“ጣና በቅርቡ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ይመዘገባል”

0
267

ዶክተር አየለ አናውጤ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ የባህልና ቅርስ ዘርፍን ይመራሉ። ዶክተር አየለ አናውጤ ተወልደው ያደጉት በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ነው። ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባህር ዳር ከተማ አጠናቀዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ሶስተኛ ዲግሪያቸውን (PhD) በሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ከኖርዌይ ሀገር በጋራ (ኖርፓርት ፕሮጀክት) ሰርተዋል::

በምስራቅ ጎጃም ዞን እና በክልል ደረጃ በተለያዩ የዳይሬክተርነት እና የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅትም የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በመሆን የባህል እና ቅርስ ዘርፍን እየመሩ ይገኛሉ።

በትምህርት እና በምርምር ስራቸው ምክንያት በኖርዌይ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ እና ቤልጂየም በመዘዋወር የተለያዩ ስልጠናዎችን እና የጥናት ስራዎችን አከናውነዋል። ከዚያም ተመልሰው ለሶስት ዓመታት በአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነው። ከዶክተር አየለ አናውጤ ጋር በክልሉ የቱሪዝም መነቃቃት ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል፡፡

መልካም ንባብ!

 

የአማራ ክልል የቱሪዝም ሁኔታ እንዴት ነው የሚታየው?

የአማራ ክልል በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ የቱሪስት ጸጋዎች ያሉት ክልል ነው።  ነገር ግን ባለን ጸጋ ልክ በቱሪዝሙ እየተጠቀምን ነበር ማለት አይቻልም።

እንደዚህም ሆኖ የፌደራል መንግሥት በቱሪዝም  ኢንቨስት ማድረግ ሲጀምር በዋናነት እንደ አማራ ክልል ያሉ የቱሪዝም ጸጋ ያላቸውን ክልሎች ታሳቢ አድርጎ ነው። እኛም ያሉንን ሀብቶች፣ ቅርሶች፣ ጸጋዎች በአንድ በኩል ትውልድ ማነጽ፣ ትውልድ ማነሳሳት፣ ትውልዱ የራሱን ታሪክ እንዲሰራ በሚያደርግ መልኩ እንጠቀምባቸዋለን።

አሁን በቅርብ አመታት በተለይ በሁለት ከፍለን በአንድ በኩል የእነዚህን ባህላዊ ኩነቶች እሴት ጠብቆ ከማክበር ባለፈ የቱሪዝም ገበያ መዳረሻ እናድርግ ብለን በክረምት የሚከበሩ ክብረ በዓሎቻችን በድምቀት እንዲከበሩ፣ ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንደ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫነቀላ፣ ቡሄ የምንላቸው ክብረ በዓላት በሙሉ፣ ቀጥሎ ደግሞ ከገና ጀምሮ ያሉ ጥምቀትን ጨምሮ እስከ የካቲት ድረስ የሚሄዱ ክብረ በዓላት ደግሞ በተመሳሳይ የሀገር ውስጥም የውጭም ቱሪስት እንዲስብ እናድርግ ብለን በተከታታይ በሰራናቸው ስራዎች በጣም ብዙ ውጤቶች እየመጣን ነው።

እኛ እንደ አማራ ክልል ብዙ ጸጋ፣ ብዙ ሀብት እያለን ነገር ግን ባለፉት 46 ዓመታት በዩኔስኮ አላስመዘገብንም። ላሊበላን ካስመዘገብን፣ የጎንደር አብያተ መንግሥትን ካስመዘገብን እና ሰሜን ተራሮች ከተመዘገቡ በኋላ ላለፉት 46 አመታት አንድም ቅርስ ከአማራ ክልል አልተመዘገበም ነበር። አሁን የኢትዮጵያ ቅርስ 19 ደርሷል፤ 12 የሚዳሰስ እና 7 የማይዳሰስ።

ሰባት የማይዳሰስ ቅርስ ሲመዘገብ በጋራ የምንጋራቸው ጥምቀትና መስቀል በዓል ይኑሩ እንጂ ለብቻችን ያስመዘገብነው ባህል ግን የለም። ስንት የግጭት አፈታት ስርአት እያለን፣ ስንት ባህላዊ እሴት እያለን፣ ስንት የማይዳሰስ ጸጋ እያለን አላስመዘገብንም። በዚህ ቁጭት ባለፉት ሁለት አመታት በርካታ ስራ ሰርተን አሁን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጫፍ የደረስንባቸው አሉ።

አንዱ ጣና ሐይቅን ለማስመዝገብ ጫፍ ደርሰናል፤ ጥናቱ አልቋል፤ ለዩኔስኮ ቀርቧል፤ ዩኔስኮም ተቀብሎታል። እንግዲህ ዘንድሮ ደቡብ ኮሪያ ላይ በሚኖረው የዩኔስኮ ጉባኤ ጣና ሐይቅ በዓለም ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርስነት ይመዘገባል።

የአገው ፈረሰኞች በዓልን አጥንተን ጨርሰን ለቅርስ ባለስልጣን አስገብተናል። ወርክሾፕ ተካሂዷል፣ ቀጣይ ኢትዮጵያ ለማስመዝገብ የምታቀርበው እሱን እንዲሆን ተስማምተናል። ስለዚህ ከሚቀጥለው ዓመት በኋላ ቻይና በሚካሄደው የዩኔስኮ ጉባኤ የአገው ፈረስ በዓልን እናስመዘግባለን።

ሌላ ደግሞ ሾንኬን እያጠናን ነው፣ ጥንታዊ እስላማዊ መንደር ነው። ዘንድሮ ጥናቱን አጠናቀን ለቅርስ ባለስልጣን እንልካለን ብለናል።

የጎብኚዎች ቁጥር ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ አንጻር ምን መሻሻል አሳይቷል?

በጣም ጥሩ ለውጥ አሳይቷል። ባለፈው አመት ለምሳሌ ወደ 3.5 ሚሊዮን ገደማ ነበር የሀገር ውስጥ ቱሪስት። አሁን 10 ሚሊዮን የሚሆን የሀገር ውስጥ ቱሪስት ነው በስድስት ወሩ ክልሉን የጎበኘው። ባለፈው አመት ተመሳሳይ ስድስት ወር  11 ሺህ ገደማ የውጭ ቱሪስት ጎብኝቷል። አሁን በስድስት ወር 24 ሺህ የውጭ ቱሪስት ጎብኝቷል፤ ከእጥፍ በላይ ማለት ነው። ስለዚህ ከ2017 ከነበረው የሀገር ውስጥ የቱሪስቱ መጠን ሶስት እጥፍ ጨምሯል፤ የውጭ ሀገር ቱሪስቱ ደግሞ በእጥፍ ጨምሯል።

ይሄ የሆነበት ምክንያት ከምንም በላይ የሰላም ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ ነው። በገቢ ደረጃም ቢታይ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ያገኘንበት ነው። ይሄ በነገራችን ላይ በተለይ የውጭ ሀገር ቱሪስት አሁን 24 ሺህ ሲሆን ከሰባት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ነው። ከኮቪድ በፊት የነበረ ቁጥር ነው። ከኮቪድ በኋላ ላለፉት ዓመታት ይሄ ቁጥር ተመዝግቦ አያውቅም፤ ዘንድሮ ነው የተመዘገበው።

ክልሉ በቱሪዝም ላይ የገጠሙት ተግዳሮቶች ምንድናቸው? እንዴትስ አለፋቸዉ?

የመጀመሪያው ተግዳሮት ለዘርፉ የምንሰጠው ትኩረት አናሳነት ነው። አቅሙ እየታወቀ  ብዙ ትኩረት አይሰጥም ነበር። ይሄ በተለይ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ትኩረት ከተሰጠው በኋላ ከፍተኛ መሻሻል አለ። አሁን የአማራ ክልል ለምሳሌ በ1.2 ቢሊዮን ብር ሙዚየም እየገነባ ያለ ክልል ነው።

ሁለተኛው ፈተና የጸጥታ ችግር ያመጣው ነበረ፤ ግን የጸጥታ ችግሩንም አንዳንድ ጊዜ እንደ ወቅቱ ማለፍ ይቻላል። እኛ እንደ ምን አጋጣሚ ተጠቀምንበት መሰለህ? እሱንም አንዳንዴ ችግር ሲገጥም ቤትህን ዘግተህ፣ ቤትህን አጽድተህ፣ ብለህ እንግዳ ለመቀበል እንደምትዘጋጀው አይነት አደረግነው።

በአንድ በኩል እያስጎበኘን በሚቻለው መጠን፣ በሌላ በኩል ግን አሰራሮችን የመዘርጋት፣ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችን የማዘጋጀት፣ ፍኖተ ካርታዎችን  የመንደፍ እና የምንሰራቸውን ነገሮች የማዘጋጀት፣ እንደዚሁ ለዓለም አቀፍ ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥናቶችን የመሳሰሉትን ነገሮች እየሰራን ነው። በመሆኑም አሁን ከጸጥታ ችግር ስንወጣ ይዘን የምንመጣው ነገር ብዙ አዲስ ነገር ይኖረናል ማለት ነው። ያ ደግሞ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፤ ከችግር ስትወጣ እና እነዚህን አሁን የፈተኑን ችግሮች እየተቀረፉ ነው፤ ለውጥ እየመጣ ነው።

እንደው ቱሪዝሙ እንዲነቃቃ ከማድረግ አንጻር፣ ከመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታም ሊሆን ይችላል፣  ከሰራችኋቸው ስራዎች በጥቂቱ…

ከምንም በላይ አሁን ለቱሪዝሙ አንድ መልካም አጋጣሚ የምለው የፌደራል መንግሥት የልማት ተነሳሽነቶች ናቸው። ብዙዎቹ የቱሪዝም ተነሳሽነቶች መሆናቸው ነው። ሦስቱ የ”ገበታ” ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ናቸው። ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ አሁን የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ሦስቱም የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ናቸው። ይሄ ለኛ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ሁለተኛ ቀጥሎ የመጣው የከተማ ኮሪደር ልማት አሁንም ለቱሪዝም ትልቅ አቅም እየሆነ ነው ያለው። እየተገነቡ ያሉት አምፊ ቲያትሮች ለኪነ-ጥበብ የሚሆኑ ቦታዎች ናቸው።

ባህር ዳር ኮሪደር በመገንባቱ ምክንያት ጣናን በስምንት አቅጣጫ እንዲታይ አደረገው። የፍቅር አደባባይ ተብለው በመሰየም ትልቅ የኪነ-ጥበብ ምሽት፣ ትልልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች የሚዘጋጅባቸው ቦታዎች ሆነዋል። ጎንደር የታደሰው ቦታ አደባባዩ ትልልቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪዝም ኩነቶች የሚካሄዱባቸው እንዲሆኑ ነው። እና እነዚህ ስራዎች ትልቅ ዕድል እየፈጠሩ ነው።

ከሌሎች ሀገራት የተወሰዱ ተሞክሮዎች አሉ?

ባለፉት ሁለት ዓመታት የኛ ክልል ወደ አምስት ሀገራት ዓለም አቀፍ የባህል ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫሎች ላይ ሀገር ወክለን ተሳትፈናል። በህንድ፣ በሩሲያ፣ በቻይና፣ በቱርክ እንዲህ ባሉ ሀገራት  አድርገናል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ጉዞዎች ከቅርስ ጥበቃ አኳያ፣ ከሙዚየም አደረጃጀት አኳያ፣ ከቱሪዝም መዳረሻ ልማት አኳያ በአካል የቀሰምናቸው ተሞክሮዎች አሉ።

ሁለተኛ ደግሞ በንባብ እና ዘመኑ በሰጠን ቴክኖሎጂ አማካኝነት ደግሞ የት ምን አይነት የቱሪዝም ማስተዋወቅ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ማልማት ስራዎች መስራት ይገባል የሚለውን እያየን እየሞከርን ነው።  የሌሎች ሀገራት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ክልሎችን  ልምድ ጭምር በመጠቀም እየሰራን ነው።

በመጨረሻ ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት?

አማራ ክልል “ከዚህ እስከዚህ” የማይባል ጸጋ ያለው ክልል ነው።  ሁሉም የቱሪዝም አይነት፣ ሁሉም የቱሪዝም አይነት ፍላጎቶች ያሉበት ክልል፣ በርካታ ጸጋዎች ያሉት ክልል ስለሆነ መጥታችሁ እንድትጎበኙ እጋብዛለሁ። ሁለተኛ ከዚህ በፊት የነበረው የጸጥታ ችግሮች፣ የጸጥታ ስጋቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጠው፣ ተሻሽለው ሰላም እየተሻሻለ ነው እና እንዲመጡ እጋብዛለሁ።

ስለነበረን ቆይታ በበኩር ዝግጅት ክፍል ስም አመሰግናለሁ!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here