የሕዝብ አንድነትን የሚጠይቀው የጋራ ቤት

0
40

የሰላም ዋጋ የሚታወቀው ሲጠፋ ቢሆንም ሰላምን ለመገንባት የሚከፈለው መስዋዕትነት ግን ሁልጊዜም ጦርነት ከሚያስከትለው ኪሳራ ያነሰ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያሳያሉ::

ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ “ሰላም የሁላችንም የጋራ ቤት ናት፤ ቤቱ ሲፈርስ ግን ሁላችንም በረንዳ ላይ እንቀራለን” ሲሉ ነው የሰላምን ዋጋ ያስገነዘቡት፤ በእርግጥም የሰው ልጅ የመኖር ተፈጥሯዊ መብቱ እንዲከበር፣ ያለ ስጋት ወጥቶ ለመግባት፣ ሠርቶ ለማትረፍ፣ የተትረፈረፈ ምርት ለማምረት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሰላም ዋጋው ከፍ ያለ ነው::

በተመሳሳይ “ሰላም የሌለው ሀብት እንደሌለ ይቆጠራል፤ ሰላም ያለው ድህነት ግን የተስፋ መጀመሪያ ነው” ይባላል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙ የሰላም እጦቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና አሳድረዋል:: ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ በአማራ ክልል የቀጠለው የሰላም እጦት ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል::

የሰዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል፤ ይህም ከባድ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስን አስከትሏል:: አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወድመዋል፣ ሚሊዮን ተማሪዎችም ከትምሕርት ገበታ ተፈናቅለዋል::

ችግሩን ለመፍታት ታዲያ ምክክርን እንደ መውጫ መንገድ በመመልከት ሕዝባዊ ውይይቶች በተደጋጋሚ ተካሂደዋል፤ በዚህም አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል::

በተካሄዱት ውይይቶችም ነዋሪው የሰላም እጦቱ ያስከተላቸውን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ዘርዝሯል፤ ሁሉም ወገን ምክክርን በማስቀደም ክልሉ ወደነበረበት ሰላም እንዲመለስ ማድረግ እንደሚገባም ነው የጠየቁት::

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ውይይቶች ተካሂደዋል፤ ከእነዚህ መካል ደግሞ በደቡብ ጎንደር እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተካሄዱት ሕዝባዊ ውይይቶች ይጠቀሳሉ:: በውይይቶቹም ሕዝቡ ችግሩ ከዚህ በላይ ቤታችንን ማንኳኳቱ ማብቃት አለበት ብሏል:: በሁሉም ነገር ከባድ ጉዳት ደርሶብናል፤ ከዚህ ባላይ ልንጎዳ አይገባም:: ሁላችንም ሰላምን ማንገስ ይገባናል፤ በሁለቱም ወገን እየሞተ ያለው የእኛው ወገን ነው:: ግጭቱ በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ነው፤ የምናውቃቸውን ሁሉ መመለስ ከእኛ ይጠበቃል የሚሉት በሕዝባዊ ውይይቶች የተነሱ መሠረታዊ ነጥቦች ናቸው::

በፍኖተ ሰላም ከተማ በነበረው የሰላም ውይይት ወቅት መነጋገር ዋናው ከቀውስ የመውጫ መንገድ መሆኑን የሀገር ተሳታፊዎች ተናግረዋል:: የሰላም መደፍረስ በሚያጋጥምበት ወቅት ችግሩ ተባብሶ የሰው ሕይወት ከማጥፋቱ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት ከመገደቡ፣ ልማትን ከማቀዝቀዙ፣ የኑሮ ውድነትን ከማባባሱ፣ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ከማድረጉ ውጪ ሌላ ትርፍ እንደሌለው በማንሳት ሰላምን ለማስፈን በተለይ የሀገር ሽግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በትኩረት እንዲሠሩ ይጠበቃል ብለዋል::

እስካሁን የተደረጉ ተደጋጋሚ የሰላም መድረኮች ሰላም እንዲሻሻል ማድረጋቸውን ተናግረዋል፤ አሁንም ከዚህ በላይ በመናበብ የተሟላ ሰላም ማምጣት እንደሚገባም አሳስበዋል::

በመራዊ ከተማ በነበረው የሕዝብ መድረክም ተመሳሳይ ሐሳብ ነው የተነሳው፤ በግጭቱ ምክንያት ትምሕርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ሕጻናትም እንዳይማሩ ሆኗል፤ መምህራን እንዳያስተምሩ አለፍ ሲልም ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል:: ይህ ደግሞ ነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ያሳጣናል፣ የትውልድ የተማረ ትውልድ ቅብብሎሹም አደጋ ውስጥ ይገባል ነው ያሉት::

በተመሳሳይ ግጭቱ በርካታ ባለሀብቶች እንዲሰደዱ፣ ሰዎች እንዲታገቱ፣ ብዙዎች ሠርተው ባለማደራቸው ምክንያት በረሀብ ውስጥ ኑሯቸውን እንዲገፉ ማድረጉን አንስተዋል:: እነዚህ ችግሮችም ማኅበራዊ ዕሴቶች እንዲሸረሸሩ ማሳያዎች ተደርገው ተነስተዋል::

ግጭቱ ያስከተላቸውን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ያነሱት ነዋሪዎች ይበጃል ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችም አንስተዋል፤ ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ታሪክ የማይረሳው ሥራ መሥራት ሊያበቃ ይገባል ያሉት በውይይቶቹ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች “ጦርነት በእኔ ትውልድ ይብቃ ማለት የሁሉም መርህ ሊሆን ይገባል:: ሁላችንም ወደ ቀድሞ ሕይወታችን ተመልሰን እንድንኖር ወገኖቻችን ወደ ሰላም እንዲመጡ እናድርግ” ብለዋል::

“ትናንት ወገናችንን ሲበላ በዐይናችን ያየነው እሳት ነገ እኛንም እንደሚበላን በመገንዘብ ሁላችንም ስለ ሰላም እንነጋገር፣ አትራፊ በሌለው የትጥቅ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖቻችንን ተመለሱ እንበል” ሲሉም ተወያዮቹ ጥሪ አቅርበዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል፤ ይህን ተከትሎም በርካቶች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል:: ይህንን ያሞገሱት ተወያዮቹ፣ የሰላምን አማራጭ የሚቀበሉትን ወደ ቀደመ ሥራቸው መመለስ፣ መገለል እንዳይሰማቸውም ተገቢውን አቀባበል ማድረግ፣ ፍቅርንም ማሳየት እንደሚገባ ጠቁመዋል::

ተወያዮቹ እንደተናገሩት አንድነት የሁሉም ነገር መሠረት ነው፤ አድዋ ድል ደግሞ የዚህ ዋና ማሳያ ነው:: ይህም ታዲያ ዛሬም ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል:: የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም አስተማማኝ እና ዘላቂ ለማድረግ የተጀመሩ ምክክሮች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል::

በደቡብ ጎንደር ዞን በላይ ጋይንት ወረዳ        በነበረው የሰላም መድረክም ሠላምን ማስፈን የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑ ተነስቷል:: ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል:: በጋራ መሥራት፣ በተለይ ምሁራን የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል:: በተመሳሳይ የሥራ ዕድልን ማስፋት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ድርሻው የጎላ መሆኑም ተነስቷል::

ጦርነትን ለማቆም ብቸኛው መንገድ ጦርነትን ማሸነፍ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ የልብን ቁስል የሚፈውስ እርቅ ማውረድ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ:: በሳይንስ ልብ-ወለድ አባትነት (The Science Fiction) እና በዓለማት ጦርነት (Wars of the World) መጽሐፋቸው የሚታወቁት እንግሊዛዊ ጸሐፊ ሀርበርት ጆርጅ ዌልስ “እኛ ጦርነትን ካላጠፋን፣ ጦርነት እኛን ማጥፋቱ አይቀሬ ነውና” ይላሉ:: ይህን ጽንሰ ሐሳብ ወደ ተግባር በመተርጎም በርካታ ሀገራት ከመበታተን ድነዋል፤ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎችም በቀውስ ውስጥ የነበሩ ሀገራት ማሳያዎች ናቸው:: ሀገራቱ ጦርነት ሀገራቸውን ከመበታተኑ በፊት በሰላማዊ አማራጭ መታደግ እንደቻሉ የአፍሪካ የሰላማዊ ግጭት አፈታት ማዕከል (ACCORD) ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል::

ሩዋንዳ በ100 ቀናት ውስጥ 800 ሺህ ሕዝቧን በእርስ በእርስ ግጭት አጥታለች:: መሠረተ ልማቷ ወድሞ እና ሕዝቧ ተከፋፍሎ ከነበረበት አስከፊ ችግር ወጥታ ዛሬ ለዓለም ምሳሌ ሆናለች። ሰላም ማለት ጦርነት ማቆም ብቻ ሳይሆን አዲስ እና የጋራ ማንነት መፍጠር፣ እውነትን ተጋፍጦ ይቅር መባባል እና የሕዝብን ኑሮ መቀየር መሆኑን የሩዋንዳ ተሞከርሮ አብነት ያደረገው የማዕከሉ መረጃ ያስገነዝባል::

የአፓርታይድ ሥርዓትን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ያጋጠመው ዘርን መሠረት ያደረገ መድሎ የፈጠረው ቀውስ ሀገሪቱን ለመበተን እንደሚዳርጋት ፍንጮች ታይተው ነበር:: ይሁን እንጂ ቀድሞ በተሠራው የሰላም አማራጭ መቀልበስ የተቻለበት መንገድ ጦርነት ሁሌም የሚሸነፈው በሰላማዊ ንግግር ለመሆኑ ሌላኛው አስረጂ ነው::

ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ የሚያጋጥሟትን ግጭቶች እና ጦርነቶች በሰላማዊ መንገድ የመቋጨት ተሞክሮ እንዳላት የሰሜኑን ጦርነት የቋጨችበት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንዱ ማሳያ ነው:: አሁንም በአማራ ክልል ውስጥ ያለው የሰላም እጦት እንዲያበቃ ሰላማዊ አማራጮችን አሟጦ የመጠቀም ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል::

ሕዝቡ ለሰላም ይተጋል፤ ታጣቂ ኃሎችም ክልሉና ሕዝቡ ከዚህ በላይ የከፋ ጉዳት ማስተናገድ የለባቸውም በሚል ወደ ሰላም እየመጡ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል::

በአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ትብብር “ሰላምን ማፅናት፣ ጸጋን ማልማት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዶ በነበረው የፓናል ውይይት ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል::

መንግሥት ከግጭቱ በፊት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላም  ሕግ ከማስከበር ባለፈ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል:: በዚህም በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን በመከተል እየገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል:: “ይህም ክልሉ ወደተሻለ ሰላም እንዲመጣ እያገዘው ነው” ብለዋል::

በግጭት  እና በጦርነት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይቻል ርእሰ መሥተዳደሩ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል:: መንግሥት አሁንም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል::

የክልሉን የተሟላ ሰላም ለማረጋገጥ  ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል በኃላፊነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥር 18  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here