ልጆችዬ እንደምን ሠነበታችሁ? ሣምንቱስ እንዴት አለፈ? መልካም ልጆችዬ በዚህ ወቅት ትምህርት ከተጀመረ ወራቶች እየተቆጠሩ መሆኑ ይታውቃል፤ ታዲያ እናንተም በየቀኑ የሚሠጣችሁን ትምህርት በአግባቡ በመከታተል በፕሮግራም እያጠናችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን::
ልጆች የአንደኛው ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና እየደረሰ ነው፡፡ በዚህም ወላጆች ልጆች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ እኛም ለልጆቻቸው ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርጉ ወላጅ እናስተዋውቃችሁ፡፡
አቶ ደረበ ሙሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ደረበ ሉሲ እና ሶሊያና የሚባሉ ሁለት ልጆች አሏቸው፡፡ ሉሲ እና ሶሊያና ኢትዮ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ነው የሚማሩት፡፡ ሉሲ ሦስተኛ፣ ሶሊያና አንደኛ ክፍል ናቸው፡፡
አቶ ደረበ ልጆቻቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ መርሃ ግብር ያዘጋጁላቸዋል፡፡ በዚህ መርሃ ግብር መሠረት ትምህርታቸውን ያጠናሉ፡፡ ሌሎች የሚያከናውኗቸውን ተግበራትም ይፈጽማሉ፡፡ መርሃ ግብሩን ዝርዝር በሰሌዳ በመጻፍ ይለጥፉላቸዋል፡፡ ያንን እየተከተሉ ሉሲ እና ሶሊያና የፈተና ዝግጅታቸውን ያካሂዳሉ፡፡
አቶ ደረበ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሳይገቡ ጀምሮ የማንበብ ልምድ እንዲያዳብሩ እና ፍቅር እንዲኖራቸው ራሳቸው እያነበቡ አርአያ ይሆኗቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በዚህም ሉሲ እና ሶሊያና ከፍተኛ የማንበብ እና የማወቅ ፍላጎት አዳብረዋል፡፡ ይህም ለፈተና ዝግጅት ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡
እርስ በርስ መረዳዳት ደግሞ ሌላኛው ዘዴ መሆኑን አቶ ደረበ ይናገራሉ፡፡ በተለይ በእድሜ ትልቋ ሉሲ ትንሿን ሶሊያና ታስጠናታለች፤ ያልገባትን ታስረዳታለች፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ ቤተሰቡ በሙሉ አንድ ላይ በመሆን የተሠሩ እና ያልተሠሩ ተግባራትን ይገመግማል፡፡ በመርሃ ግብሩ መሰረት ተግባራት ሲከወኑ ማበረታቻ ሽልማቶች ለልጆች ይሰጣሉ፡፡ ያልተከወኑ ተግባራት ካሉ ተገምግሞ እንዲስተካከል ይደረጋል በማለት አቶ ደረበ ተናግረዋል፡፡
ልጆቹ ያልገባቸው ወይም ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ሲገጥማቸው እገዛ እንደሚያደርጉላቸውም አቶ ደረበ ገልጸዋል፡፡ ሰዓትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ ለረጅም ሰዓት ስልክ እና ቴሌቪዢን ላይ ጊዜን ማዋል የማይፈቀዱ ነገሮች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሉሲ እና ሶሊያና ጥሩ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ለአብነት ሉሲ አምና ሁለተኛ ደረጃን ከክፍል ይዛ አጠናቃለች፡፡ ሶሊያናም አብዛኛውን ፈተናዎቿን ደፍናለች፡፡ ልጆች የአቶ ደረበ ተሞክሮ ጠቃሚ ነው አይደል? ወላጆች መሰል ስልቶችን ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል!
ተረት
መልካሙ ሰው
በድሮ ጊዜ አንድ ጥሩ ሰው ነበር:: አንድ ቀን ታዲያ ብቻውን ፀሎት ለማድረስ ፈልጎ ፀጥ ወዳለ ቦታ እየሄደ ሳለ አንድ የመስኖ እርሻ ቦታ ሲደርስ መንደሪን ውኃው ላይ ሲንሳፈፍ አየ:: መንደሪኑንም አንስቶ በላውና ለፀሎት መዘጋጀት ጀመረ:: በዚህ ጊዜ መንፈስ ተገለጠለትና “ለአምላክ የተገዛሁ ነኝ እያልክ ለምንድነው የሌላ ሰው ፍሬ አንስተህ የበላኸው?” አለው:: ወዲያውኑ መልካሙ ሰው በድርጊቱ ተፀፅቶ ወደ እርሻው በመመለስ የመንደሪን እርሻ አጠገብ ደረሰ:: ወደ እርሻው ባለቤትም ሄዶ “ከዛፍ ላይ የወደቀ አንድ የመንደሪን ፍሬ ውኃው አምጥቶት ስላየሁ በልቸዋለሁና ይቅር በለኝ” አለው:: የእርሻው ባለቤት ግን ይቅር አልልህም ስላለው ቅዱሱ ሰው በጣም አዘነ:: የእርሻውም ባለቤት “ይቅርታ እንዳደርግልህ ከፈለክ የምጠይቅህን ነገር ማድረግ አለብህ” አለው:: ፃዲቁም ሰው ተስማማ:: ገበሬውም “አይንና እግሮች የሌሏትን ልጄን ካላገባህ ይቅር አልልህም” አለው:: ፃዲቁም “ችግር የለም፣ ይቅር ካልከኝ አገባታለሁ” አለው::
ከዚያም ወደ እርሻው ባለቤት ቤት ሄደው መልካሙ ሰው ልጅቷ የት እንዳለች ጠየቀው:: ባለቤቱም “ልጄን ከማየትህ በፊት ስለጋብቻው ዝርዝር ሁኔታ እንነጋገር” አለው:: መልካሙ ሰው የተባለውን ሁሉ አደረገ:: ልጅቷም ከተደበቀችበት ቦታ ስትወጣ ሁለት ዓይኖችና ሁለት እግሮች ያሏት ከመሆኗም በላይ በጣም ቆንጆ ነበረች:: መልካሙ ሰው የእርሻውን ባለቤት “ዓይኖችና እግሮች የሏትም ብለኸኝ አልነበረም እንዴ?” ሲለው፣ እሱም “ልልህ የፈለኩት ልጄ ክፉ ነገር አድርጋ የማታውቅና በባህሪዋም የተሳሳተ መንገድ ያልያዘች መሆኗን ልነግርህ ፈልጌ ነው” አለው::
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች መጽሐፍ
ሞክሩ
- ውኃ ለምን ጭልጥ አድርገን እንጠጣለን? ስለማይላመጥ
- የኤሌክትሪክ ባቡር ወደ ሰሜን ይጓዛል፡፡ ጭሱ ወደ የትኛው አቅጣጫ ይወጣል? ጭስ የለውም
- ጥርስ የላት ጥሬ መብላት አያቅታት? ዶሮ
ነገር በምሳሌ
-ለአኩራፊ ምሳዉ እራት ይሆነዋል:: አኩራፊ እራሱን ነው የሚጎዳው ለማለት ነው::
-ሐሳብ ያገናኛል፤ ፍርሐት ያሸኛኛል:: ልብ ለልብ መገናኘት አብሮ ያኖራል::
-እርጎ መስሎሽ፣ እርሾ ጥልቅ፤ ነገርን ሳያጣሩ መወሰን ስህተት ነው፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


