ነገ እንዴት ይገነባል?

0
93

የተማሪዎች የትምህርት ውጤታማነት በቤት እና በትምህርት ቤት መካከል ባለው ትስስር ላይ የተመሠረተ ነው። ጥናቶችና የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳዩት ወላጆች በትምህርት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ከማምጣታቸውም በላይ የተሻለ ሥነ-ምግባርም ይኖራቸዋል።

ዕውቁ የሥነ ልቦና ምሁር ሲግመንድ ፍሩድ “የአንዲት ሀገር ነገዋ የሚወሰነው በዛሬ ተማሪዎች ነው፤ ለዚህ ደግሞ የት/ቤት እና የወላጆች መስተጋብር መሠረት ነው” ይላል::

በዛሬው ጽሑፋችንም የወላጆችን፣ የትምሕርት ባለድርሻዎችን (ወላጅ፣ መምህራን፣ የት/ቤት አመራር እና ተማሪዎች) መስተጋብር በተመለከተ እናስነብባችኋለን::

ሰላማዊት ማሩ የጣና ኀይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት፤  ተማሪዎች ትምህርትን እንዲወዱ፣ ከዚያም ባለፈ ውጤታማ እና በመልካም ሥነ-ምግባራቸው አርዓያ እንዲሆኑ የቤተሰብ ክትትል ድርሻው ከፍ ያለ ነው ትላለች::

ተማሪ ሰላማዊት በትምሕርት አቀባበላቸው የተሸሉ ከሚባሉት መካል ስትሆን ለዚህም የቤተሰብ ክትትል ትልቁን አስተዋጽኦ እንደሚወስድ ነው የተናገረችው::

ተማሪዋ እንደነገረችን ትምህርት ቤት አዘውትራ እንድትሄድ፣ ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜዋንም ከፋፍላ በአግባቡ እንድትጠቀም ወላጆቿ ዘወትር ድጋፍ ያደርጉላታል:: ከትምህርት ቤት መልስም በዕለቱ ስትማር የዋለችውን የመከለስ እና የነገውን ይዘት ቀድሞ የመዘጋጀት ልምድን አዳብራለች፤ “ለዚህ ሁሉ ነገር የወላጆቼ ድርሻ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል” ነው ያለችው::

ሌሎች ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ እና ውጤት ከመጠበቅ ይልቅ ቀድመው ለመልካም ውጤት ክትትል እንዲያደርጉ ነው ያሳሰበችው::

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ደረበ ሙሉ በትምህርት ላይ የሚገኙ ሁለት ልጆች አሏቸው:: ልጆቻቸው አሁን ላይ አንደኛ እና ሦስተኛ ክፍል ላይ ደርሰዋል:: “ወደ ትምህርት ቤት መላክ ብቻውን ግብ አይደለም” የሚሉት የተማሪ ወላጁ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት የማንበብ ልምድ እና የትምህርት ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርገው አሳድገዋቸዋል::

አቶ ደረበ እንደነገሩን ልጆቻቸው መልካም ሥነ-ምግባር ኖሯቸው እንዲያድጉ ከማድረግ ባለፈ በትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራሉ፤ ትምህርት ቤት በተደጋጋሚ በመሄድም ክትትል ያደርጋሉ:: በዚህም ልጆቻቸው የማወቅ ጉጉት እንዲኖራቸው እና ሁሌም ዝግጁ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል:: እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕላቸውም ዳብሯል::

እንደ አቶ ደረበ ገለጻ ዘወትር በሳምንቱ መጨረሻ ቤተሰባዊ ግምገማ ያደርጋሉ:: ይህም የልጆች መሻሻል ምን ላይ እንደሆነ ለማወቅ ረድቷቸዋል:: የተሻለ ላስመዘገበ የማበረታቻ ሽልማቶችን፣ ዝቅተኛ ውጤት ላስመዘገበ ደግሞ በቀጣይ እንዲያሻሽል የማበራታቻ ሐሳብ ይሰጣሉ::

የአምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አሥራት ታደሰ “ልጆች በትምህርት ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ጎን ለጎንም ተሰጥኦዋቸውን እንዲያጎለብቱ የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው” ይላሉ:: ቤተሰብ ልጆቹን በሥነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ከማድረግ ጀምሮ የጊዜን ኃያልነት እንዲረዱ በማድረግ ለውጤት የማብቃት ከፍ ያለ ኃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል:: ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የመከታተል እና መምህሮቻቸው ጋር በየጊዜው መገናኘት እንደሚገባም መክረዋል::

በትምህርት ላይ የወላጆች ክትትል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በዓለም ላይ በትምህርት ጥራታቸው ቀዳሚ የሆኑ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል:: የወላጆች ንቁ ተሳትፎ እና ክትትል ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ እያስኬዱ ካሉ ሀገራት ምካከል ፊንላንድ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፤ ፊንላንድ ኢዱኬሽን ሀብ ዶት ኮም ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ፊላንዳውያን ወላጆች፣ መምህራን እና ተማሪዎች በየቀኑ የሚገናኙበት ዊልማ ሥርዓት (Wilma System) የተሰኘ የዲጂታል መድረክ አላቸው። ይህ ሥርዓት ወላጆች ስለ ልጃቸው የዕለት ተዕለት ውሎ፣ ስለሚሰጣቸው የቤት ሥራና ስለ ሥነ-ምግባራቸው ፈጣን መረጃ የሚለዋወጡበት ነው::

ጥናታዊ ጽሑፎችን የሚያስነብበው ሪሰርች ጌት (www.researchgate.educ) ደቡብ ኮሪያ እና ቻይናም ትምህርት የቤተሰብ ህልውና ማስጠበቂያ አድርገው እንደሚያዩት ጠቁሟል:: ለዚህም ልጆቻቸው ላይ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ነው:: በእነዚህ ሀገራት ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ሲሉ የግል ፍላጎታቸውን መሥዋዕት የማድረግ ዝንባሌያቸው ከፍተኛ ነው። ይህም ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እና መነሳሳት ይፈጥርላቸዋል። በተጨማሪም ወላጆች የልጆቻቸውን ጥናት የመከታተል እና ተጨማሪ አስጠኝ የግል መምህራንን (Tutors) የመቅጠር ልምድ አላቸው።

በትምህርት መልካም ተሞክሮ ሊቀሰምባቸው ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ጃፓንም የወላጆች ክትትል ጠንካራ ነው:: በጃፓን የወላጆች ክትትል በውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን በልጆች ሰብእና ግንባታ ላይ ያተኩራል።

በጃፓን ወላጆች በትምህርት ቤት ጽዳት እና በምግብ ዝግጅት ሂደት ውስጥ በፈቃደኝነት ይሳተፋሉ። ይህ ተማሪው ወላጆቹ ለትምህርት ቤቱ ያላቸውን ክብር እንዲያይ እና ለትምህርቱ ትኩረት እንዲሰጥ ያደርጋል::

በተጨማሪም ጃፓናውያን ወላጆች ልጆቻቸው ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ሰዓት እንዲያከብሩ እና በቂ የጥናት ጊዜ እንዲኖራቸው የማድረግ መልካም ተሞክሮ አላቸው::

አሜሪካ እና ሌሎች አውሮፓውያን ሀገራትም  የወላጅ መምህራን ማኅበርን (Parent Teacher Association) ለተማሪዎች መብቃት እንደ ዋና መሠረት አድርገው ይሠሩበታል:: የወላጅ መምህራን ማሕበር (PTA) በተለይ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሁሉንም ልጆች ትምህርት፣ ጤና እና ደህንነት ለመደገፍ ወላጆችን፣ መምህራንን እና የማህበረሰብ አባላትን የሚያገናኝ ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ ድርጅት ነው። ይህ ማሕበር ለትምህርት ቤት ፍላጎቶች የገንዘብ ማሰባሰቢያዎችን ያከናውናል፣ ለተማሪዎች መብትም ይሟገታል።

አውሮፓውያንም ወላጆች በትምህርት ቤቱ በጀት አጠቃቀም፣ በሥርዓተ-ትምህርት ማሻሻያ እና በትምህርት ቤቱ ደኅንነት ላይ የመወሰን ሥልጣን እንዲኖራቸው መደረጉ ተማሪዎችን ለውጤት አብቅቷል:: በተጨማሪም ወላጆች በትምህርት ቤት ቤተ-መጻሕፍት፣ በስፖርት እንቅስቃሴዎች እና በሽርሽር ጉዞዎች ላይ አብረው በመሄድ የልጆቻቸውን የትምህርት አካባቢ በቅርበት ያውቃሉ። እነዚህ ሁሉ ስልቶች ልጆች ከህጻንነታቸው ጀምሮ የትምህርትን አስፈላጊነት እንዲረዱ በማድረግ ትኩረት እንዲሰጡ ያግዛሉ::

የሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ያላቸው ተሳትፎ በጨመረ ቁጥር የተማሪዎችን በራስ የመተማመን አቅም ያሳድጋል፤ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል። በኢትዮጵያም ወላጆች ከትምህርት ቤት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከውጤት መቀበል ባለፈ ወደ የዕለት ተዕለት የልማድ ክትትል ማሳደግ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ወላጅ አቶ ደረበ ሙሉ አብነት ናቸው::

ኮረጆ

ለልጆች ብቁነትና ተወዳዳሪነት የወላጆች ሚና

ጊዜ መስጠት፡- በቀን ውስጥ ለልጆቻችሁ በቂ ጊዜ መድቡ። ዛሬ ትምህርት ቤት ምን አዲስ ነገር እንደተማሩ፣ የከበዳቸውም ካለ የመጠየቅ ልምድን ማዳበር አስፈላጊ ነው::

ደብተር መፈተሸ፦ ትምህርቱን ባታውቁት እንኳ የልጆቻችሁን ደብተር መመልከታችሁ ልጆቻችሁ በትምህርታቸው ላይ ንቁ መሆናችሁን እንዲረዱና በኃላፊነት እንዲያጠኑ ያደርጋቸዋል።

ምቹ የጥናት አካባቢ መፍጠር፦ ልጆቻችሁ በሚያጠኑበት ወቅት ትኩረታቸውን ሊሰርቁ የሚችሉ ነገሮችን መቀነስ ይገባል:: ይህም በእነሱ እንደምትተማመኑ ግልጽ መልዕክት ስለሚሰጣቸው በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን እንዲተጉ ያደርጋቸዋል::

የጥናት ጊዜ፡- የጥናት ሰዓትን እንደ መመገቢያ ሰዓት የማይቀያየር እና የማይታጠፍ ማድረግ  ይገባል::

ከመምህራን ጋር መገናኘት፦ ትምህርት ቤት መሄድ ያለባችሁ በወላጅ በዓል ብቻ መሆን የለበትም:: በየጊዜው መምህራንን በመጠየቅ ስለ ልጃችሁ ጠንካራ እና ደካማ ጎን መረጃ ማግኘት ለልጁ መሻሻል ወሳኝ ነው።

አበረታቱ እንጂ አትቆጡ፦ ውጤት ሲቀንስ ከመጮህ ወይም ከመገረፍ ይልቅ ችግሩ የት ላይ እንደሆነ አብራችሁ ፈልጉ። “ትችላለህ፣ ጎበዝ ነህ” የሚል አዎንታዊ ቃል ከቁጣ በላይ የመለወጥ ኃይል አላቸው።

ምንጭ፡- https://www.researchgate.net

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here