣ ኩልል ባሉ የውኃማ ከባቢዎቿ እንዲሁም በጎብኚዎች ተመራጭነቷ ትታዎቃለች:: በብዙ መገለጫዎቿ ስኬታማ ሀገር ይሏታል:: ትምህርት ደግሞ አንደኛው ነው::

እኛም ኢትዮጵያ ቢኖራት ብለን ስለተመኜነው የትንሿ ሀገር ስኬታማ የትምህርት ሥርዓት ውጤታማነት ልናስነብባችሁ ወደናል::

የሲሼልስ ሥርዓተ ትምህርት ስኬት በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ የመጣ ነው፤  የትምህርት ተደራሽነት፣ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ እና የትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው የተሠሩ ዋና ዋና ሥራዎች ናቸው::

በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ የተካሄዱት የትምህርት ማሻሻያዎች በሁሉም ደረጃ የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት፣ የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፎችን በመገምገም እና የትምህርት መዋቅርን በማስተካከል በትኩረት የሠራችበት ጊዜ ነው። በተለይ ከ1983 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ውስጥ ቀጣይነት ያላቸው ማሻሻያዎችንና የትምህርት ቁጥጥር ማዕቀፎችን፣ የመምህራን የሙያ ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን እና የጥራት ማረጋገጫ ዘዴዎችን በማዘጋጀትና በመተግበር ከፍተኛ ሥራ ሠርታለች። ይህ ጊዜ ለሲሸልስ የትምህርት ለውጥ ፅኑ መሠረት የተጣለበት ተደርጎ ይወሰዳል::

በመስከረም ወር 2001 ዓ.ም ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሲሼልስ (University of Seychelles) የተባለውን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መሠረተች:: የዚህ ዩኒቨርሲቲ መመሥረት ደግሞ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ እንዲሻሻል አድርጓል፤ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የትምህርት ዕድልን በመስጠት፣ ጥናትና ምርምርን በማበረታታት እና ለሀገር ዕድገት አስተዋፅኦ በማድረግ በሲሸልስ የትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ አሻራ አስቀምጧል::

የየኒቨርሲቲው መመሥረት በሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ላይ የነበሩትን ክፍተትቶች በቅድመ እና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች በመሙላት ጉልህ አስተፅኦ አበርክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በሥሩ ባሉ የትምህርት እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጥናትና ምርምር ተቋሞቹ በኩል ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና በትምህርት እና በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዘላቂ ልማትን ለማምጣት አስተዋፅኦ አድርጓል።

ሲሸልስ አሁን ለደረሰችበት ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት መሠረቱ የሀገሪቱ የ1969 ዓ.ም የትምህርት ፖሊሲ ነው:: በዚህ ፖሊሲዋ ሦስት መሠረታዊና ለትምህርት የለውጥ ምሰሶ የሆኑ መርሆዎችን አፅድቃለች:: እነዚህም ትምህርት ለሁሉም፤ ትምህርት ለህይዎት እና ትምህርት ለግለሰብና ለሀገር ዕድገት የሚሉ ናቸው::

የትምህርት ለሁሉም መርህ ሁሉም ዜጎች መማራቸው ለሀገር ዕድገት የሚኖረውን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዜጎች እኩልና ጥራት ያለው የትምህርት እድል እንዲያገኙ ያለመ ነው:: የትምህርት ለህይዎት መርህ ትምህርት በእያንዳንዱ ግለሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ ጉልህ ስለሆነ ሁሉም ማህበረሰብ መሠረታዊ ትምህርትና የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ አቅዶ መሥራትን የሚጠይቅ ነው::

የትምህርት ለግለሰብና ለሀገር ዕድገት መርህ እሳቤ ደግሞ የተማረ ግለሰብና ማህበረሰብ ለሀገር ዕድገት የሚኖረውን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዜጎች በአካል፣ በአዕምሮ፣ በሞራልና በአስተሳሰብ ከፍ እንዲሉ ጥራት ያለው የትምህርት ዕድል ሊያገኙ ይገባል የሚል ነው::

ሲሸልስ እነዚህን ሦስት መሠረታዊ መርሆዎች ለማሳካት በመጀመሪያ ደረጃ የተከተለችው ዞናዊነት የተሰኜ የትምህርት አሠራርን መተግበር ነበር:: የዚህ ትግበራ መርህ ሁሉም ህጻናት በሚኖሩባቸው ወረዳዎች የትምህርት ዕድል ማግኜት እንዲችሉ የሚያደርግ አሠራር ነው:: ይህ አሠራር ትምህርት ቤት በሌለባቸው አካባቢዎች ለመተግበር ፈታኝ ቢሆንም ቀድሞውኑ ስለታሰበበት ትምህርት ቤት በሌለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ህፃናት የሀገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር በመረጣቸው ሌሎች ወረዳዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ይደረጋል::

አሠራሩ ትምህርት ቤት በሌለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህፃናትን ከትምህርት ውጭ እንዳይሆኑና የትምህርት ኢፍትሐዊነትን በማስቀረት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል:: ለዚህ ሲባል ወደሌሎች አካባቢዎች ለሚሄዱ ህፃናት ሙሉ የትምህርት ወጪ በመንግሥት የሚሸፈን ነው::

ሌላኛው ሲሸልስ የወሰደችው የነፃ ትምህርት ለሁሉም የሚለው የፖሊሲ እርምጃ ሀገሪቱ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንድታስመዘግብ አግዟታል፤ ይህ ፖሊሲ ምግብን፣ የደንብ ልብስን (ዩኒፎርም) እና ትራንስፖርትን ጨምሮ ለትምህርት የሚያገለግሉ ሁሉም የትምህርት ቁሶች ለተማሪዎች በነጻ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ነው::

ሲሸልስ የትምህርት ዘርፏን ውጤታማ ለማድረግ የተከተለችው ሌላኛው ፖሊሲ ደግሞ የህጻናት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ኣመታት ትምህርት ግዴታ እንዲሆን ማድረግ ነው:: በዚህም ምክንያት የትኛውም ህፃን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆን አይፈቀድለትም:: ይህንንም በትክክል ለመተግበር ከፖሊሲ ባሻገር የቅጣት ሕግ አውጥታ ተግብራለች:: ይህ የቅጣት ሕግ አንድ ህፃን ያለ በቂ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆኖ ከተገኜ የህፃኑ ወላጆች አንድ ሺህ ሩፒ (የሲሸልስ ገንዘብ) ተቀጥተው ለሦስት ወራትም በእስር እንዲቆዩ የሚያስገድድ ነው::

የትምህርት መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ደግሞ ሀገሪቱ ያከናወነችው ሌላኛው ተግባር ነው፤ ሀገሪቱ በተለይም በ1974 ዓ.ም ከፍተኛ በጀት በመመደብ በርካታ ትምህርት ቤቶችንና የሳይንስ ቤተ ሙከራዎችን ገንብታለች:: ይህም በርካታ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣትና ተማሪዎቿም በቂ በሆኑ የመማሪያ ክፍሎች በተግባር የታገዘ ትምህርት እንዲማሩ እግዟታል::

ሲሼልስ  በ1975 ዓ.ም የጀመረችው የፖሊ ቴክኒክ ስልጠናም ሲሸልስ በትምህርቱ ዘርፍ ጉልህ ውጤት እንድታስመዘግብ አስችሏታል:: የፖሊቴክኒክ ተቋሙ ምሥረታ የሀገሪቱን የትምህርት ዘርፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሳደገ ነው:: ዋና ዓላማውም መምህራንን ማሰልጠንና በልዩ ልዩ ተግባራዊ የሙያ መስኮች የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ነው::

ሲሼልስ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ የማስተማር ሳይንስ (የፔዳጎጂ) ተቋም በ1973 ዓ.ም አቋቁማለች:: ተቋሙ ከሀገሪቱ ፍላጎት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች በማዘጋጀት እና የመምህራን የሥራ ላይ ሥልጠናን የመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው ነበር። በርካታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንንም ክሪኦል በተሰኜው የሀገሪቱ ቋንቋ በማሰልጠንና ቁጥጥር በማድረግ የፔዳጎጂ ተቋሙ ለትምህርት መሻሻል ከፍተኛ አበርክቶ ነበረው::

በተጨማሪም በ1974 ዓ.ም በሁሉም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ-መጻሕፍትን ገንብታ ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጋለች:: በየአካባቢው የሚገኙ ትናንሽ ቤተ-መጻሕፍትንም ገንብታ ለአገልግሎት አብቅታለች:: ይህም ለትምህርት ሥራው ውጤታማነት ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል::

የመምህራን ውጤታማነት ደግሞ ለሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ቁልፍ ምክንያት ነው። መምህራን ከሥራ በፊትና በሥራ ላይ የተለያዩ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ፔዳጎጂ የተሰኜ ተቋም በመመሥረት የመምህራንን አቅም አሳድጋለች::

ለመምህራን የሚሰጡ ስልጠናዎችም ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል:: የስልጠና ሥርዓቱ ከመምህራን ምዝገባ ጀምሮ፣ ለስነ ምግባርና እና ሙያዊ ዕድገት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል:: ሀገሪቱ ሙያዊ አቅምን ለማሳደግ ከምትሰጠው ስልጠና ባሻገር መምህራንን ለመሳብ ለመምህራን የሚሰጡ አገልግሎቶችና ጥቅማጥቅሞች በየጊዜው እንዲሻሻሉ ታደርጋለች::

በሲሼልስ የተማሪ መምህር ጥምርታ እንደየ ትምህርት እርከኑ ይለያያል:: ለምሳሌ በቅድመ መደበኛ ትምህርት እርከን አንድ መምህር ከ16 እስከ 17 ተማሪዎችን ብቻ ያስተምራል:: በአንደኛ ደረጃም ከዚህ የራቀ አይደለም:: እንደየ ትምህርት ቤቶች የሚለያይ ሆኖ በክፍል ከፍተኛው የተማሪ ቁጥር 24 ብቻ ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ቢሆን የተማሪዎች ቁጥር በአንድ ክፍል ውስጥ አነስተኛ ነው:: እንደየ ትምህርት ቤቶችና አካባቢዎች የሚለያይ ሆኖ በአንድ ክፍል የሚማሩት ተማሪዎች እጅግ ከፍ ቢል ከ40 አያልፍም:: ይህ ደግሞ ለትምህርት ጥራት ቁልፍ ድርሻ አለው::

በትምህርት ዘርፏ ላይ ለበርካታ አመታት የተለያዩ ስርነቀል ስልቶችን የተገበረችው ሲሸልስ በ2006 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን በማግኜት የዩኔስኮን የትምህርት ለሁሉም ግብ ያሳካች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ሆናለች:: 96 ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆኑት የሲሸልስ ዜጎች ማንበብና መፃፍ የሚችሉ ናቸው:: ትምህርት በሀገሪቱ ነፃ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው:: ጥራትም የሀገሪቱ ትምህርት መገለጫ ነው::

ትምህርት በየትኛውም ተፅዕኖ ስር እንዳይወድቅ ለማድረግ በሀገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር እና በትምህርት ዘርፍ ከሚSራው ኮመን ዌልዝ ኦፍ ለርኒንግ (Common Wealth of Learning) ጋር በትብብር ለመስራትና የመምህራንን ስልጠና ወደ ዲጅታል መንገድ ለመቀየር ትብብር ጀምራለች:: የመምህራን ልማት እና የማስተማር ስልት በክፍል ውስጥ ፈጠራን በሚያበረታታ መልኩ እንዲሆንም እየሠራች ነው::

በብዙ ጥረት የተገኜው የዚች ሀገር ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት በእኛም ሀገር እንዲኖረን ተመኜን::

የአፍሪካ ሕብረት፣ የሲሼልስ ትምህርት ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው::

 

መረጃ

የንባብ ክህሎት የማሳደጊያ ስልቶች

  • ዘወትር ማንበብ

ዘወትር ቀን በቀን የማንበብ ልምድ ይኑራችሁ።  በእያንዳንዱ ቀን  የምታነቡበትን ጊዜ አስቀምጡ።

  • ትክክለኛ የንባብ ቁሳቁሶችን ምረጡ

ከእድሜ እና ከፍላጎት ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ወይም የሚጣጣሙ የንባብ ቁሳቁሶችን ምረጡ። ቀለል ያሉ መጽሐፍት ወይም ጽሑፍ በመምረጥ መጀመር፤ ከዚያም በሂደት የመረዳት ችሎታችሁን እያያችሁ ውስብስብ የሆኑ መጽሐፍትን እና ፅሁፎችን በማንበብ እራሳችሁን ፈትኑ።

  • መዝገበ ቃላት መጠቀም

አውዳዊ ፍችን በመጠቀም አዳዲስ ቃላት ተማሩ። ለየት ያሉ ቃላቶች በሚገጥሙ ጊዜ የመዝገበ ቃላት መጽሐፍ ውስጥ በመፈለግ እና በዐረፍተነገር ውስጥ እየተለማመዳችሁ ተጠቀሙባቸው።

  • የመረዳት ችሎታን ማሳደግ

አንድን ጽሑፍ ከማንበብ በፊት ፣ ስታነቡ ወይም ካነበባችሁ ቡኋላ ስለ ጽሁፉ ምንነት እና በርዕሱ ላይ ያላችሁን እውቀት እና ግንዛቤ እራሳችሁን ጠይቁ። ስላነበባችሁት ጉዳይ  ሰዎች ጋር ተወያዩ፣ ማጠቃለያ ስጡ እንዲሁም የራሳችሁን ሃሳብ እና ምልከታ አስቀምጡ።

ግእዝ በአማርኛ

 

ትማልም – ትላንት

ጌሰም –  ነገ

ናሁ –  አሁን

ይእዜ –  ዛሬ

ድሕረ ጌሠም –  ከነገ በኋላ

ቅድመ ትማልም – ከትላንት በፊት

(አስፋው ሙቀት)

በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here