በኢትዩጵያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰብ እና ህዝቦች በሲዳማ ክልል አባይ ወረዳ ነው የሚገኘው- ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ::
ፓርኩ ከአዲስ አበባ 340 ከአዋሳ ደግሞ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የተመሰረተው::
ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ በአባያ ኃይቅ እና በብላቴ ወንዝ መካከል ነው የሚገኘው:: ጠቅላላ ስፋቱም 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል:: በመልካ ምድራዊ አቀማመጡ ኮረብታዎች፣ የሳር ምድር፣ ጥቅጥቅ ደን እና የብላቴ ወንዝ ተፋሰስ ስነ ምህዳርን አካቶ ይዟል::ከፓርኩ ክልል ከፍተኛው የጉዳኖ ኮረብታ 1650 ሜትር፤ ዝቅተኛው ሻላ ኦዳ 1178 ሜትር ተለክቷል::
በፓርኩ ክልል 198 የእፅዋት ዝርያዋች፣ 28 መካከለኛ እና በአካል ግዝፈት ያላቸው አጥቢ የዱር እንስሳት እና ከ200 በላይ የዓእዋፍ ዝርያዎች መገኘታቸው ተመዝግቧል- በድረ ገፆች::
ከዱር እንስሳትም አንበሳ፣ አቦ ሸማኔ፣ ጉማሬ፣ የዱር ውሻ፣ ዓዞ፣ መገኘታቸው ተረጋግጧል::
በዓየር ንብረቱ በረሀማ እና ወይና ደጋ ሲሆን አማካይ ሙቀቱ 16 ዲግሪ ሴልሺየስ ተለክቷል::
ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳቱን እና በስምጥ ሸለቆ ቀጣና በሚገኘው ትልቁ አባያ ኃይቅ ዙሪያ የሚገኝ ስነምህዳርን ለመጠበቅ ዓላማ አድርጐ ነው የተመሰረተው::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ናሽናል ፓርክ አሶሴሽን፣ አውቶሪያ፣ ፊልምፊክሰር እና ጐግል ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

