ገንዘብ የመያዝ ገደቦች እና የወንጀል ተጠያቂነት

0
292

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ (Money Laundering) ወንጀልን እና የባንኮችን የገንዘብ እጥረት (Liquidity) ለመከላከል ሲባል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን ያወጣል። ከእነዚህም መመሪያዎች መካከል ዓብይ ቦታ የሚይዘው ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ጥሬ ገንዘብ መያዝ (Cash Holding Limit) ስለሚፈቀደው የገንዘብ መጠን የሚደነግገው መመሪያ ነው።

በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የክልል ዐቃቤ ሕግ አቶ አበራ ጋሸ ለበኵር ጋዜጣ እንደተናገሩት ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው ጥሬ ገንዘብ የመያዝ እና ከባንክ የማውጣት ገደቦችን ያስቀምጣል። እነዚህን የተላለፈ ደግሞ እንደ አግባብነቱ በእስራት፣ በገንዘብ  ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ አስረድተዋል።

ይህ የሆነውም ይላሉ አቶ አበራ ገንዘብ በመደበኛው ግብይት እና በፋይናንስ ተቋማት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ነው። ለዚህም የሚያግዙ ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው  መመሪያ ቁጥር CMD 1/2012 እና መመሪያ ቁጥር   CMD/2/2013  መሆናቸውን   አስረድተዋል።

ሰዎች ከመደበኛ የፋይናንስ ሥርዓት ውጭ መያዝ ያለባቸውን የገንዘብ መጠን ብሔራዊ ባንክ ጥሬ ገንዘብ ከማከማቸት ጋር በተያያዘ ያወጣውን  ክልከላ አውቀው ሊሆን እንደሚገባ አቶ አበራ አስገንዝበዋል። በመመሪያ ቁጥር CMD 1/2012 አንቀጽ 3.6 መሰረት ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት ከተፈቀደው ገደብ በላይ የባንክ ኖቶችን እና ሳንቲሞችን በሥራ ቦታ (ቢሮ)፣ በቤት ውስጥ ወይም በሌሎች ማናቸውም ቦታዎች ላይ ከመጠን በላይ መያዝ ወይም መደበኛ ዝውውርን ሊጎዳ ወይም ሊያቆም በሚችል መንገድ እንዲሁም ሕጋዊ  ገንዘብን ሊያበላሽ በሚችል መንገድ ማከማቸት በጥብቅ የተከለከለ ነው::ይህን መመሪያ ለማሻሻል በብሔራዊ ባንክ የወጣው መመሪያ ቁጥር CMD /2/2013 ደግሞ ከዚህ ቀደም ግለሰቦች እና ድርጅቶች በአንድ ጊዜ የባንክ ኖቶችን (የወረቀት ብር) እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መያዝ ይችሉ የነበረውን የገንዘብ መጠን ለመቀነስ የወጣ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ብሔራዊ ባንክ መጠኑን ለግለሰቦች እና ለድርጅቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው ወደ አንድ መቶ ሺህ ብር እና ሁለት መቶ ሺህ ብር ዝቅ ማድረጉን ጠቁመዋል። ማንኛውም ግለሰብ ከፋይናንስ ተቋማት በተለይም ከባንክ ውጪ (በኪሱ፣ በቤቱ ወይም በቢሮው) መያዝ የሚችለው የገንዘብ መጠን ደግሞ አንድ መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው። ይህም ማለት ማንኛውም ግለሰብ ወይም የንግድ ድርጅት   ለዕለታዊ እንቅስቃሴው የሚያስፈልገው ሆኖ ቢገኝ እንኳን ከዚህ መጠን በላይ ጥሬ ገንዘብ ማስቀመጥ አይችልም ማለት ነው። ከዚህ መጠን በላይ የሆነ ገንዘብ ያለው አካል ገንዘቡን ወደ መደበኛ የፋይናንስ ስርዓት በተለይም ወደ ባንክ ገቢ ማድረግ ይጠበቅበታል።

እንደ አቃቢ ሕግ ባለሙያው ማብራሪያ የተጠቀሰውን የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በመተላለፍ ማንኛውም ግለሰብ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ እንዲሁም ድርጅቶች ደግሞ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ማስቀመጥ ወይም መያዝ አይችሉም፡፡ ከተጠቀሰው ገንዘብ መጠን በላይ ይዘው ከተገኙም የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል:: የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ቁጥር 1359/2017 አንቀጽ 51(4) ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ወንጀሉ የተፈፀመበት ንብረት ማለትም ገንዘቡ መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ የተወሰነውን የጥሬ ገንዘብ ማውጣት እና መያዝ ገደቦችን የጣሰ እንደሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከ10 ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል። ስለሆነም  ማንኛውም ግለሰብ ከመደበኛው የፋይናንስ ስርዓት ውጭ ጥሬ ገንዘብ  አከማችቶ ከተገኘ፣ ከደበቀ እና ይዞ ከተገኘ በወንጀል ያስጠይቃል።

በመመሪያው ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ የመያዝ ወንጀሉ የተፈፀመው በድርጅቶች ሲሆን ደግሞ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ (4)፣ (6) እና (7) መሰረት ከ7 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር መቀጮ  እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል::

የተፈቀደው የገንዘብ መጠን

እንደ አቶ አበራ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ባለው መመሪያ መሰረት ማንኛውም  ድርጅት ወይም ተቋም ከባንክ ውጪ በተቋሙ ውስጥ ወይም በንግድ ቦታው መያዝ የሚችለው ከፍተኛው የገንዘብ መጠን  ሁለት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ነው።

በተመሳሳይ ማንኛውም ሰው ከባንክ ውጪ (በኪሱ፣ በቤቱ ወይም በቢሮው) በጥሬ ገንዘብ መያዝ የሚችለው የገንዘብ መጠን ደግሞ አንድ መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው።

የሕጉ ዓላማ

ብሔራዊ ባንክ  ይህንን ሕግ ያወጣበት ዋና ዋና ምክንያቶች  ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ወደ መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓት ለማስገባት፣ ሕጋዊ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማበረታታት፤  የብር ኖቶች ባልተገባ ቦታ እንዳይቀመጡ እና ጉዳት እንዳይደርስባቸው፣ ገንዘብ በባንክ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እና በግብይት ላይ እንዲውል፣ ለወንጀል መፈፀሚያ ዓላማ እንዳይውሉ ለማድረግ ወይም ሕገ-ወጥ ዝውውርን ለመግታት (ኮንትሮባንድ፣ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ሌሎች በሕገ-ወጥ ጥሬ ገንዘብ የሚከናወኑ ወንጀሎችን) ለመከላከል፣ ኅብረተሰቡ ጥሬ ገንዘብ ከመያዝ ይልቅ የዲጂታል ባንኪንግ አማራጮችን (ሞባይል ባንኪንግ፣ ቼክ፣ ሲፒኦ) እንዲጠቀም ለማድረግ ነው።

ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበራ በተለይ ብዙኃን መገናኛዎች  የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

በሕጉ መተላለፍ የሚከተሉ ቅጣቶች

በግለሰቦች ከመጠን በላይ ተይዞ የተገኘው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል፤  እስከ ሦስት ዓመት እስራት ወይም 10 ሺህ ብር ይቀጣል። ሕጋዊ ሰውነት ለተሰጣቸው ድርጅቶች ደግሞ ከ7 እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ያስቀጣል::    ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጣው እና አሁን በሥራ ላይ ያለው መመሪያ እንደሚያመለክተው ማንኛውም ሰው ከመደበኛ የፋይናንስ ስርዓት ውጪ (በኪሱ፣ በቤቱ ወይም በቢሮው) ጥሬ ገንዘብ መያዝ የሚችለው የገንዘብ መጠን ገደብ መጠን አንድ መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ብቻ ነው። ከዚህ መጠን በላይ ገንዘብ ይዞ መገኘት በሕግ ያስቀጣል። ገንዘቡ ሊወረስ እና ግለሰቡም በወንጀል ሊጠየቅ ይችላል።

ለድርጅቶች ደግሞ  ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ መያዝ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ይህንን ሕግ መተላለፍ ገንዘብን ከማስወረስ ባለፈ ድርጅቱን የሚመራው ኃላፊ ወይም የድርጅቱ ሰራተኛ ከድርጅቱ ጋር  ተጠያቂ በመሆን ለእስራትና ለገንዘብ መቀጮ ቅጣት እንደሚዳርግ የዐቃቢ ሕግ ባለሙያው አስገንዝበዋል። ስለሆነም ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከዚህ መጠን በላይ የሆነን ገንዘብ በባንክ አካውንታቸው ውስጥ ማስቀመጥ እና ለክፍያ ሲፈልጉም የባንክ አማራጮችን (ቼክ ወይም ኤሌክትሮኒክ ክፍያ) መጠቀም በሕግ የሚጠበቅባቸው ግዴታ ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በእጅ ሲገኝ በአፋጣኝ ወደ ባንክ ገቢ መደረግ አለበት። ይህም ሕጋዊ እና አስተማማኝ መንገድ ነው።

የህግ አንቀጽ

ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት አያድንም

 

ሕግ ስልጣን ባለው አካል የተደነገገ የተግባር ወይም የምግባር ደንብ እና አስገዳጅ የሕግ ኀይል ያለው አካል ነው። ይህንንም ዜጎች ሊታዘዙት እና ሊከተሉት የሚገባ ሆኖ ማዕቀብ ወይም ሕጋዊ ውጤት የሚጥል ሕግ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በመሆኑም የአንድ ሀገር ሕግ፦

* ሰላምን፣ ነባራዊ ሁኔታውን እና የግለሰብ መብቶችን ለማስጠበቅ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን እና ሥርዓት ያለው ማኅበራዊ ለውጥ እንዲኖር ለማድረግ ያገለግላል።

* ሕግን አለማወቅ እና የሕግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ በወንጀልም ሆነ በፍትሀብሔር ጉዳይ ሕጎቹ ስልጣን ባለው የሕግ አውጭ አካል ወጥተው ከጸደቁበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል። በመሆኑም ዜጎች የሕጎቹን መኖር ወይም መውጣት የማወቅ ግዴታ አለባቸው።

ይኸውም ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም የሚለው የሕግ መርሕ ከሮማዊያን ሕግ የተወሰደ ሲሆን ሕግን የማያውቅ ሰው ይዘቱን ባለማወቅ ብቻ ሕጉን በመተላለፍ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል የሚገልጽ የሕግ መርህ ነው።

የመረጃ ምንጭ፦ ፌደራል ዐቃቢ ሕግ

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here