አዋጁ ምን አዲስ ነገር ይዟል?

0
199

ጠንካራ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓት መኖር ለሰላም መስፈን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለገጠሩ ማኅበረሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ይህን መሰረት በማድረግም የአማራ ክልል  ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፤ 5ኛ ዓመት፤ 11ኛ መደበኛ ጉባኤው  የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ማሻሻያ አዋጅን አጽድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።

ዓላማው የመሬት ይዞታ ዋስትናን በማረጋገጥ ግጭትን መቀነስ እና መሬትን ሳያባክኑ ለተመደበው ትክክለኛ አገልግሎት በማዋል የምግብ ዋስትናን እና ዘላቂ ልማትን ማምጣት እንደሆነ ተመላክቷል።

የክልሉ መሬት ቢሮ አዲሱን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ አስመልክቶ ጥር 04 ቀን 2018 ዓ.ም መግለጫ ሰጥቷል። አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ የመሬት ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እና ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለውም በመግለጫው ተመላክቷል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በመግለጫቸው  አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚመልስ እና በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ሊዘልቅ የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል።

ዘላቂ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀምን ሥርዓትን በማስፈን የክልሉን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በዘላቂነት የሚያረጋግጥ  መሆኑን አዋጁ በግልጽ ማስቀመጡንም ኃላፊው ተናግረዋል:: ይህ አዋጅ ሲወጣ በየደረጃው የሚገኙ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሕግ ምርምር ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እና ተጨማሪ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑን አስረድተዋል። የአዋጁን ማስፈጸሚያ ደንብ የማዘጋጀት ሥራ መጀመሩን እና በቀጣይ መመሪያዎች እንደሚዘጋጁም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል::

ነባሩን የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 252/2009 ማሻሻል ያስፈለገበትም  አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያሉ ጉዳዮችን ባለመያዙ እና እንደ ሀገር የገጠር መሬት አጠቃቀምን ተመሳሳይ ለማድረግ በማስፈለጉ እንደሆነ  ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል። በተጨማሪም የክልሉን ዘላቂ ልማት ለማሳደግ፣ የሕዝቡን የአገልግሎት ፍላጎት፣ የገጠር መሬትን አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሳይንሳዊ የማድረግን አስፈላጊነት፣ የቴክኖሎጂውን ማደግ፣ በአተገባበር ሂደት የታዩ ጉድለቶችን ለማስተካከል እና ዘላቂ የገጠር መሬት አሥተዳደር መረጃን ለማዳበር እንደሆነም አቶ ሲሳይ አብራርተዋል::

የተሻሻለው አዋጅ በይዘቱ በተለይም የክልሉን አንጡራ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርጉ፣ አዳዲስ እሳቤዎችን፣  የመሬት መረጃ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶች፣ የመረጃ ደህንነት ሥርዓት ጥበቃ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አካቶ የያዘ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሌላው ከሀገራዊ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ 1324/2016 አንቀጽ 60 ንዑስ (2) ጋር ተመሳሳይ የሆነ የመሬት አሥተዳደር እንዲኖራቸው ለማድረግ ታሳቢ መደረጉንም ጠቅሰዋል:: ከዚህ አኳያ የክልሉ የመንግሥት አስፈፃሚ ተቋማት እንደገና መልሶ ማደራጀት ሥልጣን እና ተግባር አዋጅ ቁጥር 300/2017 ለመሬት ቢሮ ሥልጣን የሰጠበት፣ ከፌዴራሉ ጋር የተጣጣመ እና የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ የዋጀ አዋጅ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ለአዋጁ  መሻሻል መሰረታዊ  ምክንያቶች መካከል

የአርሶ አደሮችን እና የከፊል አርብቶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ጋር ማራመድ እንዲቻል እና በመሬት ይዞታው ላይ ያለውን የንብረት መብት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሆነ ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል::

ሌላው ለአዋጁ መሻሻል ምክንያት ከክልሉ  የ25 ዓመቱ አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ለማደራጀት እና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና አጠቃቀም ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖረው ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ መቃኘት በማስፈለጉ ነው፡፡ በመሬት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን ለመቀነስ፣ ዘመናዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፣ የሴቶች፣ ሕጸናት እና ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት እና ዋስትና ለማረጋገጥ ነው፡፡

እንዲሁም የግል ባለሀብቱ እና አግባብ ያላቸው ድርጅቶች መሬትን በአግባቡ በማልማት የመጠቀም እና የመጠበቅ ኃላፊነትን ከፍ ለማድረግ፣ በተበታተነ መንገድ ያሉ አርሶ አደሮችን በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ወደ አንድ ማዕከል ለማምጣት፣ ከተሜነትን በገጠር በመመስረት ዜጎች ባሉበት ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማድረግ፣ የገጠር ኮሪደር ልማትን ለመተግበር፣ አርሶ አደሮችን የመሠረተ ልማት (የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌ፣ የኢንተርኔት እና ሌሎችን) ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የክልሉን መሬት እና የተፈጥሮ ሀብቱን በአግባቡ ማስተዳደር የሚሉት ጉዳዮች በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ አዋጅ ይዟቸው የመጡ ዋና ዋና ጉዳዮች

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ አዋጁ የሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የተጠቃሚነት መብት ከለላ የሰጠ ነው::እነዚህ አካላት  እንደማንኛውም አርሶ አደር በገጠር ይዞታቸው ላይ ማግኘት የሚገባቸውን መብት እንዲያገኙ ሙሉ ዕውቅና እና ድጋፍ የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

መሬትን በባለቤትነት የመጠቀም መብት እና የሕግ ዋስትና ሽፋንም ለአርሶ አደሮች ሰጥቷል:: አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለልጆቻቸው እና ላመኑበት ለማንኛውም ሰው በስጦታ  እንዲሰጡ ዕድል የሰጠ እንደሆነም አቶ ሲሳይ አስገንዝበዋል። ባለይዞታው በመሬቱ መጠቀም፣ ማከራየት፣ ለጋራ አራሽ መስጠት፣ ቋሚ ንብረትን በሽያጭ የማስተላለፍ፣ በኩታ ገጠም ማረስን እና አሥተዳደራዊ ወሰን የማይገድበው የመለዋወጥ መብትን በሰፊው መስጠቱን ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ሌላው አዋጁ የወጣቶችን እና በአዲስ መሬት ጠያቂዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ከሦስተኛ ወገን ነጻ የሆነ መሬት አሥተዳደርን በማስፈን ወጣቶች ተደራጅተውም ሆነ በተናጠል በፍትሐዊነት የሚያስተናግድ እና አልምተው እንዲጠቀሙ የሚያግዝ መሆኑን አክለዋል። በበቂ ሁኔታ ያልለማ መሬትን በመለየት በግብርና ልማት ለሚሰማሩ ወጣቶች በሕጋዊ መንገድ መስጠት እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ ባለቤት የሌለው መሬት ካለ ወጣቶች ተደራጅተውም ሆነ በተናጠል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል። በገጠር መሬት የመጠቀም መብትን እንደማስያዣ በመጠቀም ለግብርናና ተያያዥ ገቢ ማስገኛ ተግባራት የብድር አቅርቦትን ለገጠር ባለይዞታዎች ተደራሽ ለማድረግ ዕድል እንደ ሚሰጥም ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል::

መሬትን ስለመለካት፣ ካርታ ስለማዘጋጀት እንዲሁም ከዳታ ጋር በተያያዘ አሻሚ የነበሩ ሕጎችን እና በማንዋል ብቻ የነበረውን የመሬት አሥተዳደርን በዲጂታል እንዲሆን አድርጓል።

አዋጁ ለባሕላዊ ሽምግልና ዕውቅና በመስጠት አለመግባባቶች እና ግጭቶች በሽምግልና እንዲፈቱ ዕድል ሰጥቷል። የአሥተዳደር ሥርዓቱ ከማኅበረሰቡ ዕሴቶች ጋር እንዲስማማ ማድረግንም በትልቁ ዕውቅና የሰጠ ነው::

የአርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ለግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዋስትና እንዲሆንም ያገዘ ነው ብለዋል:: ስለሆነም አርሶ አደሩ የአርንጓዴ ማረጋገጫ ደብተሩን በማስያዝ ከአበዳሪ ተቋማት የብድር አገልግሎት የሚያገኝበት በመሆኑ የገጠሩን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

አዋጁ የገጠር መሬት የሚጠቀሙ ባለሀብቶችን የረጅም ጊዜ ብድር እንዲያገኙ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በበቂ ሁኔታ ለመግዛት ዕድል ይሰጣል። ስለሆነም በሰፋፊ የእርሻ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ይበልጥ ልማታቸውን ለማከናወን የተሻለ ዕድል ይዞ እንደመጣ አስታውቀዋል። ከዚህ በፊት አርሶ አደሮች በማሳቸው ላይ ያለሙትን ቋሚ ንብረት የመሸጥ መብት አልነበራቸውም። አሁን ግን ቤትን ጨምሮ ሌሎች ቋሚ ተክሎችን እንዲሸጡ የፈቀደ ነው ብለዋል::

ለመንግሥት ሠራተኞች በውርስ እና በስጦታ መሬት ማግኘት የሚችሉበትን መብት ያጎናጸፈ አዋጅ እንደሆነም ቢሮ ኃላፊው  ገልጸዋል:: በሀገራችን እና በክልላችን ተጨባጭ ሁኔታ ዝቅተኛው የአርሶ አደሮች መሬት መጠን ሩብ ሄክታር ነው:: ከዚህ መጠን በታች ከሆነ ለአንድ ሰው ብቻ በሥጦታ ወይም በውርስ ማስተላለፍ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

 

መረጃ

የገጠር መሬት አስተዳደር ማለት የገጠር መሬት ይዞታ መብት የሚሰጥበት፣ ዋስትና የሚረጋገጥበት፣ የመሬት ሀብት ዋጋ የሚተመንበት፣ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ የሚተገበርበት በመሬት ተጠቃሚዎች መካከል፣ የሚነሱ ግጭቶች የሚፈቱበት እና ግዴታዎች የሚተገበሩበት እንዲሁም የገጠር መሬት መረጃ ሥርዓት የሚዘረጋበት ሂደት ነው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 11   ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here