ዐፄ ዳዊት ቀዳማዊ የዐፄ ሰይፈ አርእድ ልጅ ናቸው:: ዐፄ ሰይፈ አርእድ ከዐፄ አምደ ጺዮን ቀጥሎ የነገሡ ሲሆን መላው ኢትዮጵያን ለ28 ዓመታት አስተዳድረዋል:: እሳቸው ሲያልፉ ልጃቸው ዐፄ ውድም አስፈሬ ነገሡ:: ዐፄ ዳዊት ደግሞ ስልጣኑን ከወንድማቸው ከውድም አስፈሬ ተረከቡ::
ዐፄ ዳዊት ወደ መንበረ ስልጣናቸው በመጡ ሰሞን ከግብጽ ጋር ከዚህ ቀደም የተደረገው የሰላም ስምምነት ደብዛው የጠፋበት እና የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የሻከረበት ጊዜ እንደነበር ፍስሃ ያዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ በተሰኘው ቅፅ አንድ መጽሐፉ ይጠቅሳል:: ይህን ዐፄ ዳዊት የሻከረውን የግብጽ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ለማሻሻል እና ቀደም ሲል የተደረጉ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም አጠናክሮ ለማስቀጠል ሙከራ አድርገዋል::
ንጉሡ ከአባታቸው ዘመን ጀምሮ በሽምግልና የሚመጡ የሃይማኖት ሊቃውንትን እስከ ወደብ ድረስ በመሄድ ይቀበሉ ነበር:: በወንድማቸው በውድም አስፈሬ ዘመነ መንግሥት ጉዞ የጀመሩ የግብጽ ሊቃውንት በመንገድ ላይ እንዳሉ ዐፄ ውድም አስፈሬ ሕይወታቸው አለፈ:: በዚህም ዐፄ ዳዊት ተተኩ:: መንገድ የጀመሩት ሽማግሌዎች ኢትዮጵያ ደረሱ:: ዐፄ ዳዊትም አክሱም ድረስ በመሄድ አገኟቸው:: በማንኛውም ጉዳይ የመጡበትን አሳክተው እንዲመለሱም አደረጉ:: ይህ ነገር በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የነበረውን ግንኙነት የተሻለ እንዲሆን አስችሏል::
በዚህም ሰላማዊ ንግድ እንዲካሄድ፣ በግብጽ ያሉ ክርስቲያኖች እንዳይበደሉ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንዳይጉላሉ በሚሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ተደረሰ::የኢትዮጵያን እና የግብጽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ዐፄ ዳዊት የራሳቸውን መልዕክተኞች ወደ ካይሮ ላኩ::
መልዕክተኞችም ለግብጽ ሱልጣን የሚሰጥ በ20 ግመሎች የተጫነ ዕቃ ይዘው ነበር:: ለገጸ በረከት ከተያዘው ዕቃ ውስጥም በሽምብራ መልክና ቅርጽ የተሠሩ ወርቆች የሞሉበት በርካታ ከረጢቶች እና በወርቅ የተሠሩ ማሰሮዎች ይገኙበታል::
መልዕክተኞቹ ከግብጽ ሱልጣን ጋር ተገናኝተው ስጦታውን አበረከቱ:: ሱልጣኑም በክብር ተቀብሎ እንዲስተናገዱ አደረጋቸው::
በዚህ ጊዜ በዐፄ ዳዊት እና በሱልጣኑ መካከል ከቃላት የዘለለ እርቀ ሰላም ወረደ፤ ወይም የወረደ መሰለ:: ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ የግብጹ ሱልጣን ተደስቶ ማንኛውም ኢትዮጵያዊያን ወደ ግብጽም ሆነ ወደ እየሩሳሌም ሲጓዙ በየመንገዱ ችግር እንዳይገጥማቸው፣ በእየሩሳሌም የሚገኙ መነኮሳት እና ምዕመናን ያለ ችግር እንዲንቀሳቀሱ፣ በሰላም እንዲኖሩ አዘዘ:: ዐፄ ዳዊት የግብጽን ሱልጣን ድጋፍ ካገኙ በኋላ የእየሩሳሌም ፓትሪያሪክ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተመለሱ ጊዜ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን እና ንግሥት እሌኒ አገኘችው ከሚባለው ከእውነተኛው መስቀል እንጨት አንድ ጉማጅ እንዲልኩላቸው ለእየሩሳሌም ገዳም ባለስልጣናት ጥያቄ አቀረቡ::
ከጥያቄው ጋርም በርካታ የወርቅ ስጦታ ጨምረው ላኩ:: በመልክተኞቹ አማካኝነት ስጦታው የደረሳቸው ባለስልጣናትም የንጉሡን ስጦታ ተቀበሉ:: ግማሹን ወርቅ የእየሱስ ክርስቶስ መቃብር በሚገኝብት በጎለጎታ አስቀመጡት::
በግማሹ ወርቅ የማርያምን እና እየሱስን ስዕል በአንድነት ያለበትን ምስል በተጨማሪም አክሊለ እሾክ እንዳደረገ የሚያሳየውን ምስል ገዝተው ከግማደ መስቀሉ ጉማጅ ጋር አብረው ወደ ኢትዮጵያ እንደላኩት ፍስሃ ያዜ ጽፏል:: መልዕክተኞቹ ስጦታውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ እንደ ቀድሞው የደህንነት ስጋት ባለመኖሩ እና በመንገዳቸው ላይ ምንም የገጠማቸው ችግር ባለመኖሩ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መሪዎች የተደረገው ስምምነት መተግበር አመላካች እና አረጋጋጭ ነበር:: መልዕክተኞቹ ኢትዮጵያ ሲገቡ ዐፄ ዳዊት ሩቅ ቦታ ድረስ ሄደው ተቀብለዋቸዋል:: ሕዝቡም በሆታ ወጥቶ ደስታውን ገለጸ:: ከፍተኛ በዓል እና ድግስም ተደረገ:: በሌላ ትውፊት ደግሞ እንዲህ ተተርኳል ‹‹ይነብር መስቀልየ በዲበ መስቀል (መስቀሌ በመስቀል ላይ ይቀመጣል) የሚል ህልም ዐይተው መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ወሰኑ::
በእርሳቸው የንግሥና ዘመን የግብጽ ነገሥታት በግብጽና አካባቢው ይኖሩ በነበሩ ክርስቲያኖች ላይ በደሎችን ይፈፅሙ ነበር፤ የግብጽ፣ የአርመን፣ የቁስጥንጥንያ፣ የሶሪያና የሮም ክርስቲያኖች መስቀሉን እንዳይሳለሙ ጫና ያደርጉባቸውም ነበር:: ይህን ጉዳይ የሰሙት ዐፄ ዳዊት፣ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና በግብጽና አካባቢው የነበሩ ክርስቲያኖችን ስቃይ ለማስቆም ወደ ግብጽ ዘመቱ:: ንጉሡ ካርቱም በደረሱ ጊዜ የዓባይን ወንዝ ወደ በረሃ እንዲፈስ በማድረግ አቅጣጫውን እንዲቀይርም አደረጉት:: ይህኛውን ታሪክ ግን ፍስሃ ያዜን ጨምሮ ሌሎች የታሪክ ጸሐፊዎች አይቀበሉትም:: በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጌታ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ይተረካል::
ስለአመጣጡም ሁለት ታሪክ ምንጮች ያሉት ነው:: አንዱ ዐፄ ዳዊት ራሳቸው ወደ ግብጽ ዘምተው ይዘውት መጡ ይላል:: ነገር ግን ዐፄ ዳዊት ግብጽን አልተሻገሩም:: ቢሆንም እንኳን መስቀሉ ያለው እየሩሳሌም እንጂ ግብጽ አይደለም::
ሁለተኛው ደግሞ የዐፄ ዳዊት አባት ዐፄ ሰይፈ አርዕድ የግብጽ ሱልጣኖችን በኃይል ይገፉዋቸው ስለነበር እነርሱም ክርስቲያኖችን ያሰቃዩ ነበር::
በዚህም እርቅ እንዲፈጸም አለመግባባቱንም እርዲሪቅ በማሰብ በአባ ማርቆስ የሊቀ ጵጵስና ዘመን የኢየሩሳሌም ፓትርያሪክ መሪ ሆነው ከእስክንድርያም አባ ቄርሎስ (አሕናስ ኤጵስ ቆጶስ) እንዲሁም አባ ማዕምር የተባሉ ሊቅ ወደ ኢትዮጵያ መጡ:: በዚህ ጊዜ ሰይፈ አርዕድ አርፈው የልጅ ልጃቸው ዐፄ ዳዊት ነግሠው ነበር:: እነዚህ መልዕክተኞች የግብጽና የኢትዮጵያን አለመግባባት በመፍታት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ዐፄ ዳዊት በነበራቸው መንፈሳዊ ቅንዓት እሌኒ አስቆፍራ ካስወጣችው መስቀል ግማደ መስቀሉን እንዲልኩላቸው ለገጸ በረከትም እንዲሆን ብዙ ወርቅና አልማዝ አስጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ:: ፓትሪያሪኩም የመስቀሉን ክፋይ አክሊለ ሦክ ሉቃስ የሣለውን የምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል ላኩላቸው:: ግማደ መስቀሉም በዚህ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መስከረም 10 ቀን ገብቷል ይባላል::
አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል-ኒየችኮ በጻፉት እና ዓለማየሁ አበበ በተረጎመው “የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ አሁን ዘመን” በተሰኘው መጽሐፍ ዐፄ ዳዊት በማኅበረ ቅዱሳን እና በአንዳንድ የቤተ ክህነት ሰዎች ስልጣን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ግፊት ይደረግባቸው እንደነበር ተጽፏል:: ልጃቸው ዐፄ ዘረያዕቆብ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ከፍተኛ ተጸዕኖ ይደረግ ነበር:: ይህ ደግሞ ዐፄ ዳዊት ከግብጽ መንግሥት ጋር ከነበራቸው ሽኩቻ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል በመጸሐፉ ግምት ተቀምጧል:: ለዚህም ደግሞ በቤተ ክህነት ውስጥ ያሉ ግብጻዊያን ካህናት ንጉሡ ስልጣን እንዲለቁ በማነሳሳት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ:: ዐፄ ዳዊትንም አስወግደው የሚመች እና እንደፈለገ ለማሾር እንዲሁም ለግብጽ መንግሥት የሚመች ንጉሥ ለማምጣት ፍላጎት ነበራቸው:: የዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት በሀገር ውስጥ አስተዳደር እና ተያያዥ ጉዳዮች የይፋቶች እና የአዳሎች ጦርነት ይፈትነው ነበር:: ከዚህ ውጪ በሰሜን ደግሞ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አመጾች ከመኖራቸው ውጪ አብዛኛው ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥቱ ስር ሲተዳደር ነው የኖረው::
ይፋቶችን እና አዳሎችን ግን እስከ ስልጣናቸው መጨረሻ ማስገበር እና በስራቸው መስተዳደር ሳይችሉ ቀርተዋል:: ለግጭቱ መባባስ ምክንያት የሆነው ሃይማኖት ልዩነት ብቻ ሳይሆን የውጪ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ነው:: በዋናነት የየመን መንግሥት ከግጭቱ ጀርባ ነበረበት:: በተለይም በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንገስሥት የተነሳው እና ኤደንን እና ቀይባህርን እያስተዳደረ ስልጣኑን እስከ ዘይላ ድረስ ያሰፋው የየመኑ ሹም በኢትዮጵያ ነገሥታት ላይ የሚያምጹ እና የሚሸፍቱትን ባላባቶች በመሳሪያ፣ በወታደር እና በሌሎች መንገዶች እርዳታ እና ድጋፍ ያደርግ ነበር:: ሲሸነፉም መጠጊያ እና መሸሻ እያዘጋጀ ያስጠልላቸው ነበር::
በተመሳሳይ የግብጽ ሱልጣኖችም ለአማጺያን በግልጽም ሆነ በድብቅ እገዛ ያደርጉ ነበር::ዐፄ ዳዊት ከ30 ዓመት የንግሥና ቆይታ በኋላ ጥቅምት 9 በ1395 ዓ.ም በአደጋ ሕይወታቸው አለፈ::
ንጉሡ ጥብቅ ሃይማኖተኛ በመሆናቸውም ጦርነቶች ላይ አይሳተፉም ነበር:: ከበታች ያሉ ሹማምንቶቻቸው ነበር በጦርነቶች የሚዋጉት:: ዐፄ ዳዊት ከጦርነት ይልቅ ዲፕሎማሲን ይመርጡ የነበሩ ንጉሥ ናቸው::
ሳምንቱ በታሪክ
ካሳ ምርጫ ነገሡ
ደጃዝማች ካሳ ምርጫ (አባ በዝብዝ) ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ስመ መንግሥታቸው “ዮሐንስ ራብዓዊ” ( ዮሐንስ ፬ኛ) ተብሎ፣ በጳጳሱ በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው በሥርዓተ መንግሥት ንጉሠ ጽዮን፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ።
በታሪክ እንደተመዘገበው በዚሁ ንግሥ ምክንያት ሦስት ቀን በዓል ሆኖ፣ ለግብር አራት ሺህ ሰንጋ ታርዶ፣ 50 ጉንዶ ማር የፈጀ፣ ሺህ ገንቦ ጠጅ ቀርቦ፣ በደስታ ሲበላ ሲጠጣ ሰንብቷል።
ዓፄ ዮሐንስ 4ኛ ከአባታቸው ከተንቤን ባላባት የራስ ስኹል ሚካኤል የልጅ ልጅ ሹም ተንቤን ምርጫ እና ከእናታቸው የእንደርታው ገዢ የራስ አርአያ እህት ወይዘሮ ወለተ ሥላሴ ሐምሌ 5 ቀን 1829 ዓ.ም ማይ በሀ በሚባል ሥፍራ ተወለዱ።
ምንጭ፡- “የጥንቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” -መሪ ራስ አማን በላይ
ሾዪቺ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጃፓን ሠራዊት ውስጥ ተሰልፎ የነበረው 50 ዓለቃ ሾዪቺ ዮኮይ ጦርነቱ ባከተመ በ27 ዓመቱ ጥር 15 1964 ዓ.ም ተደብቆ በኖረበት በጉዋም ጫካ ውስጥ ተገኝቶ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
ሲመለስ «በሕይወቴ ስመለስ ትልቅ እፍረት እየተሰማኝ ነው» ብሎ ተናገረ። ሾዪቺ ከተመለሰ በኋላ ለ25 ዓመታት ኖሯል ሲል ሂስትሪ ዶት ኮም ዘግቧል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


