ኢትዮጵያ ሰፊ እና ሁሉን አብቃይ ለም መሬትን ከምቹ የአየር ንብረት ጋር አጣምራ ይዛለች፡፡ ይህም ምቹ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት (ገንዘብን፣ ጉልበትን እና ዕውቀትን ተጠቅሞ የማልማት ሂደት) ልዩ ትኩረት እንድትሰጥ ይጋብዛል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የእርሻ መሬት እና ምቹ የአየር ሁኔታ አስተማማኝ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን ያስቻላት ሲሆን ይህንን አስቀጥሎ ለመጓዝም በተለያዩ ክልሎች የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትርያል ፓርክ ተገንብቶ ሥራ ተጀምሯል። ኢንቨስትመንት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ምሰሶ ነዉና ዘርፉን ማነቃቃት ደግሞ ቀዳሚ ጉዳይ ሊሆን ይገባል:: በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እሴትን ጨምራ ለማቅረብ፤ ለዚህም ሁሉንም ጥሬ ግብዓቶች ተጠቅመው ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ሁኔታዎችን እያመቻቸች ትገኛለች፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በግጭት ውስጥ የሚገኘው የአማራ ክልል መንግሥትም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሰላማዊ አማራጮች እንዲፈጠሩ እያከናወነ ካለው ሥራ ጎን ለጎን የክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ አሁን ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገርም ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት የሚያስፈልግ ሲሆን ለኢንቨስትመንት ዕድገት መሠረት ከሆኑት መካከልም ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋነኛዉ በመሆኑ ለሰላም የሚከፈለዉ ዋጋ ከሁሉም የበለጠ ሊሆን ይገባዋል ፡፡ ባለሀብቶች በሚያለሙበት አካባቢ እምነት ኖሯቸው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሠማሩ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራው በዘላቂነት እንዲቀጥል፣ ወጥ የሆነ ምርታማነትን በማረጋገጥ በምርት አቅርቦት ሊያጋጥም የሚችልን የኑሮ ውድነት ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።ይሁንና በአሁኑ ወቅት በተገኘዉ አንጻራዊ መረጋገት እና ሰላም አማካኝነት በችግር ውስጥም ሆኖ ስኬቶች እንደተገኙ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አረጋግጧል። ለአብነትም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን፣ ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ምርት (ኤክስፖርት) መጠን መጨመርን፣ በተኪ ምርት የተመዘገበውን ውጤት እና በማምረት አቅም የተመዘገበውን አበረታች ዕድገት በመጥቀስ ቢሮዉ የተገኘዉን እድገት የጠቆመ ሲሆን አሁንም ከዚህ በበለጠ ለዉጥ ለማምጣት ይቻል ዘንድ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል ፡፡በመሆኑም ወደሚፈለገዉ ስኬት ለመድረስ እንችል ዘንድ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል።
በዚህም መሠረት ወደ ክልሉ የሚመጡ ኢንቨስተሮች ወይም ባለሀብቶችም መሬትን ለረጅም ጊዜ አጥሮ ከማስቀመጥ እና ላልተፈለገ ዓላማ ከመጠቀም በመዉጣት ክልሉን በማልማት ሕዝብ እና መንግሥት የጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡
የክልሉ መንግሥትም ኢንቨስትመንቱ በተሳለጠ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ማነቆ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ለምሳሌ የቢሮክራሲ እና የኃይል አቅርቦት ችግሮችን መፍታት፣ መመሪያዎችን እና ደንቦችን ማሻሻል፣ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የአካባቢ ፀጋን መለየት፣ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የመሬት አቅርቦት ሥርዓቱን ማሻሻል፣አገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ ማድረግ፣አሠራሮችን በየወቅቱ መፈተሽ እና ከወቅቱ ጋር በማገናዘብ ተለዋዋጭ አሥራሮችን በመፍጠር እና በመሳሰሉት ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል።
በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


