በዓላት ለገጽታ ግንባታ  እና ለኢትዮጵያ ከፍታ!

0
148

ኢትዮጵያ የድንቅ ባህል እንዲሁም የመስህብ ስፍራዎች  ባለቤት ናት፡፡ የራሷ ቋንቋ እና ፊደል፣ ያመጋገብም ሆነ ያለባበስ ሥርዓት ያላት አስደማሚ ሀገር ናት፡፡ አራቱ  የሙዚቃ ቅኝቶች የተፈጠሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የዓለምን ትኩረት በእጅጉ የሳቡ በርካታ  ኃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላትም በድምቀት ይከበሩባታል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኘው የጥምቀት በዓል በያመቱ በድምቀት ከሚከበሩት ኃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ ዘንድሮም ጎንደርን፣ በሰሜን ሸዋ ኢራንቡቲ፣አዲስ አበባን፣ ባሕር ዳርን ጨምሮ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች   በድምቀት ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ  ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጎብኝዎች ታድመዋል፡፡

ከጥምቀት በዓል መከበር ቀደም ብሎም የሻደይ አሸንድየ፣ የዕንቁጣጣሽ፣    የመስቀል፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓላት… በታላቅ ድምቀት ተከብረዋል፡፡ መጪው ወቅትም የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ በዓል እንዲሁም የመርቆርዮስ ክብረ በኣል በደብረታቦር እና ሌሎች ታላላቅ በዓላት የሚከበሩበት ነው፡፡

በዓላትን ስናከብርም ሆነ ጎብኝዎችን ስናስተናግድ አንድ ልብ ልንለው የሚገባን ቁም ነገር አለ፡፡ ጎብኝዎች አቅደው፣ ሀብት ይዘው፣ ውጣ ውረድ የበዛበት ረዥም መንገድ ተጉዘው ወደ ሀገራችን የሚመጡት በበዓላቱ ከመታደም እንዲሁም የመስህብ ስፍራዎቻችንን ከመጎብኘት ባሻገር በኢትዮጵያውያን ውብ ባህል መሠረት ለመስተናገድ፣ ደስታን እንዲሁም ርካታን ለማግኘት ሲሉ ነው፡፡ ጎብኝዎቻችን እነሱ ጋ የሌለ፣ ባንጻሩም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ድንቅ ባህል ጠርቷቸው ሲመጡ በባህላችን ኮርተን፣ ራሳችንን ሆነን ልንቀበላቸው ይገባል፡፡ ባለባበሳችን፣ ባጊያጌጣችን፣ ባነጋገራችን  ራሳችንን ሆነን፣ ማረፊያዎቻችንን እና መዝናኛዎቻችንን እንደ ወግ ባህላችን አዘጋጅተን፣ ባህላዊ ምግቦችን እንዲሁም መጠጦችን አዘጋጅተን በተለመደው ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህላችን ተቀብለን ባክብሮት እንዲሁም በትህትና ማስተናገድ ይኖርብናል፡፡

እንግዶቻችን በማረፊያም ሆነ በመዝናኛ  አካባቢዎች ሲሆኑ  የደኀንነት ስሜት እንዲሰማቸው፣ ያለ ሥጋት ወደፈለጉት አካባቢ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡

ለዚህ ደግሞ ባህላዊ ምግቦችን የሚያቀርቡ፣ የመኝታ እና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሆቴሎችን፣ ምግብ ቤቶችን፣ መዝናኛዎችን… ማደራጀትም አስፈላጊ ነው። እነዚህ ተቋማት እኛነታችንን እንዲገልጹ አድርገን ማሰናዳት ይኖርብናል።

አልባሳትን ጨምሮ ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶቻችንን ለጎብኝዎች በማቅረብ አምራቹም ሆነ ነጋዴው  በተገቢው ሁኔታ የልፋት ዋጋውን እንዲያገኝ ማድረግም  የበዓል ወቅት ተግባራችን ሊሆን ይገባል። የግብርና ምርቶችንም ቢሆን ወግ እና ባህላችንን ሳንለቅ ለአያያዝ እና አጠቃቀም ምቹ አድርገን በማዘጋጀት ለጎብኝዎች ብንሸጥ የቱሪዝም ዘርፉን ዘላቂ የገቢ ምንጭ ማድረግ እንችላለን።

ጎብኝዎች ሀብት ይዘው ከሩቅ አገር ተጉዘው ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው  ወደ ሀገራችን የሚመጡት በእነሱ ሀገር የሌለውን፣  ባንጻሩም  በእኛ ሀገር ብቻ የሚገኘውን፣ የእኛነታችን መገለጫ የሆነውን ባህላችንን እንዲሁም የመስህብ ቦታዎቻችንን ለማየት፣  መልካም መስተንግዶ ለማግኘት፣ የማይረሳ አስደሳች ጊዜን ለማሳለፍ  እንደሆነ ተገንዝበን  ራሳችንን ሆነን ጎንበስ ቀና በማለት ማስተናገድ እና በዓላትን ለገጽታ መገንቢያ  እንዲሁም ለኢትዮጵያ ከፍታ መጠቀም ዘመናዊነት ደግሞም ብልህነት ነው።

ጎብኝዎቻችንን በዚህ መልኩ አስተናግደን ደስታ እና ርካታ  እንዲያገኙ ካደረግን ለጉብኝት የሚኖራቸውን የቆይታ ጊዜ ያራዝማሉ፡፡ የቆይታ ጊዜያቸው በተራዘመ ቁጥር ደግሞ ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ ይጨምራል፡፡ ጎብኝዎቹ የቆይታ ጊዜያቸውን አራዝመው፣ በመስተንግ ዷችን ተደስተው   ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም ስለ እኛ መልካም ገጽታ ግንባር ቀደም መስካሪዎች   ይሆናሉ፡፡

ጥምቀቱ በተከበረባቸዉ ቦታወች  ከተለያዩ አለማት የመጡ ጎብኝወች፣የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ፣ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊወች ተገኝተዋል።  በቀጣይም ሀገራችንን በመናፈቅ ለሌሎች  ሕዝባዊ እና ኃይማኖታዊ በዓላት  ሌሎች ጎብኝዎችን ጨምረው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ከፍታ የሚኖረው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ በጥንቃቄ እና በትኩረት ልንተገብረዉ ይገባል፡፡

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here