ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምንድን ነው?

0
110
GUI (Graphical User Interface) concept.

ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኤ አይ) ከሳይንስ ልብወለድ ገጾች ወደ እውነታ ተሸጋግሯል:: ከስማርት ስልኮች እና ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ ሆስፒታሎች፣ ባንኮች፣ ፋብሪካዎች እና ሚዲያዎች ድረስ የሰው ሠራሽ አስታውሎቶች አሁን ሰዎች እንዴት እንደሚግባቡ፣ እንደሚሠሩ፣ እንደሚማሩ እና ውሳኔዎቻቸው ላይ ጭምር ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው:: ይህ ለውጥ በአንድ ጀምበር አልተከሰተም:: ከበርካታ አስርት ዓመታት የምርምር እና  የድካም ውጤቶች በኋላ  ነው::

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ማለት ማሽኖች ወይም የኮምፒውተር ሥርዓቶች በተለምዶ የሰውን አዕምሮ የሚጠይቁ ተግባራትን የማከናወን ችሎታ ማለት ነው::  እነዚህ ተግባራት ከልምድ መማርን፣ ቋንቋን መረዳት፣ ምስሎችን መለየት፣ ችግሮችን መፍታት፣ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንዲሁም እንደ ሙዚቃ፣ ሥነ-ጥበብ እና የዜና መጣጥፎች ያሉ ይዘቶችን መፍጠርን ያካትታሉ::

ሰው ሠራሽ አስተውሎት አንድ ነጠላ ቴክኖሎጂ ሳይሆን ሰፊ መስክ ነው:: የሰውን ቋንቋ እንዲረዱ እና እንዲናገሩ ማስቻል ነው:: የኮምፒውተር ማሽኖች ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እንዲተረጉሙ መፍቀድም ነው:: አስቸጋሪ የቀዶ ጥገናዎችን የሚያደርጉ፣ በጦርነት ቦታ ሰዎችን ተክተው የሚዋጉ፣ ምርምር የሚያካሂዱ፣ አስተናጋጆች እና ጥበቃዎች በማሽን እየተተገበሩ እንደሚገኙ ሪሰርች ጌት (www.researchgate.net)ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል::

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥቅም ላይ የዋለው በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር በ1956 ነበር:: የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲው  ጆን ማካርቲ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሚለውን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋለው ወይም የተጠቀመ ሳይንቲስት ነው::

ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የማሰብ ችሎታን (Intelligence) በሰው ሠራሽ ሥርዓቶች (Artificial Systems) ውስጥ መፍጠር ነው:: በጥቅሉ የኮምፒውተር ሳይንስ ቅርንጫፍ ሲሆን ማሽኖች የሰውን ልጅ አዕምሯዊ ተግባራት እንዲፈጽሙ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው:: ዋና ዓላማው ኮምፒውተሮች የሰው ልጅ አዕምሮ የሚሠራቸውን ውስብስብ ተግባራት ለአብነትም ምስልን መለየት፣ ድምጽን መረዳት፣ ወይም ቋንቋን መተርጎም እንዲያከናውኑ ማስቻል ነው::

ለአብነትም ስልክዎን በፊት ገጽታዎ  (Face ID) ሲከፍቱ ካሜራው እርስዎን መለየት መቻሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት  ሥራ ነው:: ሰው ሠራሽ አስተውሎት  ንግግርን ይረዳል፣  ውሳኔ ይሰጣል:: ለአብነትም ዩቲዩብን (YouTube) እርስዎ የወደዷቸውን ቪዲዮዎች መሠረት በማድረግ “ይህንን ትወዱታላችሁ?” ብሎ ሌላ ቪዲዮ እንዲያዩ ሲመክርዎ አንዱ ማሳያ ነው::  ጎግል ካርታን በመጠቀምም  (Google Maps) የትራፊክ መጨናነቅን ተንትኖ ወደ መድረሻዎ ፈጣኑን መንገድ ሊመርጥልዎ ይችላል::በዚህም  በትራፊክ መጨናነቅ ያጋጠመዎትን መዘግይት መፍትሔ ይሰጥወታል::

ሳንዲያጎ ኤድዩኬሽን (sandiego.edu)ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው በሰው ሠራሽ አስተውሎት  ሊተገበሩ የሚችሉ ዘርፎች በጣም ሰፊ እና የተለያዩ ናቸው:: አዳዲስ የአጠቃቀም ጉዳዮችም በየጊዜው እየወጡ ነው:: በሰው ጉልበት የሚከናወኑ አሰልቺ እና ተደጋጋሚ ሥራዎችን በፍጥነት ያዘጋጃል::  በንግድ ተቋማት ውስጥ ለኩባንያዎች የደንበኞችን ፍላጎትና የድጋፍ ጥያቄዎችን የማስተናገድ እና የመመለስ ሥራን በመሸፈን የሰው ኃይል ወደ ሌሎች የሥራ ዘርፎች እንዲሰማራ ያስችላል:: በተመሳሳይ በማምረቻው ዘርፍ ለሰው ልጆች ፈታኝ እና አደገኛ የሆኑ የሥራ ዘርፎችን ሮቦቶች ተክተው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው::

በጤና አጠባበቀ ዘርፍም  እንደ ኤም.አር.አይ እና ሲቲ ስካን የመሳሰሉ ምርመራዎች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሽታን እና በሰውነት ውስጥ ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን በከፍተኛ ጥራት መለየት ያስችላል::

በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኘው ሰው ሠራሽ አስተውሎት መኖሪያ ቤትን እና  ስማርት ሲቲን ማለትም እንደ ትራንስፖርት፣ ኢነርጂ እና የቆሻሻ አያያዝ ያሉ ሥርዓቶችን በኢንተርኔት በመታገዝ እና መረጃ ትንተናን በመጠቀም ሥራዎችን ለማመቻቸት እና ጥራት ያለው ሕይዎትን በማጎልበት የከተማ ኑሮን ያሻሽላል::

አገልግሎቶችን ቀልጣፋ፣ ዘላቂ እና ለነዋሪዎች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ዲጂታል ቴክኖሎጂን እና ዳታን ይጠቀማል::  በመኖሪያ ቤት ውስጥ ሙቀትን እና የቤት ብርሐን በሚፈገው መጠን ማስተካከል ይችላል::

በትምህርት ዘፍርፉም ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ተጨባጭ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው:: በሰው ሠራሽ አስተውሎት  የተደገፉ የመማሪያ መድረኮች ተማሪዎች በራሳቸው ዘይቤ እና ፍጥነት እንዲማሩ እየረዳቸው ነው:: አኗኗርን ዘመናዊ ለማድረግ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው:: በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመታገዝ የእለት ተዕለት ተግባራት እና እቅድን በመቆጣጠር እንዲሁም በማንቃት እና ምክረሃሳብ በማቅረብ ሥራዎችን እያሳለጠ  ነው::

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) አንዱ ወሳኝ ተጽዕኖ የሚኖረው በፋይናንስ ዘርፍ ነው:: ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለመተንተን እና የፋይናንስ ተቋማት ተአማኒነት ያለው እና ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን ያስችላል:: ለምሳሌ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የተጭበረበረ ግብይትን ለመለየት እና የገበያ አዝማሚያን ለመተንበይ ይጠቅማል:: ከዚህ በተጨማሪም ለግለሰቦች የኢንቨስትመንት ምክረሃሳብ ያቀርባል::

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥራን  እና የደንበኞችን እርካታ ለማሻሻል ጠቃሚ ነው:: በሰው ሠራሽ አስተውሎት የበለጸገ ቻትቦት(  የሰዎችን ንግግር በጽሑፍ ወይም በድምጽ የሚያስመስል፣ ለደንበኛ አገልግሎት፣ መረጃን ለማውጣት ወይም ለግል የርዳታ ተግባራት የሚያገለግል፣ የተጠቃሚ ግብዕት ደንቦችን  በመተንተን የሚሠራ የኮምፒዩተር ፕሮግራም ነው:: ደንበኞችን ለመርዳት፣ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና ደንበኞች የሚፈልጉትን ለማሳወቅ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው::)  መረጃን በመተንተን ለደንበኞች መልዕክት ያስተላልፋል::

በተጨማሪም ሰው ሠራሽ አስተውሎት የሕዝብ መጓጓዣ(ትራንስፖርት) አገልግሎትን ለማዘመን፣ መጨናነቅን ለመቀነስ እና የጉዞ ሰዓትን ለማሻሻል ጥቅም ላይ እየዋለ ነው:: በግብርናው መስክ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) የሰብል ምርትን ለማሳደግ እና ብክነትን ለመቀነስ ጥቅም ላይ ይውላል:: በሰው ሠራሽ አስተውሎት የጎለበተ መሳሪያ የአፈርን ርጥበት ደረጃ፣ የሙቀት መጠን እና ሌሎች የአካባቢ ሁኔታዎችን በመከታተል አርሶ አደሮች ለመዝራት እና ለማጨድ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያግዝ መረጃን ያቀርባል::

በአጠቃላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደየ አየር ንብረት ለውጥ እና የጤና አጠባበቅ ያሉ  የዓለምን አንገብጋቢ ፈተናዎች ለመፍታት ጥቅም ላይ ይውላል:: የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት፣ የአየር ሁኔታን ለመተንበይ እና ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ ክስተቶች ለጎርፍ እና ድርቅ የተጋለጡ አካባቢዎችን ለመለየት ያችላል:: በተጨማሪም አዳዲስ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ለማዳበር እና የኢንዱስትሪዎችን የካርቦን መጠን ለመቀነስ ግልጋሎት ላይ ይውላል::

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ በአፍሪካ ልማት ባንክ የወጣ አዲስ ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳመላከተው  እ.አ.አበ2035  አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ላይ እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ሃብት ሊጨምር እንደሚችል ገልጿል:: ይህም የአህጉሪቱን አሁናዊ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ምርት አንድ ሦስተኛውን ያህል ነው::  በዚህም አህጉሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ዕድገት ተመራጭ ከሆኑ አካባቢዎች አንዷ ያደርጋታል::

ሰው ሠራሽ አስተውሎት በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ከታወቀበት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሕዝቡን፣ ኢንዱስትሪውን እና ኢኮኖሚውን በፍጥነት በመለወጥ ላይ ይገኛል:: እ.አ.አ. በ2025 መገባደጃ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሰዎች መካከል አንዱ 16 ነጥብ ሦስት በመቶ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሳሪያዎችን ለሥራ፣ ለመማር ወይም ለዕለት ተዕለት ተግባራት እንደተጠቀመ ተረጋግጧል:: ከአራት ዓመት በኋላም (በ2030)  50 በመቶ የሚሆነው በሰው ልጅ ጉልበት ይከናወን የነበረው ሥራ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ይተካል ተብሎ ይጠበቃል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በርካታ ጠቀሜታዎች ቢያስገኝም ሚስጥር ሊያባክን ይችላል፣ ለሳይበር ጥቃት ሊዳረግ ይችላል፣ሀሰተኛ መረጃ ሊሰጥ ይችላል፣ በርካታ ሠራተኞችን ከሥራ ገበታቸው ሊያፈናቅል ይችላል፤ የሚል ሥጋት መፍጠሩም አልቀረም:: ሆኖም በቀጣይ ቴክኖሎጂው ይበልጥ እየዘመነ ሲሄድና ሲሻሻል በርካታ ሠራተኞችን ከሥራ ገበታቸው ሊያፈናቅል ይችላል ከሚለው ስጋት ውጪ ሌሎች እንደ ሥጋት የተጠቀሱ ነገሮች ይስተካከላሉ ተብሎ ይጠበቃል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥር 18  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here