አባ ቸኮል ቢሆነኝ በባህር ዳር ዙሪያ በሚገኘው ደብረ ማርያም አካባቢ የሚኖሩ እድሜያቸውን ሙሉ በሥራና በአገልግሎት ያሳለፉ ታታሪ አባት ናቸው። በታህሳስ 3 ቀን 1936 ዓ.ም. የተወለዱት አባ ቸኮል በአሁኑ ወቅት በ82 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም አሁንም ድረስ በግብርናውና በንቃት በመሳተፍ ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ አርአያ እየሆኑ ይገኛሉ።
አባ ቸኮል የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ግብርናንና መንፈሳዊ ትምህርትን አጣምረው በመማር ነው። አባታቸው ጠንካራ ገበሬ ስለነበሩ የግብርናን ሙያ በሚገባ አስተምረዋቸዋል። በ1955 ዓ.ም. የክህነት ማዕረግ የተቀበሉት አባ ቸኮል ለብዙ ዓመታት በቤተክርስቲያን ውስጥ በቄሰ ገበዝነትና በምክትል ሊቀመንበርነት አገልግለዋል። በደብረ ማሪያም ገዳም በኃላፊነት በቆዩበት ዘመናቸውለቤተክርስትያን የተለያዩ ለውጦችን አስገኝተዋል። ካህናት ደሞዝ አይከፈላቸውም ነበር፤ እርሳቸው ደመወዝ እንዲጀመርላቸው አድርገዋል። ምንም እንኳን የሥራ ጫናና ቤተሰብን የማስተማር ኃላፊነት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ከ4ኛ ክፍል እንዳይቀጥሉ ቢያስገድዳቸውምየዕውቀት ፍላጎታቸው ግን አልቀነሰም ነበር። ልጆቻቸውን በማስተማር ለከፍተኛ ደረጃ በማድረስ የተበቀሉት ይመስላል።
ሕይወታቸው በትጋትና በራስ መተማመን ከተሠራ ዕድሜ ለሥራ እንቅፋት እንደማይሆን ያሳያል። ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጎን ለጎን እርሻ በማረስ፣ አሳ በማስገር፣ አትክልትና ፍራፍሬ አዳቅሎ በማልማት ለሌሎች አርአያ ናቸው። ዘመናዊ የዓሳ እርባታ፣ በዘመናዊ ንብ እርባታ፣ ቋሚ ዛፎችን እንዲተከሉ በማድረግ፣ በእግረ መንገድም ጣና ዳር ያለውን ማሳቸውን ለመዝናኛ ሎጅ በማዘጋጀት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ እድሜ ያልገደባቸው ታታሪ ሰው ናቸው። በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሞዴል አርሶ አደርነት እውቅናዎችን አግኝተዋል። የሕይወት ታሪካቸው፣ ሁልጊዜም ለአዲስ ዕውቀትና ለሥራ ዝግጁ መሆንን ያስተምራል እና እኛም የበኩር እንግዳችን አድርገናቸዋል።
አባ ቸኮል ከቤተክህነት አገልግሎትዎ ጎን ለጎን በግብርና ሕይወትዎ የጥምር ግብርና ተግባሪ ነዎት እና የግብርና ስራዎን በተመለከተ ልምድዎን ያጋሩን?
አባታችን ጠንካራ ገበሬ ስለነበረ፣ በልጅነታችን የግብርና ሥራን በሚገባ አስተምሮናል። የቤተ ክርስቲያን ትምህርቴን እየተከታተልኩ ጎን ለጎን ግብርናውን እየሰራሁ አባቴን አግዝ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግብርናውንና አሳ የማስገር ሥራን አጣምሬ እሠራለሁ። ጠዋት እስከ 6 ሰዓት ድረስ አርሳለሁ፤ ከዚያም አሳ አሰግራለሁ። ማታም እንዲሁ ተመልሼ በሬዬን ጠምጄ እሠራለሁ፤ በጣም ማልጄ ያገኘሁትንም አሳ ልጆቼ እንዲሸጡት እሰጣቸዋለሁ። ግብርናውን ግን ከቤተሰቤ ጋር ቀኑን ሙሉ ነው ስሰራ የምውለው።
ከእርሻው እና አሳ ማስገር ስራው ጎን ለጎን አትክልት እና ፍራፍሬ ጀመርኩ። በአካባቢው በወቅቱ ማንም ስለአትክልትና ፍራፍሬ የሚያውቅ አልነበረም እኔ ነበርኩ የጀመርኩት። ስራውን በጎመን ማልማት ጀመርኩ። ጎመን ዘሩን አዳቅየ ውሃ በባልዲ እየተሸከምን እያጠጣን አለማነው፤ ሰዎችንም እያስተማርኩ በመስራት እኔ የመጀመሪያ ተጠቃሚ ሆንኩ። ከዚያ ቀስ እያለ ሰው ጎመን ማልማት ጀመረና ጥቅል ጎመን በቃ ተስፋፋ፣ ተለመደ። ከእኛ አልፎም ወደ አጎራባች ቀበሌዎች ሁሉ እየተወሰደ ጎመን ማልማት ተለመደ። አንድ ባኮ የጎመን ዘር በ60 ሳንቲም ገዝቼ ነው ማዳቅለው፡፡ እናም በ60 ሳንቲም የተከልሁት ዘር ሁለት መቶ ብር ምርት ያስገኘኝ ነበር። እንዲያ እያደርኩ ስሰራ ጥቅሙን ከእኔ በተግባር እያዩ ብዙዎች ሰርተው ተጠቀሙ።
በባህርዳር እና ሌሎች አካባቢዎች የብርቱካን ተክል ማዳቀል የጀመሩት እና እንዲስፋፋ ያደረጉ እርስዎ ነዎት ይባላል እና ስለዚህ ጉዳይ ይንገሩን እስኪ?
አዎ! ከዚያ በኋላ ወደ ቋሚ አትክልት ስራ ገባሁ። ብርቱካንን ያስጀመርኩት እኔ ነኝ። ሌሎችን እየሰራሁ አትክልት እና ፍራፍሬ ወደ ማልማት ብገባ አዋጪ መሆኑን ተገንዝቤ የብርቱካን ዘር ከአንዳሳ የእርሻ ምርምር አምጥቼ ከወረዳው ግብርና ባለሙያ ጋር አዳቀልኩ። በዓመቱ ወደ ስድስት ያህል የብርቱካን ዛፎች ፀደቁልኝ። በዓመቱ ደግሞ ባለሙያ መጣልኝ እና ሌሎችን አዳቀልን። እንደዚያ እያደረግሁ የማዳቀል ስራውን በየዓመቱ እየቀጠልኩ ስሄድ ከሆነ ጊዜ በኋላ የብርቱካን ዛፎች ተራብተው ተባዙ። የማገኘው ጥቅሙ ትልቅ ነው፤ አትክልት ባይኖር እኮ እርሻው ብቻውን ልጅ ለማሳደግ ነበር። ብርቱካንን የመሰለ ጥሩ ገቢ ያለው የለም። አሁን ብዙ የጎረቤት አካባቢዎች እየጠሩኝ እስከ ተንታ ጪርቆስ፣ እስከ ጎምባጥ ሚካኤል ድረስ ብርቱካን አዳቅያለሁ።
ከዚያ ጎን ለጎን ደግሞ አሳ ማርባት ጀመርኩ።የዓሳ እርባታ ሥራን ለመጀመር የተነሳሳሁት በቴሌቪዥን አንድ ተሞክሮ አይቼ በመነሳሳት ነው። ሥራውን ለመጀመር የወረዳውን ግብርና መመሪያ ጠይቄ፣ ካረባህማ እናስተምርሃለን” የሚል ምላሽ አገኘሁ። የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት መጀመሪያ ላይ ዓሳዎችን ለማርባት የሚያገለግሉ ሁለት የዓሳ መያዣዎችን ሰጡኝ። እናም ማርቢያ ገንዳ ገንብቼ እስካሁን አረባለሁ። ይህ የማርቢያ ቦታ የዓሳ እርባታ ማዕከል ከመሆኑም በላይ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጥተው ምርምር የሚያካሂዱበትና ትምህርት የሚወስዱበት ቦታ ሆኖ አሁን ድረስ ያገለግላል።
“ሁለት ወፍ በአንድ ድንጋይ” እንደሚባለው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ከዓሳ እርባታው የሚወጣው ውሃና ቆሻሻ ወደ ጣና ሐይቅ ገብቶ ሐይቁን ከመበከል ይልቅ በቀጥታ ወደ አትክልት ቦታቸው በመሄድ እንደ ማዳበሪያና መስኖ ያገለግላል። በአሁኑ ወቅት የዓሳ እርባታውን በሁለት ከፍየው አንዱን ለተባዕት ዓሳዎች ሌላውን ደግሞ ለማራቢያነት ለመጠቀም አቅጃለሁ።
እርስዎ ሁሉንም አይነት የግብርና ስራዎች ነው የሚሰሩት ሚስጢሩ ምንድን ነው? ውጤቱስ እንዴት ነው?
እኔ ግብርና ያመጣውን አዲስ ነገር ሁሉ እቀበላለሁ። ለዚያም ነው ተጠቃሚ የሆንኩት። ውጤቱማነቱም አሁን በበሬ የታረሰ እና በትራክተር የታረሰ አንድ አይደለም ዘመናዊ የሆነው ነገር ውጤቱ ጥሩ ነው። አሁን ብትጠይቁ በዚህ አካባቢ ጠቅላላ ያላስተማርኩት ሰው የለም። እኔ በተግባር ስለማደርግ እኔን ነው የሚጠሩኝ። ሌላ ገበሬ አለ እኮ ብዙ- ግን የተሰጠውን በተግባር አያደርገውም። እና ስለዚህ ግብርና ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን ይሰጠኛል። እና በወረዳም በሀገር አቀፍም ብዙ ስልጠናዎችን ሰልጥኛለሁ።
በባሕር ዳር እና ዙሪያዋ በብዙ አካባቢዎች ዛፎችን እንደተከሉ ይነገራል እስኪ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የእርስዎን አስተዋፅኦ ያስረዱን?
ተፈጥሮ ሀብትማ ጥሩ ነው። አንድ ጊዜ ደቡብ ክልል ለስልጠና ሄጄ ነበረ። ሃዋሳ አደርንና ሻሸመኔ ሄድን። ሻሸመኔን አልፈን ወደ ምሥራቅ አርሲ ሄድን። በመንገድ ስንጓዝ ብቻ ስታየው የተፈጥሮ የኮሶ ዛፉ፣ ጥዱ፣ ዝግባው ያለው ተፈጥሮ እና አየሩ ሁሉ ያስገርም ነበር። እና ከዚያ ሄጄ ሰልጥኜ እና ብዙ ልምድ አግኝቼ ተመለስኩ። ከዚያ በኋላ ተመልሼ የዝግባ፣ የግራር፣ የጥድ፣ የእሼ፣ የዶቅማ ችግኞችን እያፈላሁ አሁን እዚህ ከእኔ ግቢ የሌለውን ወደ አሥር ለሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ሰጥቻለሁ። ለዘንዘልማ ሚካኤል፣ ለዘንዘልማ አቦ፣ ተንታ ጪርቆስ፣ ደብረ ጽዮን። እንደገና ደብረ መድኃኒዓለም፣ እንደገና ለአዲሱ ሚካኤል ሰጥቻለሁ።
የተፈጥሮ ሀብት ለትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ነው። ዛሬ አሁን በየቦታው ዛፎቹ አድገው አፍርተው ከጥላነት አልፈው ፍሬ እየሰጡ ሳይ ደስ ይለኛል። ለምሳሌ አንድ ጊዜ ተንታ ጨርቆስ ለቅሶ ሄጄ ሳለሁ ሰዎች ከጸሃይ ለመጠለል በተከልኳቸው ዝግባዎች ስር ቁጭ ብለው አገኘኋቸው። ከዚያም ወደ እነርሱ ጠጋ አልኩና ‘ይቺን ዛፍ ምን አይነት ሰው ተክሏት ይሆን” አልኳቸው። ‘አሃ እንደው የተባረከ ሰው ተክሏት ይኸው እዚህ ላይ ጥላ ሆናን አርፈናል’ አሉ። እኔ መሆኔን ስነግራቸው ‘ኧረ እግዚአብሔር ያቆይህ’ እያሉ መረቁኝ። እና እንደዚህ አይነት ነገሮች ለእኔ ደስታ ይሰጡኛል። አሁን እኛ እድሜያችን ይሄድ ይሆናል ቀጣዩ ትውልድ ግን ይጠቀማል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የምናያቸው፣ የምናርፍባቸው የዛፍ ጥላዎች ቀድመው የነበሩት ሰዎች የተከሏቸው ናቸው።
የልጅ አስተዳደግ ልምድዎን ያጋሩን፣ ልጆችዎ የእርስዎን ፈለግ ተከትለው ይሆን?
አዎ ልጆቼ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩ የተመሰገኑ በየስራቸው የሚሸለሙም ናቸው። ለልጆቻችንን በስርዓት እንዲያድጉ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረግሁ ነበር ያሳደግኋቸው። ለትምህርት ትልቅ ትኩረት እሰጣለሁ እና ሁሉንም ልጆቼን አስተምሬያለሁ። አንዳንዶቹ ማስተርስ፣ አንዳንዶቹ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ዲፕሎማ አላቸው። ትንንሾቹም ደግሞ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።
የስራ ፍልስፍናዎት እና ለስራ ያለዎትን ፍቅር እንዴት ይገልፁልናል?
ብዙ የመንግሥት ሥርዓትና የጊዜ ለውጦችን አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ጊዜ የተረዳሁት ለውጥ የሚመጣው በሥራ ብቻ መሆኑን ነው።”ሰው ሠርቶ መኖር አለበት” የሚል ጽኑ አቋም አለኝ፡፡ በዚህ እድሜየ እርሻን፣ የዓሳ እርባታንና ንብ ማርባትን አጣምሬ በመሥራት ለልጆቼ አርአያ መሆን እፈልጋለሁ። “ዋናው ነገር ሠርቶ መለወጥ ነው፤ እኔ አሁን በዚህ እድሜዬ የምሠራው ለልጆቼ ምሳሌ ለመሆን ነው።”
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


