በእግር ኳስ ዓለም ተወዳጅ፣ ሀብታም እና ጠንካራ ፉክክር ያለበት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እንደገና ከተደራጀ 34 ዓመታትን ደፍኗል። በዚህ የሦስት አስርት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ዓለም ያደነቃቸው ክስተቶች ተስተናግደዋል፤ የማይሰበሩ የሚመስሉ ክብረወሰኖች ተሰባብረዋል፤ ታላላቅ ተጫዋቾች መጥተው አልፈዋል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ግርግር አንድ ለጆሮ የሚከብድ እና ለማመን የሚቸግር እውነት እንደ ተራራ ገዝፎ ከእንግሊዛውያን ፊት ቆሟል። የሊጉ ባለቤቶች፣ የእግር ኳስ ፈጣሪ ነን የሚሉት እንግሊዛውያን፣ በገዛ ሜዳቸው እና በራሳቸው ሊግ በአንድም እንግሊዛዊ አሰልጣኝ አማካኝነት የፕሪሚየር ሊጉን ክብር መጎናጸፍ አለመቻላቸው ነው። ይህ የእግር ኳስ ዓለም ታላቁ “ተቃርኖ” ነው ሲል ቢቢሲ ሰፖርት አስነብቧል።
አሁን ግን በምዕራብ ለንደን ሰማይ ስር አዲስ የተስፋ ጮራ ፈንጥቋል። ወጣቱ ሊያም ሮሴኒየር የቼልሲን መንበር መረከቡ ተከትሎ ነው ይህንን የዘመናት እርግማን ይሰብራል የሚል ተስፋ የተጣለበት። እ.አ.አ 1992 የሊድስ ዩናይትዱ አለቃ ሀዋርድ ዊልኪንሰን ቡድናቸውን ለድል ሲያበቁ ይህ የመጨረሻው የእንግሊዛዊ ድል ይሆናል ብሎ የገመተ ሰው አልነበረም። ያኔ ሊጉ ገና የመጀመሪያ ዲቪዚዮን በሚል ስያሜ ይጠራ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ መድረክ የባዕዳን መፈንጫ ሆኗል ይላል የቢቢሲ ዘገባ።
ከዊልኪንሰን በኋላ 12 አሰልጣኞች ቡድኖቻቸውን ለሊጉ ክብር አብቅተዋል። ነገር ግን ዝርዝሩን ስንመለከት አብዛኞቹ አሰልጣኞች እንግሊዛውያን አይደሉም። የታላቁ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን 13 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች እና የካታላኑ ፔፕ ጋርዲዮላ ስድስት ዋንጫዎች የዚህ ማሳያ ናቸው። ይህ ታዲያ ለእንግሊዝ እግር ኳስ አፍቃሪዎች የራስ ምታት የሆነው ለምን እንደሆነ ለመረዳት የሌሎችን የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች መመልከት በቂ ነው። በጣሊያን ከ20 የሊጉ አሰልጣኞች 16ቱ ጣሊያናውያን ናቸው፤ በስፔን ከግማሽ በላይ፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ በተመሳሳይ ሀገር በቀል አሰልጣኞች ሊጋቸውን በበላይነት ይመራሉ። በእንግሊዝ ግን ከዚህ ይለያል።
ስኮትላንዳዊው የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር ፈርጉሰን የኦልድ ትራፎርድን የ26 ዓመታት የዋንጫ ጥማት ሲቆርጡ ለእንግሊዛውያን አሰልጣኞች ደግሞ የጨለማው ዘመን እየመጣባቸው እንደሆነ አብስረዋል። በወቅቱ የአስቶን ቪላው ሮን አትኪንሰን እ.አ.አ በ1993 ሁለተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ለዋንጫው የቀረበበት ብቸኛው የመጨረሻው ወርቃማ እድል ነበር።
ከዚያ በኋላ ፕሪሚየር ሊጉ የዓለም ምርጥ አሰልጣኞች መዳረሻ በመሆኑ ለእንግሊዛውያን አሰልጣኞች በይፋ ፀሐይ መጥለቋ ተረጋግጧል። ፈረንሳያዊው የቀድሞው የአርሴናሉ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር ከጃፓን ሲመጡ የእንግሊዝን እግር ኳስ ባህል ይቀይራሉ ብሎ ማንም የገመተ አልነበረም። ነገር ግን የአመጋገብ ስርዓትን ከመቀየር ጀምሮ እስከ ታክቲክ አብዮት በመፍጠር ቬንገር “የማይሸነፉት” (The Invincibles) የተሰኘውን ቡድን በመገንባት አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል።
ራሱን ልዩው ሰው (The Special One) እያለ የሚጠራው ፖርቹጋላዊው ጆዜ ሞሪንሆም የቼልሲን የ50 ዓመታት የዋንጫ ጥማት ቆረጠ። ጣሊያናውያኑ አንቼሎቲ አንቶኒዮ ኮንቴ እና ሮቤርቶ ማንቺኒ የእነርሱን ፈለግ በመከተል በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ ቻሉ። ጀርመናዊው የርገን ክሎፕም በሊቨርፑል ታሪክ አዲስ የእግር ኳስ አቢዮት በማቀጣጠል የራሱን ታሪክ በደማቅ ቀለም መጻፍ ቻለ። በዚህ ሁሉ መካከል ግን እንግሊዛውያን አሰልጣኝ ተመልካች ብቻ ሆኖ ቀርተዋል።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ዲዮን ደብሊን “ከእንግሊዝ ውጪ የሚመጡት አሰልጣኞች በአውሮፓ መድረክ የተፈተኑ እና የማሸነፍን ሚስጥር ያወቁ ናቸው። ምናልባት እንግሊዛውያን የጎደላቸው ይህ የማሸነፍ ጥበብ (Know-how) ሊሆን ይችላል እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል።
እንግሊዛውያን አሰልጣኞች ፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፍ ያቃታቸው ብቃት ስለሌላቸው ነው ወይስ በትልልቅ ክለቦች እድል ስለማያገኙ? የሚለው መመለስ ያለበት አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን ቢቢሲ ስፖርት ያስረዳል። በፕሪሚየር ሊጉ ረጅም ልምድ ያላቸው ቶኒ ፑሊስ ችግሩ የእድል ማጣት እንደሆነ ያምናሉ። ባለፉት 25 ዓመታት ስንት እንግሊዛዊ አሰልጣኞች ናቸው እንደ ዩናይትድ፣ ቼልሲ ወይም ሲቲ ያሉ ክለቦችን የመሩት? ሲሉም ይጠይቃሉ። የእርሳቸው ምርጥ ፈረስ ካልተሰጠህ ውድድሩን ማሸነፍ አትችልም የሚል አንድምታ ያለው ነው።
አሰልጣኝ ጋሪ ኦኔል ግን ይህንን ሀሳብ አይቀበሉትም። “ፕሪሚየር ሊግ የችሮታ ቦታ አይደለም። የዓለም ምርጡ ሊግ እንደመሆኑ ቦታውን ሠርተህ ማግኘት አለብህ። ከውጪ የሚመጡት አሰልጣኞች በስራቸው አስመስክረው ነው የመጡት” በማለት እንግሊዛውያን አሰልጣኞች ራሳቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው ይሞግታሉ።
የቢቢሲ መረጃ እንደ ኬቨን ኪገን ያሉ እንግሊዛውያን እድሉን አግኝተው ነበር። የኪገኑ ኒውካስል እ.አ.አ በ1996 የ12 ነጥብ መሪነቱን ለፈርጉሰን አሳልፎ ሲሰጥ የእንግሊዛውያን አሰልጣኞች የስነ-ልቦና ጥንካሬ ጥያቄ ውስጥ ገባ። ከዚያ ወዲህ ሀሪ ሬድናፕ፣ ሳም አላርዳይስ እና ኤዲ ሀው በተወሰነ መልኩ ወደ ላይኛው ደረጃ ከፍ ቢሉም ዋንጫውን ለመንካት ግን አልታደሉም።
አሁን ሁሉም ዓይኖች በሊያም ሮሴኒየር ላይ ናቸው። ዕድሜያቸው 41 የሆኑት አዲሱ የቸልሲ አለቃ ሮዝኒየር ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ የመጡበት መንገድ ለየት ያለ ነው። በባለሀብቱ ቶድ ቦህሊ ኩባንያ በሆነው ከብሉኮ (BlueCo) ከፈረንሳይ ስትራስቡርግ በቀጥታ ወደ ለንደን መምጣታቸው አዲስ የመመልመያ መንገድን አመላካች ነው።
የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ዋይን ሩኒ የሮዝኒየር መሾም ለወጣት እንግሊዛዊ አሰልጣኞች ትልቅ ብርሃን እንደሆነ ይናገራል። “ወጣት እንግሊዛውያን አሰልጣኞች በትልልቅ ክለቦች እድል አያገኙም። ሮሴኒየር ይህንን እድል ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን ጠንክሮ ሠርቶ እዚህ መድረሱ ለሁላችንም ፈር ቀዳጅ ይሆናል” ሲል ተስፋውን ተናግሯል።
ሮሴኒየር በእጁ ላይ ያለው የቼልሲ ስብስብ፣ የሀብት አቅም እና የተሰጥኦ ክምችት ከዚህ በፊት እንግሊዛውያን አሰልጣኞች ካገኙት እድል ሁሉ የተሻለ ነው። ግን ይህ በቂ ይሆን? በጋርዲዮላ እና አርቴታ የበላይነት በተያዘ ሊግ ሮሴኒየር የታሪክን አቅጣጫ መቀየር ይችላል? ጊዜ የሚመልሰው ጥያቄ ነው።
በእርግጥ ተስፋው በሮሴኒየር ብቻ የተወሰነ አይደለም። የኒውካስሉ ኤዲ ሀው በብዙዎች ዘንድ ቀጣዩ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ አሸናፊ እንግሊዛዊ ለመሆን ትልቅ ግምት የተሰጣቸው ናቸው። ኒውካስልን ከወራጅ ቀጠና አንስተው ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የመለሱት ኤዲ ሀው የታክቲክ ብስለት እና የተጫዋች አያያዝ ጥበብ እንዳላቸው አስመስክረዋል።
የቀድሞው የዩናይትድ ተከላካይ ፊል ጆንስ “ኤዲ ሀው የእግር ኳስ ፍልስፍናው ዘመናዊ ነው። ጊዜ እና ነጻነት ከተሰጠው ያንን ወርቃማ ዋንጫ ወደ እንግሊዛዊ እጅ የመመለስ አቅም አለው” ሲል ይመሰክራል። እንዲሁም ፍራንክ ላምፓርድ በኮቨንትሪ ሲቲ እያደረገው ያለው የቡድን ዳግም ግንባታ ለወደፊቱ ተስፋ ሰጪ ይመስላል። ሾን ዳይችም ቢሆኑ ያላቸውን አቅም አቅልሎ ማየት እንደማይቻል መረጃው ይጠቁማል።
እርግማኑ ይሰበር ይሆን? ወይስ እንግሊዛውያን በገዛ ሊጋቸው እንግዳ ሆነው ይቀጥላሉ? መልሱን ጊዜ ብቻ ይፈታዋል፤ ነገር ግን የሊያም ሮሴኒየር ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ መግባት ለጥያቄው መልስ አዲስ ፍንጭ እና ተስፋ ሰጥቷል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


