በዶሮ እርባታ የተለወጠዉ ሕይወት

0
157

ወ/ሮ ኢክራም ሙሐመድ በደሴ ከተማ አሥተዳደር ቀበሌ 10 ነዋሪ ናት። ወይዘሮዋ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሠርታ ለመለወጥ ባላት ፍላጎት ወደ አረብ ሀገራት  አቅንታ ነበር፡፡ አሁን ላይ ወደ ሀገሯ ተመልሳ በዶሮ እርባታ ዘርፍ መሰማራቷን ነው ለበኵር ጋዜጣ በስልክ የተናገረችው።

“ኢክራም፣ ዛሕራ እና ጓደኞቻቸው” በሚል ስያሜ   እሷን ጨምሮ በአምስት አባላት የተቋቋመው  ማህበራቸው የአንድ ቀን ጫጩት በማምጣት አሳድገው ለከተማው ነዋሪ እና ለአርሶ አደሩ እያስረከቡ መሆኑን ነግራናለች።

እንደ ወይዘሮ ኢክራም ገለጻ   እያንዳንዳቸው ዶሮዎች  በዓመት እስከ 340 እንቁላል ይጥላሉ። በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ የዶሮ እርባታ የጀመረችው ወ/ሮ ኢክራም አሁን ላይ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባዘጋጀው ለዶሮ እርባታ የሚያገለግል ሼድ ከጓደኞቿ ጋር  በጥቃቅን ተደራጅታ ተጠቃሚ ሆናለች፤ ኑሮዋም ተሻሽሏል።

አባላቱ በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በኩልም ባገኙት ሙያዊ ድጋፍ ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ነግራናለች። ለዶሮ እርባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች (ምጥን መኖ፣ የመኖ ጥሬ ዕቃዎች፣ የክትባት መድኃኒት፣ መጠለያዎች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች) በወቅቱ እና በበቂ ሁኔታ ከቀረቡ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻልም ወይዘሮ ኢክራም  ሐሳቧን አጋርታናለች።

ሌላኛው በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሠማርቶ እየሠራ የሚገኘው የጎንደር ከተማ ነዋሪው ወጣት ካሳሁን በሬ ነው። ካሳሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2006 ዓ.ም በእንስሳት  ሕክምና በዲግሪ እንደተመረቀ ተናግሯል። ቀድሞም በዶሮ እርባታ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት የነበረው ካሳሁን፤ በ2009 ዓ.ም ከአንድ ጓደኛው ጋር 50 ሺህ ብር ከአበዳሪ ተቋማት ተበድረው የግለሰብ ቤት በመከራየት ነበር ሥራውን የጀመሩት። አሁን ላይ “ካሳሁን፣ መሠረት፣ ሰለሞን እና ጓደኞቻቸው” በሚል ማኅበር በመደራጀት ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።

የከተማ አሥተዳደሩ ሙያዊ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር  200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሼድ ሠርቶ እንዳስረከባቸው እና የነበረባቸው የቦታ ችግር እንደተፈታ ካሳሁን  ገልጿል። የከተማ አሥተዳደሩ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እንዳመቻቸላቸውም ጠቅሷል።

የመኖ ዋጋ መናር ትልቅ ፈተና ቢሆንም ይህን ታግሎ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ጠቁሟል። ዶሮ እና እንቁላል ለበዓላት ለአርሶ አደሩ ያቀርባሉ። ለዶሮ እርባታ አስፈላጊ ጥንቃቄ እንደ ሚያስፈልገው የተናገረው አቶ ካሳሁን፤ የጤና እንክብካቤ፣ የመኖሪያ ቦታው ፅዱ መሆን እና የተመጣጠነ መኖ በበቂ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ እንቁላል ጣይ እና ሦስት ሺህ የስጋ ዶሮዎችን እየተንከባከቡ  እንቁላል ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ካሳሁን የገለጸው።

ወጣቶቹ የአንድ ቀን ጫጩት ተረክበው በማሳደግ ከ45 ቀን በኋላ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም ተናግሯል። በቀጣይ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ ዘዴን በመጠቀም በተሻለ መንገድ አሥፋፍቶ ለመሥራት በሂደት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ዘርፉ በትንሽ ቦታ እና ገንዘብ በመጀመር ብዙ ማትረፍ የሚቻልበት በመሆኑ ወጣቱ በዚህ ዘርፍ ቢሰማራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ካሳሁን ጠቁሟል፡፡ በተለይ የገቢ ማስገኛ ሥራ የሌላቸው ሴቶች እና ወጣቶች ተገቢውን ሥልጠና ወስደው ወደ ዘርፉ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ነው ተሞክሮውን ያጋራን።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃደ ጸጋው በከተማ አሥተዳደሩ የእንስሳት ሃብት ልማትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ለበኵር በስልክ ተናግረዋል። የዶሮ እርባታ እና የእንቁላል ምርትን በማሳደግ በኩልም የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት የዶሮ እርባታ ጠቀሜታን በመረዳት በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ዶሮ አርቢው በተነሳሽነት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው የገበያ ትስስር ችግርም እንደሌለ አመልክተዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የአንድ ቀን ጫጩት  እና የእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ በስፋት  እየተከናወነ ነው። ለዘርፉ እድገትም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 29 ሼዶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።

የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት የዶሮ ዝርያን ለማግኘት ችግሮች ቢኖሩም አሁን ላይ ግን ኮምቦልቻ የዶሮ እርባታ ይህንን ችግር ለመፍታት ወደ ተግባር መግባቱን አስረድተዋል። የዶሮ እርባታ ሥራ የዝቅተኛ ኅብረተሰብ ክፍል ሥራ አድርጎ የማየት አስተሳሰብ ተቀይሮ የተማሩ ግለሰቦችም በዘርፉ ተሰማርተው እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዳይነሳ ከሥራ እና ክህሎት ጽ/ቤት ጋር በቅንጅት ተናበው እንደሚሠሩም ኃላፊው ጠቁመዋል። የብድር አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከባንኮች ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ ነው።

የመኖ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ኃላፊው፤ ከመኖ አካፋፋዮች ከባሕር ዳር እና ከደብረ ዘይት እንዲሁም ከኢትዮ ቺክን እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

በከተማዋ በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ 40 ኢንተርፕራይዞች፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮ ማርባት ስድስት ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ መኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል። ዘርፉ የባለሙያን ክትትል የሚፈልግ በመሆኑ በቅርበት የባለሙያ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት። አዳዲስ የሚመጡ የዶሮ ዝርያዎችን ለአርቢዎች የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ ነው። እንዲሁም አርቢው በራሱ ቦታ እና በትንሽ ቦታ ማርባት እንደሚቻል ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው።

ዘርፉ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆንም የመሥሪያ ቦታ የሚሆኑ ሼዶችን ገንብቶ ለዶሮ አርቢዎች በማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሚገኝ ኃላፊው ጠቁመዋል። ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ከቦታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች መኖራቸውን አምነው ከተማ አሥተዳደሩ ዶሮን በክላስተር ለማርባት በከተማው ገራዶ አካባቢ  በአንድ ነጥብ ስምንት ሄክታር መሬት ላይ 65 ሚሊዮን ብር አውጥቶ እየገነባ ይገኛል። ይህም አዲስ ለሚደራጁ ሥራ ፈላጊዎች እንደሚሆን አመላክተዋል።

በቀጣይ አምስት ዓመት የሞላቸውን ኢንተርፕራይዞች ደረጃቸውን ከፍ እያረጉ አዲስ ለሚደራጁ ኢንተርፕራይዞች እየተሰጠ ነው ብለዋል። በዘርፉ ለሚሰማሩ ወጣቶች አስፈላጊውን ሥልጠና፣ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋልም ብለዋል።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለሙያ አቶ ዜናው ይታይህ በበኩላቸው  በ2018 ዓ.ም እስካሁን በእንቁላል አምራች አንድ ሺህ 602 ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በአንድ ቀን ጫጩት  ተረክበው ለማሳደግ 670 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተዋል። 20 ሺህ 116 ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠረ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ባለሙያው፤ የመሥሪያ ቦታ እና መነሻ ካፒታል ዋናዎቹ ናቸው። ይህንን ችግር ለመፍታት በከተሞች የሼድ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው። ሼዶቹ በተጠናከረ መንገድ እንዲገነቡ እና  የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲሳተፉም እየተደረገ እንዲሁም ለአርቢዎቹ አስፈላጊ ሥልጠና፣ ክትትል እና ድጋፍ እስከ ቀበሌ ድረስ እየተሰጠ ነው።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ የዶሮ ሃብት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙላቱ ዳኘው እንዳሉት ደግሞ በ2018 ዓ.ም 26 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማቅረብ ታቅዶ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ማቅረብ ተችሏል። ከእቅዱ አኳያ ዝቅተኛ አፈፃፀም ቢሆንም በቀጣይ ወራት ሌሎች ተጨማሪ የጫጩት መፈልፈያ ፋብሪካዎችንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለማሥገንባት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት የኮምቦልቻ የዶሮ ብዜት ማዕከልን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ከፍተኛ ባለሙያው አንስተዋል። ዘርፉ ሰፊ ግብዓት የሚጠይቅ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችን እና ኢንቨስት የሚያደርጉ አካላትን የማስተባበር እና የመቀስቀስ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የተመጣጠነ የዶሮ መኖ ከማቅረብ ጀምሮ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች የተለያዩ የዶሮ ዝርያዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአካባቢያዊ የዶሮ ዝርያን ለማሻሻል በፓኬጅ ተቀርፆ እስከ ቀበሌ ድረስ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናኑንም ከፍተኛ ባለሙያው ጠቁመዋል። የአንዳሳ የእንስሳት ምርምር  ማዕከል እና የኮምቦልቻ ዶሮ ብዜት ኢንተርፕራይዝ እያቀረቡ መሆኑን ገልፀዋል። የዶሮን የጤና አጠባበቅ፣ የተሻሻለ መኖ አቅርቦት እና ዝርያን ማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ግብዓቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል

መረጃ

በክልሉ አገልግሎት እየሰጡ ካሉት የዶሮ ዝርያዎች መካከል፦

የእንቁላል ዶሮ ዝርያዎች

  • ሎህማን (ብራውን፣ዋይት)
  • ቦቫንስ ብራውን (ዋይት)

የስጋ እና የእንቁላል  ዶሮ ዝርያዎች

  • ኮይኮይክ
  • ሳሶ (T44) comercial dual

የስጋ ዶሮ ዝርያዎች

  • ሃባርድ
  • ሮዝ
  • ኮብ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

የመረጃ ምንጭ፦ የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 18   ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here