ጥምቀት ከመንፈሳዊ ፋይዳዉ ባሻገር

0
104

ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በአደባባይ ከሚከበሩ ታላልቅ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሃንስ እጅ መጠመቁን ለማሰብ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በየዓመቱ ጥር 11 ይከበራል።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች በበዓሉ መንፈሳዊ ህይወታቸው የሚታደስበትና የሚነቃቁበት እንዲሁም ፈጣሪያቸው ስላደረገላቸው ነገር ሁሉ በጸሎት፣ በእልልታና በዝማሬ ምስጋና የሚያቀርቡበት በዓል ነው::

የጥምቀት በዓል አከባበር የሚጀመረው በበዓሉ ዋዜማ ሲሆን ይህም ከተራ ይባላል።  እለቱ ታቦታት በዝማሬ ታጅበው ከመንበራቸው ወደጥምቀተ ባህሩ ጉዞ የሚያደርጉበት  ነው:: ከተራ የጥምቀት ሥርዓት የሚከናወንበት ቦታ ወይም ባህር ለመፍጠር ወንዝን በመከተር ወይም በመገደብ ጥምቀተ ባህርን የመፍጠር ተግባር የሚፈጸምበት ዕለት ነው።

የተፈጥሮ ባህር በሌለባቸው የገጠር አካባቢዎች በዚህ የከተራ ቀን ባህረ ጥምቀትን በግድብ መስራት የግድ ሲሆን  በጊዜ ሂደት አንዳንድ አካባቢዎች  ቋሚ የጥምቀተ ባህር ገንዳዎችን ይገነባሉ።

ከነዚህ መካከል የጎንደሩ የፋሲለደስ ገንዳ  እና የአክሱሙ የንግስተ ሳባ ገንዳ በቀደምትነት የሚጠቀሱ ታሪካዊ ቦታዎች ናቸው።

ከተራ የመጠመቂያውን ባህር ከማዘጋጀትም አልፎ  የታቦታቱ ማደሪያ ድንኳኖች የሚተከሉበትና ታቦታቱ ከመንበራቸው  ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባህር ለአዳር የሚወጡበትና ምእመናን ታቦታትን በማጀብ በዝማሬ፣ በእልልታ፣ በምስጋና፣ እና በሆታ የሚጓዙበት ዕለት ነው::

እናም በዚህ ዕለት ምዕመናኑ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚሉትን ብሂል ተከትለው አስቀድመው ለበዓሉ ያዘጋጇቸውን ንፁህና ነጫጭ አልባሳት ለብሰው በተለያዩ ጌጣጌጦች አምረውና ደምቀው ወደ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቸው ረፋድ ላይ ይወጣሉ።

ምዕመኑ ነጭ የመልበሳቸው ምክንያት ንጽህናና ታማኝነትን ሲያመላክት በጌጣጌጥ መዋባቸውና ሆታቸው ደግሞ በጥምቀቱ መዳንና መፈወስን በማሰብ ደስታቸውን  ለመግለፅ እና ፈጣሪያቸውን ለማወደስ ነው።

በዚሁ እምነታቸው መሰረትም ምዕመናኑ ከቤተ ክርስቲያናቸው ሲደርሱ የየግል ጸሎታቸውን በማድረስ ታቦታቱን ለማንገስ ይዘጋጃሉ። ካህናቱም ጽላቶችን በሚገባቸው የክብር መጎናጸፊያ ከብክበው ራሳቸውንም በአሸበረቁ ልብሰ ተክህኖና ካባዎች አስውበው ስርዓቱን በጋራ ጸሎት ያስጀምራሉ::

እኩለ ቀን ላይ ታዲያ ካህናትና ዲያቆናት የቤተ ክርስትያኗን ወረብ፣ ቅኔና መወድስ እያቀረቡ፣ የሰንበት ተማሪዎች በአማርኛና በግዕዝ ቋንቋዎች የምስጋና መዝሙሮችን እያሰሙ፣ በእናቶች እልልታና በኮበሌዎች ሆታና ጭፈራ እየታጀቡ አመሻሽ ላይ ወደ ተዘጋጀላቸው የታቦታቱ ማደሪያ ጥምቀተ ባህር ደርሰው ያርፋሉ። በአጠቃላይ የታቦታት ጉዞ በአማኞች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ በዮሐንስ እጅ ዝቅ ብሎ የመጠመቁን እና ትሕትናን ያሳየበት ሂደት መታሰቢያ ነው::

የከተራው በዓል ታቦታቱን ወደ ማደሪያቸው በማድረስ ይጠናቀቅ እንጂ የጥምቀተ ባህሩ ስፍራ ግን የስብከተ ወንጌል ትምህርት፣ የቅኔ መወድስ፣ የምስጋና መዝሙርና እልልታ ሳይለየው  ያድራል።

ጎህ ሲቀድ ታዲያ ጥር 11 በዓለ ጥምቀት መባቱ እውን ሆኗልና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ከተካሄዱ በኋላ ጥምቀተ ባህሩ ከስፍራው በተገኙት የካህናት አለቃ መስቀል ይባረካል። በመባረኩም በማየ ዮርዳኖስ (ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ስለመጠመቁ ማሳያ) ሆኗልና ክርስቲያኑ ምዕመን ይጠመቃሉ።

ጥምቀት እንደ ወርሃ ጳጉሜ ሰዎች በካህኑ ከተባረከው ጥምቀተ ባህር፣ ወንዝ ወይም ገንዳ ውስጥ ካህናት ወይም ዲያቆናት በሚረጩት  ጸበል የሚጠመቁበት ነው።

ጥምቀትን ስናነሳ በልዩ ድባብ የተለየ ባህላዊ ትውፊት የምታከብረው ጎንደር ትጠቀሳለች:: በአጼ ፋስለደስ መዋኛ ገንዳ የሚከናወነው የጥምቀት ስርዓት ዋናው የበዓሉ ድምቀ ነው:: ካህኑ ገንዳውን እንደባረኩ በዋና ገንዳው ዙሪያ ከተንሰራፉ ዕድሜ ጠገብ አገር በቀል ዛፎች ቅርንጫፍ  ላይ ተደብቀው በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ ታዳጊዎች ድንገት መሰስ እያሉ ወደ ገንዳው በመወርወር እየዋኙ ለበዓሉ የተለየ  ድባብ ይፈጥራሉ።

ቀሪው ምዕመን ደግሞ በካህናቱና ዲያቆናቱ እየተረጨ ይጠመቃል። ይህ ሂደት እና የጎንደር የጥምቀት አከባበር በ2011 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የሰው ልጅ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል::

የፈረስ ጉግስና የዱላ ምክክቶችም  በጎንደር የበዓሉ ማድመቂያዎች ናቸው።

በዓሉ መኸር ከተከተተ በኋላ የሚከበር መሆኑ  ምዕመናን በነቂስ ወጥተው እንዲታደሙ ያስችላል:: ይህ ጎንደርን የሚጎበኙ በርካታ የውጭ ቱሪስቶች ከመኖራቸው ጋር ሲደመር በእርግጥም የጎንደርን ጥምቀት ደማቅና ተወዳጅ ያደርገዋል::

ይኸው የጥምቀት በዓል ንጋት ላይ የሚፈፀመውን የመጠመቅ ሥርዓት ካጠናቀቀ በኋላ ታቦታቱ ወደመንበራቸው የመመለስ ጉዞም እንደቀደመው ድምቀት አይለየውም።

የካህናት፣ ዲያቆናትና ምዕመናን አልባሳትን ጨምሮ ጥላውና ድባቡ፣  ጸናጽሉ፣ መቋሚያና ካባው፣ በገናና ማሲንቆው፣ እንሶስላና ሎሚው፣ አደስና ቅቤው፣ ድሪ- አንባር- ጉትቻው፣ ሸንኮራና  ዱላው ወዘተ የጥምቀቱ ማድመቂያ ቁሳዊ ትውፊቶች ናቸው።

“በእደ ዮሐንስ ተጠምቀ፣

ኢየሱስ ናዝራዊ፣ ሰማያዊ

ሰማያዊ”

የሚለውን ጨምሮ በርካታ ዝማሬዎችና መወድሶች በካህናት፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እየተዘመሩ፤ በእናቶች ደግሞ፡-

“ዓመት ድገመኝ  ጌታዬ

የከርሞ ሰው በለኝ ጌታዬ

እረሰይ  ስለቴ ሰመረ፣

ለድንግል ማርያም ልጅ ነግሬው ነበረ” የሚሉና መሰል ስንኞች በእልልታ፣ ጭብጨባና እስክስታ ታጅበው ይቀነቀናሉ:: “ኃይ ሎጋው ሽቦ… ” የሚሉና መሰል ግጥሞች ከሩጫ፣ ዝላይና ግፊያ ጋር ተሰናስለው ጎረምሶችን እያስጨፈሩ በዓሉን የሚያደምቁ የጥምቀት ቃላዊ ትውፊቶች ናቸው።

በዚህ መንገድ በዓሉን በድምቀት ያጀቧቸውን ታቦታት ወደ ቤተ ክርስቲያን ካስገቡ በኋላ በየዘመዱ ቤት እየዞሩ ድግስ መካፈል፣ መብላትና መጠጣት፣ መጨፈርና መዝናናት ደግሞ የበዓሉ መቋጫ ነው።

ከዚያ በፊት በዓሉ ላይ መንፈሳዊ እርካታን ማግኘት፣ የተጣላን ማስታረቅ፣ አንድነትና ተግባቦትን የሚያስገኙ ትስስሮችን መፍጠር፣ በተለይ ባገር ቤት ሎሚ መወራወር፣ ባህላዊ ትውፊትን ማስቀጠል፣ ሀገራዊ ገጽታን መገንባትና የመሳሰሉት ደግሞ የጥምቀት በዓል ማህበረ- ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች ናቸው። ስዕለትና መልካም ምኞትም  መንፈሳዊ ትሩፋታችን ነውና እኛም በዚሁ ቃላዊ ትውፊት ተሰናበትን፡-

“ከርሞ እንገናኝ ለዓመት

እናንተም ሳትሞቱ እኛም ሳንሞት::”

ማረፊያ

የጥምቀት ስንኞች

ኧረ ነይ እምዬ ማሪያም፣

እንዲያው ባንዱ ልጅሽ በመድኃኒዓለም፡፡

ኧረ አደራ አደራ መድኃኒዓለም፣

ምን አልባት ምን አልባት ሰው አይሆነው  የለም፡፡

ኧረ አዘቀዘቀች ፀሐይ፣

የቆንጆዎቹን አንገት ልታይ ፡፡

ዕጣን ዕጣን ይሸታል መሬቱ፣

አባቴ ገብርኤል ያደረበቱ፡፡

አረበረበ የወይን ሀረግ፣

የሚካኤልስ ያለው ማዕረግ፡፡

 

(ጌታቸው ፈንቴ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here