የሕጻናት ቢጫነት ለምን ይከሰታል?

0
169

አራተኛ ልጃቸውን በሕክምና ማዕከል በቀዶ ጥገና የተገላገሉ አንድ እናት በወለዱ በሦስተኛው ቀን ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ተነገራቸው፡፡ ታዲያ እቃቸውን ሸክፈው ጤና ማዕከሉን ከመልቀቃቸው በፊት የሕጻናት ገላ  ላይ ቢጫነት ተከስቶ ችግር እንደሚያመጣ ግንዛቤው ስለነበራቸው(ከዚህ በፊት ሌሎች የሚያውቋቸው እናቶች ልጆቻቸው ቢጫነት አጋጥሟቸው አይተው ነበር)፡፡

እሳቸውም የልጃቸው  ቢጫ መሆን እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ እጁ ላይ ጫን ሲያደርጉት ምልክቱን ተመለከቱ፡፡ ልጃቸው ሲወለድ ከአራት ኪሎ በላይ መሆኑን የሚያስታውሱት ወይዘሮዋ ይህ ሁኔታ ያጋጥመዋል ብለው አላሰቡም ነበር፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ የሰሙት ክብደታቸው አነስተኛ የሆኑ ጨቅላ ሕጻናት ላይ ቢጫነት ይከሰታል የሚለውን ነበር፡፡  ችግሩን  ወዲያውኑ ለጤና ባለሙያዎች በማሳየት ለ24 ሠዓታት ሕክምና ተሰጥቶት  ሊወጣ መቻሉን ነው ያጫወቱን፡፡

አስተያየት ሰጭዋ ሕጻኑ ቢጫ ሊሆን የቻለው  የእርሳቸው  እና የልጃቸው የደም አይነት ባለመመሳሰሉ መከሰቱን በዘርፉ   ባለሙያ እንደተነገራቸው ያስታውሳሉ፡፡

የወይዘሮዋን አጋጣሚ ለማሳያነት አነሳንላችሁ እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሕጻናት በዚህ ሂደት አልፈዋል፡፡ እኛም ይህን ጉዳይ ይዘን ከባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ በፈለገ ሕይዎት ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል እና  በሐሌታ የሕጻናት ስቴሻሊቲ ክሊኒከ የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር አስቻለው ካሴ ለበኵር ጋዜጣ እንደገለጹት የጨቅላ ሕጻናት ቢጫ መሆን ማለት ከአንድ ወር በታች የሆኑ ሕጻናት ቆዳቸው ወይም ዐይናቸው ነጩ ክፍል ቢጫ ሲሆን ማለት ነው፡፡

ቢጫ መሆን የሚከሰተው የጨቅላ ሕጻናት ጉበታቸው በደንብ ያልጎለበተ ከመሆኑ የተነሳ ቢሊሩቢን የሚባለውን ኬሚካል ከደም ውስጥ እንዲወገድ ማድረግ ስለማይችል ነው፡፡ ቢሊሩቢን የሚባለው በቀይ የደም ሕዋስ ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል በሰውነት ውስጥ ከመጠን በላይ ሲኖር ቢጫነት ይከሰታል፡፡ የቀይ ደም ሕዋሳት መሰባበር እና የሞቱ ቀይ ደም ሕዋሳት  አለመወገድ ቢሊሩቢን እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ መሰረታዊ የጤና ችግሮችም ካሉ ቢጫነት ሊከሰት ይችላል፡፡

ምክንያቶቹ በርካታ እንደሆኑ የሚያስረዱት ባለሙያው፤ የሚከተሉትም ለጨቅላ ሕጻናት ቢጫ መሆን እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነሱም፡- የተፈጥሮ ቢጫነት እንደተወለዱ የቀይ ደም ሕዋስ መቀነስ፣  የእናት እና የልጅ የደም አለመመሳሰል ማለትም  እናት አር ኤች ነጌቲቭ ወይም ሾተላይ ካለባት ሕጻኑ አር ኤች ፖዘቲቭ ከሆነ፣ ሌላኛው ደግሞ የደም ወገኗ ከሕጻኑ የተለየ ከሆነ ለአብነትም የእናት የደም አይነት ኦ(o) ሆኖ የሕጻኑ ከኦ ውጭ ከሆነ፣ በወሊድ ጊዜ በሚፈጠሩ አደጋዎች (በወሊድ ወቅት ሕፃኑ የመጋጋጥ/የቆዳ ስር መጥቆር) አጋጥሞት ከነበር ደም በመከማቸት ብዙ ቀይ የደም ሴሎች ሲሞቱ የቢሊሩቢን ኬሚካል መጠን ስለሚጨምር ለቢጫነት ይዳረጋሉ፡፡ የተለያዩ ኢንፌክሽኖችም ቢጫነትን ያመጣሉ፡፡

እንደ ጤና ባለሙያው ማብራሪያ ብዙ ጊዜ ታፍነው የሚወለዱ ሕጻናትም ቢጫ ይሆናሉ፡፡ ቀይ የደም ሕዋስ በብዛት ካለ፣ የሰውነት የፈሳሽ እጥረት ያለባቸው ሕጻናት፣ የመወለጃ ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ሕጻናት ጉበታቸው ስለማይዳብር ቢሊሩቢንን አያስወግድም፡፡ ጡት በደንብ ያልጠቡ ሕጻናት፣ ከተወለዱ በ24 ሠዓታት ውስጥ የመጀመሪያውን አይነምድር  ካልተጸዳዱም ቢጫነት ይከሰታል፡፡ በአጋጣሚ እናት የደም ግፊት ካለባት ልጁ ክብደቱ ሊያንስ ይችላል፡፡ ክብደታቸው አነስተኛ ሆነው የሚወለዱ ሕጻናት ደግሞ ቀይ የደም ሕዋሳታቸው ይጨምራል፤ በዚህም ለቢጫነት ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ዶ/ር አስቻለው እንዳስረዱት ብዙ ጊዜ እንደሕመም የሚቆጠረው ወይም የከፋ ነው የሚባለው ጨቅላ ሕጻናት በተወለዱ በ24 ሰዓታት ውስጥ ቢጫነት ከተከሰተባቸው ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ቢጫነት ይባላል፡፡ ቢጫነት በተወለዱ እስከ ሁለት ሳምንት ባለው ጊዜ መከሰቱን ልብ ይሏል፡፡ ወይም ደግሞ ቢጫነቱ እንደየ እድሜው እና የቢሊሩቢን መጠን ይለያያል፡፡  ከሁለት ሳምንት በላይ የቆየ ቢጫነት እንደ ሕመም ስለሚቆጠር በደንብ ሕክምና ያስፈልገዋል፡፡ ከመጠን በላይ ሲሆን የሚያስከትለው ጉዳትም ከፍተኛ ነው፡፡

ምልክቶቹ፦

ጨቅላ ሕጻናት እንደየ ቢጫነት ደረጃቸው ምልክቶቹም እንደሚለያዩ ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡ ቢጫነቱ በዐይናቸው ነጭ ክፍል ይጀምራል፤ ከዚያም በፊታቸው፣ በደረታቸው አለፍ ሲልም እስከ እግራቸው ድረስ  ይታያል፡፡ እየበረታ ሲሄድም መጥባት መቀነስ እና መጥባት አለመቻል፣ የሙቀት መጨመር፣ የአተነፋፈስ መዛባት፣ የልብ ምት መጨመር ወይም መቀነስ ያጋጥማል፡፡  ማንቀጥቀጥ እና ራስ እስከመሳትም ያደርሳል፡፡

ሕክምና ቶሎ ካልተደረገላቸውም በፊት የነበራቸው የሰውነት ቅርጽ ይቀየራል፡፡ አንገታቸው ይጎብጣል፡፡ ለሞት የማጋለጡ ሁኔታ እንደየ ምክንያቶቹ ቢለያይም ብዙ ጊዜ ከእናቶች የደም አይነት ጋር ባለመገናኘት የተከሰተው ቢጫነት ለሞት ይዳርጋል፡፡  ከሞት ቢተርፉም ሲያድጉ  ልጆች ራሳቸውን ማንቀሳቀስ የማይችሉ፣ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው እና ለሚጥል በሽታ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡

ሕክምናው፦

ዶ/ር አስቻለ እንዳብራሩት ሕክምናው እንደየ ቢጫነቱ መንስኤ ይለያያል፡፡ የመጀመሪያው ጨቅላ ሕጻናትን በበቂ ሁኔታ ፀሐይ ማሞቅ ተገቢ ነው፡፡ እናቶች ልጆቻቸው ቢጫነት እንዳለባቸው ካሰቡ ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ የመጀመሪያው ተግባራቸው መሆን አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ  ፊት  እና ዐይን ላይ ቢጫነት ሲኖር ቀላል ስለሚሆን በደም ሥራቸው ፈሳሽ(ግሉኮስ) በመሥጠት ይታከማል፡፡ ሌላው ደግሞ የጨረር ሕክምና (phototherapy) ሲሆን በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የቢሊሩቢን መጠን በሰገራ እና በሽንት እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ ከጨረር ሕክምና በላይ ከሆነ ደግሞ የሕጻኑ ደም ተወግዶ በሌላ ይተካል፡፡

ሌላው  የሕጻኑ ቢጫነት መንስኤ በተፈጥሮው ከኢንዛይም እጥረት ከሆነ ሌሎች በአፍ የሚሰጡ መድሃኒቶች አሉ፡፡

መከላከያዎቹ፦

ዶ/ር አስቻለው እንዳስረዱት አንዲት እናት  ነፍሰጡር መሆኗን ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ የወሊድ ክትትል ማድረግ እና በጤና ተቋማት ውስጥ መውለድ እንደሚጠበቅባት ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡ በክትትሏም የደም ወገን ስለሚታወቅ የሚወለደውን ጨቅላ ሕጻን ከቢጫነት መታደግ ይቻላል፡፡  በተለይ ሾተላይ(አርኤች ኔጋቲቭ) መሆናቸውን ማረጋገጥ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን በማድረጓም ቀድሞ ቢጫነትን ለመከላከል ይረዳል፡፡

ሌላኛው ደግሞ እናቶች ከወለዱ በኋላ ጨለማ ክፍል ውስጥ መቀመጥ የለባቸውም፡፡ ብርሐን ያለበት ቦታ መሆናቸው የሕጻኑን የቆዳ ቀለም ለመለየት ያስችላቸዋል፡፡ በሰውነት ውስጥ ያለው ፈሳሽ ተጠብቆ እንዲቆይ በበቂ ሁኔታ ጡት ማጥባት፣  ከጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል አንዱ የሆነውን እንጥል ማስቆረጥንም ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም እንጥል በሚቆረጥበት ጊዜ በዙ ደም ስለሚፈስ እና የብዙ ፈሳሽ ከሰውነት መወገድ ደግሞ ለቢጫነት ይዳርጋል፡፡

በተጨማሪም ወላጆች የጨቅላ ሕጻናት ልጆቻቸው ዐይን እና ቆዳቸው ላይ ቢጫነት እንዳለ ካስተዋሉ፣ አለመጥባት ካለ፣ ያልተለመዱ የሰውነት እንቅስቃሴዎች ካጋጠማቸው ወደ ጤና ተቋማት በፍጥነት እንዲሄዱ መክረዋል፡፡

*በዓለም ላይ ከተወለዱ 100 ሕጻናት መካከል 60ዎቹ ቢጫነት ያጋጥማቸዋል፡፡

 

ጤና አዳም

 

*ሕጻናት በተወለዱ ከሁለት እስከ አራት ቀናት ውስጥ የቆዳና የዐይን ነጩ ክፍል ቢጫ መሆን ይጀምራል::

*የልጅዎ ቆዳ መልክ ወደ ቢጫነት መቀየሩን ለማወቅ የልጅዎን የግንባር፣አፍንጫ፣ እጅ ቆዳ ጫን ጫን በማድረግ በተጫኑበት ቦታ የቆዳው ቀለም ወደ ቢጫነት መቀየር አለመቀየሩን ያረጋግጡ::

*ያለጊዜያቸው/ከ38 ሳምንታት የእርግዝና ጊዜ በታች የሚወለዱ ሕጻናት የመውለጃ ጊዜያቸው ደርሶ ከሚወለዱት ሕጻናት አንፃር ሲታዩ ቢሊሩቢንን የማስወገድ አቅማቸዉ የቀነሰ ነዉ::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here