መሬት ለአርሶ አደሮች የኢኮኖሚ፣ የማንነት እና የታሪክ ሕብረት በሆነ መልኩ የማይነጣጠል የሕይወት መሰረት ነው። ነገር ግን በተለያዩ ወቅቶች በሀገራችን ብሎም በክልላችን በነባሩ የገጠር መሬት አሥተዳደር ሥርዓቶች እና የሕግ ማዕቀፎች ውስንነት ምክንያት ይህ መሰረታዊ ሀብት ዘላቂነት ያለው አያያዝ፣ አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓት ተበጅቶለት በጥንቃቄ ባለመመራቱ ለግጭት፣ ለክርክር፣ ለውዝግብ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች መነሻ ሆኖ ቆይቷል።
ጠንካራ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓት መኖር ለሰላም መስፈን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለገጠሩ ማኅበረሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። ይህንን መሰረት በማድረግም የአማራ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፤ 5ኛ ዓመት፤ 11ኛ መደበኛ ጉባኤው የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ማሻሻያ አዋጅን አጽድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አዲሱን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ አስመልክቶም ጥር 04 ቀን 2018 ዓ.ም መግለጫ ሰጥቷል። አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ የመሬት ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እና ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለውም በመግለጫው ተመላክቷል።
አዋጁ ለመሬት ባለይዞታዎች ጠቃሚ መብቶችን ይዞ የመጣ መሆኑን የተናገሩት የክልሉ መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ናቸው። የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ በርካታ ጥቅሞችን ይዞ መምጣቱንም አስረድተዋል።
ቢሮ ኃላፊው እንደተናገሩት አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው። ካሁን በፊት በነበሩ ሕጎች የመሬት ይዞታ ለውጥ በአሥተዳደር ወሰኖች የታጠረ እንደነበር ገልፀዋል:: ይህ አዋጅ ግን ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ ሳይገድበው ማንኛውም ባለይዞታ የመሬት ልውውጥ በአሥተዳደራዊ ወሰን ሳይገደብ ማካሄድ እንደሚቻል ተደንግጓል ነው ያሉት::
የኢፌዲሪ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ መሻሻል የክልሉን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ በማሻሻል በኩል እንደሁነኛ ምክንያት ተወስዷል:: በመሆኑም በሥራ ላይ የቆየው የክልሉ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ እንዲሻሻል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች የክልሉን ነባራዊ ሁኔታዎች ባገናዘበ መልኩ አዋጁ መዘጋጀቱን ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል::
አዋጁ ከገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የታዩ ችግሮችን ለማቃለል እና በዘርፉ የተጠቃሚውን መብት በማስፋት መሬትን ወደ ልማት እና ወደ ዘላቂ የሰላም መሰረት ለመቀየር የተዘጋጀ ነው ብለዋል። አዋጁ አዳዲስ እሳቤዎችን፣ ዓለም አቀፍ የአሠራር ደረጃዎችን፣ ፍልስፍናዎችን፣ የመሬት መረጃ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶችን፣ የመረጃ ደህንነትን፣ ጥራት እና ሌሎች ጠቃሚ አሠራሮችን ያካተተ መሆኑንም ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ ዘላቂ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሥርዓትን በማስፈን የክልሉን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በዘላቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል:: አዋጁ ሲወጣ በየደረጃው የሚገኙ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሕግ ምርምር ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እና ተጨማሪ ግብዓት የተገኙበት ነው። በመሆኑም ክልላዊ ማሻሻያ አዋጁን ለማዘጋጀት ሰፊ ጊዜ ተወስዶ በርካታ አካላትንም ባሳተፈ መልኩ እንዲዳብር ተደርጓል:: የበርካታ ባላድርሻ አካላት እና የገጠር መሬት ባለይዞታዎችም በስፋት መክረውበት ረጅም ጊዜ ተወስዶ በተደጋጋሚ ታይቶ እንዲፀድቅም የተደረገ አዋጅ ነው።
አዋጁ ካሁን በፊት በከተማ መሬት ሊዝ አዋጅ ትርጉም እና በገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ መካከል በተሰጠ የትርጉም ልዩነት ምክንያት በርካታ የገጠር መሬት ባለይዞታዎችን ላልተገባ የመልካም አሥተዳደር ችግር የዳረገ፤ የከተማ እና የገጠር መሬት አሥተዳደር ተቋማትን ላልተፈለገ መገፋፋት ያበቃ ጉዳይ ነው::
በመሆኑም ይህ አዋጅ የአርሶ እና ከፊል አርብቶ አደር የመሬት ይዞታዎች ወደ ከተማ ክልል ሲካተቱ የባለይዞታዎችን ዋስትና ለማስቀጠል የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ወይም ተግባር እና ኃላፊነት ማካተቱ በግልፅም ማስቀመጡ እንደ ትልቅ ለውጥ የሚወሰድ ጉዳይ መሆኑ ተጠቁሟል::
የአዋጁ ዝርዝር ድንጋጌዎቹ በተለይ ወቅቱን የዋጀ፣ ዘመናዊ እና ሳይንሳዊ መሰረት ያለው፣ ዘላቂ የገጠር መሬት አሥተዳደር፣ አያያዝ እና አጠቃቀም እንዲኖር እና የአገልግሎት አሰጣጡም ዘመኑ የደረሰበትን፣ የሀገሪቱን እና የክልሉን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግቦች ታሳቢ ያደረግ እንዲሆን በማድረግ በርካታ ቴክኒካል የአሠራር ማሻሻያዎችን ያካተተ ረቂቅ ሕግ ነው:: ረቂቅ ሕጉ በአራት ክፍሎች እና በ77 አንቀፆች ተዋቅሮ የቀረበ ነው። የአዋጁን ማስፈጸሚያ ደንብ የማዘጋጀት ሥራ መጀመሩን እና በቀጣይ መመሪያዎች እንደሚዘጋጁም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል::
የተሻሻለውን የኢፌዲሪ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 ዓ.ም አንቀፅ 60 (2) መነሻ በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሰረት በክልሉ በሥራ ላይ የቆየውን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 252/2009 ዓ.ም አሁን ላይ ዘርፉ እንደ ክልል የደረሰበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሳቤዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ከፌዴራሉ አዲስ የመሬት ሕግ ጋር አጣጥሞ በማሻሻል ሥራ ላይ ማዋል በማስፈለጉ እንደሆነም ተመላክቷል።
ሕጋዊ ተጠያቂነት
አዋጁ የመሬት አሥተዳደር ተቋማትን የሥራ ድርሻ ከላይ እስከ ታች ተጠያቂነትን ጭምር በግልጽ ማስቀመጡን ነው ቢሮ ኃላፊው ያብራሩት። የገጠር መሬት ባለይዞታው መሬቱን ለሚፈለገው ዓላማ ካልተጠቀመ የሚወሰዱ ርምጃዎችንም ያካተተ ነው ብለዋል:: ይህም በአጠቃቀሙ መሰረት ካልሠራ ከምክር ጀምሮ መሬቱን እስከ መጨረሻው ሊነጠቅ እንደሚችል በአዋጁ መካተቱን ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል:: ለምሳሌ ለእርሻ፣ ለግጦሽ ወይም ለደን ልማት ተብሎ የተለየን መሬት ለታቀደለት ዓላማ ብቻ ለማዋል አዲሱ አዋጁ ያስገድዳል።
አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ በመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሕገ-ወጥ ቤት ግንባታን ጨምሮ ለሚከሰቱ ሕግን የተላለፉ ሕገ ወጥ ተግባራት የወንጀል ተጠያቂነት እና የሚወሰዱ ርምጃዎችንም በግልጽ ያካተተ ነው። በተለይ በረቂቅ አዋጁ ክፍል 4 በልዩ ልዩ ድንጋጌዎቹ አንቀፅ 73 ንዑስ አንቀፅ 1-7 ላይ የወንጀል ተጠያቂነትን በዝርዝር ተመላክቷል።
ማንኛዉም ሰው የግል፣ የወል ወይም የመንግሥት ይዞታን በሕገ-ወጥ መንገድ የወረረ ከብር 30 ሺህ እስከ 100 ሺህ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል::
ማንኛውም ሰው በግል፣ በወል ወይም በመንግሥት ይዞታ ላይ ጉዳት ያደረሰ ከብር 50 ሺህ እስከ 150 ሺህ ወይም ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣሌ።
ማንኛውም ሰው ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ማንኛውንም ግንባታ የሠራ ወይም እንዲሠራ የፈቀደ ከብር 25 ሺህ እስከ 50 ሺህ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል::
ማንኛውም ሰው ከመሬት አጠቃቀም እቅድ ውጭ ይዞታውን ጥቅም ላይ ያዋለ ከብር 20 ሺህ እስከ 50 ሺህ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል።
ሀሰተኛ የመሬት ይዞታ ማስረጃ ያቀረበ ሰው፣ ማስረጃ የሰወረ ወይም የተሳሳተ ማስረጃ የሰጠ ባለሙያ ከብር 10 ሺህ እስከ 25 ሺህ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል::
ማንኛውም ሰው መሬት የሸጠ ወይም የገዛ እንደሆነ ከብር 100 ሺህ እስከ 200 ሺህ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል::
በዚህ አንቀፅ ከንዑስ አንቀፅ (1) እስከ ከንዑስ አንቀፅ (6) የተደነገው እንደተጠበቀ ሆኖ የፍትሀብሔር እና የወንጀል ኃላፊነትን በተመለከት ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ሌሎች ሕግጋት ድንጋጌዎች ተግባራዊ ይደረጋል። በመሆኑም መሰል የወንጀል ተጠያቂነት ድንጋጌዎች በግልፅ እና በዝርዝር በረቂቅ አዋጁ መካተታቸው ከነባር የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ሕጎች አንፃር አዳጊ ይዘት እንዳለው መረዳት ይቻላል:: ይህ በዚሁ ዘርፍ ያለውን ሙስና እና ብልሹ አሠራር ከመከላከል አንፃር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎም ይታመናል።
ሲጠቃለል ማንኛውም ሰው የግል፣ የወል ወይም የመንግሥት ይዞታን በሕገ ወጥ መንገድ የወረረ፣ ጉዳት ያደረሰ፣ ከመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ውጭ ይዞታውን ጥቅም ላይ ያዋለ፣ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ሕገ ወጥ ግንባታ የሠራ እና እንዲሠራ የፈቀደ እንዲሁም ሀሰተኛ የመሬት ማስረጃ ያቀረበ ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ25 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት በየደረጃው መቀመጡን ነው ያብራሩት።
መረጃ
የመሬት አዋጁ በአዲስ ያመጣቸው መብቶች እና ዕድሎች
መሬትን ለብድር ማስያዣነት መጠቀም፤ ብድሩን መክፈል ካልቻለም የመሬት መጠቀሚያ መብቱ ሊወሰድ ይችላል።
አርሶ አደሮች መሬታቸውን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለሌላ አካል ማከራየት ይችላሉ።
የመሬት መጠቀሚያ መብቱን እንደ ካፒታል በመቁጠር ከባለሃብቶች ጋር በሽርክና ማልማት ይቻላል።
ለእርሻ፣ ለግጦሽ ወይም ለደን ልማት ተብሎ የተለየን መሬት ለታቀደለት ዓላማ ብቻ ለማዋል ያስገድዳል።
የመሬት መጠቀሚያ መብትን ለቤተሰብ አባል በስጦታ ወይም በኑዛዜ የማስተላለፍ መብትንም ሰጥቷል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


