የጥር ወር ለባሕር ዳር ልዩ ገጽታ የሚያላብሳት ወቅት ነው። ጥርን በባሕር ዳር በሚል በርካታ ሳቢ እና አጓጊ ሁነቶችን እያስተናደች ነው፡፡ የንግድ ኤግዚቪሽን፣ የባሕል ፌስቲቫል፣ የከተማ ማስዋብ ዘመቻ፣ የብስክሌት እና የጀልባ ሽርሽር (በጣና ሐይቅ ደሴቶች)፣ የባሕል ኤግዚቪሽን (በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ኮሪደር)፣ ከጥር 11 ባሻገር በሌሎች አቢያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ቀናት የሚከበሩት የጥምቀት በዓላት (የሰባሩ ጊዮርጊስን ጨምሮ)፣ ቃና ዘገሊላ (በግዮን ናይል ቪው ሰገነት)፣ የታንኳ ውድድር (በፈለገ ግዮን ሪዞርት)፣ የቁንጅና ውድድር እና ፋሽን ሾው (በግዮርጊስ ኮሪደር)፣ የባሕል ምሽት (በሙሉዓለም የባሕል ማዕከል)፣ የምግብ መጠጥ ፌስቲቫል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው “ከተማዋን ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ ለጎብኚዎች እና ለኗሪዎች የተመቸችና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል።
“ክልሉ ሰፊ ቱባ ባሕልና ዕሴት ያለው እና የማንነታችን መገለጫ በመሆኑ ጠብቀን ማቆየትና ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል” ነው ያሉት።
ከተማ አሰተዳደሩ ጥርን በባሕርዳር እያሳደገ በመምጣት በ30 ቀን እንዲከበር ሲያደርግ ዋናው ዓላማም ማንነትን እና ማኅበረሰብን ለማስተዋወቅ ለውን ጉልህ ድርሻ ማጠናከር ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የጥምቀት በዓልን በጣና ዳርቻ በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር የገለፁት ክቡር ከንቲባው እስከ ጥር 30 ባሕርዳር ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን በደመቀ መልኩ የሚከበር በመኾኑ ጎብኝዎች በቦታው ተገኝተው የማይረሳ ጊዜ እንዲያሳልፉ ጥሪ አድርገዋል።
ጥርን በባሕር ዳር ዝግጅቶች ባሕርዳር የቱሪዝም ፀጋዎች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ነው። መልካም አጋጣሚውን በመጠቀም ባሕሎችን እና ዕሴቶችን በወጉ ማስተዋወቅ ይገባል።
በተመሳሳይ ጥርን በባሕር ዳር እና የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ የማኅበረ ቅዱሳን ባሕር ዳር ማዕከል ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ውይይት አካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አዲስ ትርፌ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች በከተማዋ የሚገኙ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመጎብኘት ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
የጥምቀት በዓልም ባሕር ዳርን ከሚያደምቁ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ያነሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ ጥርን በባሕር ዳር በሚል የሚከበሩት ሁነቶች የከተማዋ ድምቀቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አሥራት አርዓያ (ዶ/ር) የጥምቀት በዓል ሀገራዊ ፋይዳ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ለውይይት አቅርበዋል።
ተመራማሪው እንዳሉት የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባለፈ ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር፣ የጋራ ዕሴቶችን በማጠናከር ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል፡፡
በተለይም ደግሞ በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያውያንን ወደ ማዕከላዊ መንግሥቱ ያሰባሰበ በዓል መሆኑን ነው የገለጹት። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ አንድነቷ ቀስ በቀስ ያቀራረበ በዓል እንደነበር ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ዜጎች ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ዕውቀት የሚገበዩበት የባሕል ትምህርት ቤት ተደርጎም ይወሰዳል ነው ያሉት። በሕዝቦች መካከል የባሕል ትስስር፣ የጋራ ዕሴት እና ማኅበራዊ ተግባቦት እንዲሁም መቀራረብን የሚፈጥር የአደባባይ በዓል እንደሆነም ገልጸዋል።
ተመራማሪው ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳላቱት በበዓሉ ላይ የሚከናወኑ የአባቶች ጸሎት፣ ቡራኬ እና የማጽናኛ ቃላት (ትምሕርት) ሥነ ልቦናን ብሎም ማኅበራዊ መረጋጋትን ይፈጥራል። ይህን ለማሳካት ደግሞ ከውጭ ባሕል አፍቃሪነት ወጥቶ ለራስ ባሕል ቅድሚያ መሥጠት ይገባል።
ቤተክርስቲያኒቱን ያሳተፈ የሥነ ምግባር ደንቦችን በማዘጋጀት ማስተማር፣ ሊቃውንቱን ያሳተፈ ማኅበረሰብ አቀፍ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተመራማሪው አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት፣ ቤተክርስቲያን እና ሌሎች አጋር አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የጥምቀት ትርጉም፣ ታሪካዊ ዳራ፣ ሀገራዊ ፋይዳ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች ላይ የተዘጋጁ ጽሑፎች ቀርቦው ምክክር ተደርጓል።
የጥምቀት ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ዳራውን አሥመልክቶ ጥናት ያቀረቡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማዕከል የሐዲስ ኪዳን መምህር ኃይለ ማርያም ዘውዱ የጥምቀት በዓል ዋነኛ መነሻው ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ መሆኑን ገልጸዋል።
መምህር ኃይለማርያም እንዳሉት ኢትዮጵያ የጥምቀት ሥርዓትን ማክበር የጀመረችው ከ34 ዓ.ም ጀምሮ ነው። በተለይም ደግሞ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት በዓሉ በአደባባይ መከበር ጀምሯል። በስድስተኛው መቶ ከፍለ ዘመን በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመን ከቅዱስ ያሬድ ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ ጀምረዋል።
በቅዱስ ላልይበላ ዘመን ደግሞ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተናጠል ይፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል በማስቀረት በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተሰባስበው በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ተደርጓል። ይህም የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ቅንጅት እና ድምቀት እንዲኖረው አድርጓል።
በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዓተ በዓል ተጠናከሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትዕዛዝ መተላለፉምንም መምህሩ አንስተዋል። በንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ዛሬ እየተከበረ ለሚገኘው በዓል ትልቅ መሠረት የተጣለበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።
በዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት ማንኛውም የሃይማኖቱ ተከታዮች ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ ማውረድ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡
በጎንደር ዘመነ መንግሥታትም ቋሚ የጥምቀት ቦታዎች ለጥምቀት ተብሎ የተሠራበት ዘመን ነበር። በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን በዓሉ ከሃይማኖታዊነቱ ባለፈ የብሔራዊ አንድነት ምልክት እየሆነ መጣ። መሳፍንቶች እና መሪዎች ሕዝቡን ሰብስበው ወታደራዊ ትርኢቶች እና የፈረስ ጉግስ የሚቀርብበት ማኅበራዊ መድረከ እየሆነ እንደመጣ ገልጸዋል።
በዓሉ በ2012 ዓ.ም በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ የቱሪስት መስህብ ተደርጓል። አሁን ላይ በበዓሉ አከባበር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ክንወኖቹን ቤተ ክርስቲያኗ በባለቤትነት መምራት እንዳለባት አሳስበዋል።
ከበዓላት አስቀድሞ ስለ አከባበሩ መንፈሳዊ መመሪያ መስጠት፣ በበዓላት ሥም የሚዘጋጁ ተቃራኒ ዝግጅቶችን ማስቆም፣ አለባብስንም ሆነ መሰል ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን እንዲታረሙ ቀድሞ ማስገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እና ሕጉ በሚያዝዘው መንገድ እንዲከበር ሁሉም ሊሠራ እንደሚገባ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። የሃይማኖቱ ተከታዮች በተለይም ደግሞ ወጣቶች የቤተ ክርስቲያኗን ሕግ እና ሥርዓት መረዳት እና መጠበቅ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ሃይማኖታዊ ዕሴቱን ባልጣሰ መንገድ ጠቃሚ ባሕላዊ ዕሴቶችንም ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አጫጭር መረጃ
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች፡-
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት
የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
የአፄ ፋሲል ግቢ
የአክሱም ሀውልቶች
የአዋሽ ወንዝ የታችኛው ሸለቆ
የኦሞ ወንዝ የታችኛው ሸለቆ
የጥያ ትክል ድንጋዮች
የሐረር ጁጎል ግንብ
የኮንሶ መልካምድራዊ ገጽታ
የጌዴዎ ባህላዊ ገጽታ
ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ
መልካ ቁንቱሬ እና ባልቺት የአርኪዮሎጂና ፓሊዮንቶሎጂ ቦታዎች
የመስቀል በዓል አከባበር
የጥምቀት በዓል አባበር
ፊቼ ጨምባላላ
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።


