የመጀመሪያዉ ዙር  ፉክክር እና የክለቦች የቤት ሥራ

0
108

የዘንድሮው የኢትዮጵያ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ  የመጀመሪያው ዙር ውድድር በሀዋሳ እና በጅማ ከተሞች ተደርጎ ተጠናቋል። 20 ክለቦች በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ከአማራ ክልል ደሴ ከተማ እና ደ/ብርሃን ከተማ ክለቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች በምድብ ሁለት ተደልደለው እየተፎካከሩ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ጥሩ የውድድር ጊዜ ማሳለፋቸውን ያስመዘገቡት ነጥብ ያሳያል።

ጋሞ ጨንቻ በ21 ነጥብ እየመራ ከምድብ አንድ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል። የካ እና ባቱ ከተማ በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። ከምድብ ሁለት ሀላባ ከተማ በ22 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ የመጀመሪያውን ዙር ሲጨርስ 16 ነጥብ ያለው ደሴ ከተማ አዲስ ከተማን በግብ ክፍያ በልጦ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። ደ/ብርሃን ከተማ ደግሞ በ14 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ይዞ መጨረሱን የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያስነብባል።ድልነሳው ሽታው ከየካ ክ/ከተማ እና አማኑኤል ግዛቸው ከደሴ ከተማ ክለብ በእኩል ስድስት ግቦች ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆነው እየመሩ ይገኛሉ።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ የወንዶች ከፍተኛ ሊግ  የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከመቼውም ጊዜ በላይ ታክቲካዊ ብልጫዎች፣ የመከላከል ጥበብ እና የውጤት መዋዠቅ የታየበት ሆኖ ነው የተጠናቀቀው።   በሊጉ ለመቆየት የሚደረገው ፉክክር ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከሚያደረገው ፉክክር ያልተናነሳ የሞት ሽረት ትግል እየታየበት ነው።

ከምድብ ሁለት ሀላባ ከተማ አስደናቂ ጉዞ እያደረገ ይገኛል፤ እስካሁን በሊጉ ካደረጋቸው ዐስር ጨዋታዎች ውስጥ አልተሸነፈም፤ ይህም ክለቡ ምን ያህል ጠንካራ የኋላ ደጀን እንደገነባ ማሳያ ነው፤ ሁለት ግብ ብቻ እንደተቆጠረበትም ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከመሪው ሀላባ ከተማ በስድስት  ነጥብ ርቆ  ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደሴ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ካደረጋቸው ዐስር የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች አራቱን አሽንፏል፤ በተመሳሳይ በአራት መርሀግብሮች ነጥብ ተጋርቶ ሲውጣ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው የተሸነፈው።

ደሴ ከተማ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ ቀዳሚ አስፈሪ የፊት መስመር ግንብቷል፤ የፊት መስመሩ በመጀመሪያው ዙር በአጠቃለይ 15 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በአማካይ በየጨዋታው ከአንድ ግብ በላይ የማስቆጠር ብቃት እንዳለው አስመስክሯል። የኋላ ክፍሉ ደግሞ ስድስት ግቦች ብቻ ተቆጥሮበታል።  ደሴ ከተማ ምንም እንኳን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቢሆንም ከመሪው ሀላባ ከተማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት መስፋቱ ለክለቡ አመራሮችም ሆነ ለአሰልጣኞች የቡድን አባላት እረፍት  የሚሰጥ አልሆነም።

የደሴ ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ጌታቸው ከአሚኮ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት እስከ መጨረሻዋ እስትንፋስ ድረስ ታግሎ በመጨረሻው መርሀግብር በአርሲ ነገሌ ተበልጦ ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ እድሉን ያጣበት አጋጣሚ በክለቡ ቤተሰቦች ዘንድ የፈጠረው ቁጭት ቀላል እንዳለሆነ ተናግሯል። ያንን መጥፎ ትዝታ ለመፋቅ ዘንድሮ ክለቡ በአማካይ በየጨዋታው ከአንድ ግብ በላይ የማስቆጠር ብቃት እንዳለው አስመስክሯል።  ከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ ክለቡን እንደ አንድ ትልቅ የልማት ፕሮጀክት በመቁጠር በበጀት እና በሞራል ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ቢኒያም ተናግሯል። “የዘንድሮው ዕቅዳችን አንድ እና አንድ ነው፤ እርሱም የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊነትን ማረጋገጥ ነው”ሲል ሥራ አስኪያጁ ዕቅዳቸውን ያስረዳል።

ይሁን እንጂ የክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በታሰበው ፍጥነት አለመጀመሩ እና የአመራር ለውጥ ሂደቶች መዘግየት በመጀመሪያዎቹ ዙር ጨዋታዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር አቶ ቢኒያም ጌታቸው ተናግረዋል። የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድኑ በሊጉ ካሉ ክለቦች አንጻር ልምድ ባላቸው እና ጥሩ ስም ባላቸው ተጫዋቾች የተገነባ ቢሆንም ይህ ጥንካሬ በአንዳንዶች ዘንድ የተሳሳተ መዘናጋትን ፈጥሮ እንደነበር አልሸሸገም። “ተጫዋቾቻችን የፕሪምየር ሊግ እጩ ነን የሚል የራስን አቅም አግዝፎ የመመልከት ስሜት በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ላይ አሳይተዋል” የሚሉት አሰልጣኙ ይህም ዋጋ እንዳስከፈላቸው እና  ነጥብ እንዲጥሉ ምክንያት መሆኑን አልሸሸጉም።

አሁን ግን የቡድኑ ወቅታዊ አቋም ድብልቅልቅ ካለ ስሜት ወጥቶ ወደ መረጋጋት እየመጣ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሦስት እና አራት ጨዋታዎች ላይ አጥቂዎቹ ያሳዩት የአጨራረስ ብቃት ተስፋ ሰጪ ነው።  “ግብ ጠባቂ ላይ በጣም ወሳኝ እና አስተማማኝ ሰው ያስፈልገናል፤ እንዲሁም በመሀል ተከላካይ እና አማካይ ቦታዎች ላይ ክፍተቶች አሉብን” ሲሉ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የቡድኑን የቴክኒክ ችግሮች ለይተው አስቀምጠዋል።

ይህንን ክፍተት ለመቅረፍም ለሁለተኛው ዙር ውድድር ጥር 20 በተከፈተው እና እስከ ይካቲት 17 በሚቆየው የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት በመጠቀም አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ዕቅድ መያዛቸውን አሰልጣኙ አብራርተዋል። “ያሉብንን ክፍተቶች መድፈን ከቻልን እና ያለንን የማጥቃት ኃይል ይበልጥ ካጠናከርን ከመሪው ሀላባ ከተማ ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ ብቻ ሳይሆን የሊጉን ዋንጫ አንስተን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ እንችላለን” የሚል ጽኑ እምነት አላቸው አሰልጣኙ። ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም እንዳሉት “ደጋፊዎቻችን ከጎናችን ከሆኑ እና እኛም የቤት ስራችንን በአግባቡ ከሰራን የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊነታችንን በሜዳ ላይ እናረጋግጣለን” ብለዋል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ያለውን ፉክክር ይበልጥ ውስብስብ ያደረገው ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አቋም ነው። በ14 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደብረ ብርሃን ከተማ ከደሴ ከተማ በተለየ የጨዋታ ባህሪ ይዞ ቀርቧል። ደብረ ብርሃን ከተማ ለመሸነፍ የሚከብድ፣ ለማሸነፍም የሚቸገር አይነት ቡድን ሆኖ በመጀመሪያው ዙር ታይቷል። ካደረጋቸው ዐስር ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱን አሸንፈዋል፤ በሁለቱ ሲሸነፍ አምስቱን በአቻ ውጤት አጠናቋል። ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ስምንት ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ አስቆጥረዋል፤ በተመሳሳይ  ስምንት ግብ ደግሞ ተጥሮበታል።

ይህም ጨዋታን አሸንፎ ለመውጣት የሚያስችል ገዳይ የፊት መስመር አቅም የሌለው መሆኑን ነው። ክለቡ  ምንም እንኳን በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ቢመስልም የበዙት የአቻ ውጤቶች ከመሪዎቹ ጋር ያለውን ርቀት ማጥበብ እንዳይችል አድርገውታል። በአሁኑ ሰዓት ከንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ከመንጌ ቤንሻንጉል ክለቦች ጋር በእኩል 14 ነጥብ መቀመጡ በአንድ ጨዋታ መሸነፍ ወይም አቻ መውጣት እስከ ስድስተኛ ደረጃ ሊያወርደው የሚችልበትን ስጋት ፈጥሮበታል። ክለቡ በሁለተኛው ዙር ውድድር በሁሉም የሜዳ ክፍል ያሉበትን ክፍተት ቀርፎ ካልተመለስ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ በፉክክር ለመቆየት ይቸገራል-የብዙዎች አስተያየት ነው።

የሊጉ የታችኛው ክፍል ላይ ያለው ፉክክርም ቢሆን ከላይኛው ባልተናነሰ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ጠንካራ ፉክክር አሳይቶናል። አዲስ አበባ ከተማ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል በሰባት ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ተቀምጧል። ይህ የታችኛው ክፍል ፉክክር በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ለተቀመጡ ቡድኖችም ትልቅ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም  የመዳን ተስፋ ካላቸው ቡድኖች ጋር የሚደረጉ ጨዋታዎች ያልተጠበቀ ውጤት ይዘው ሊመጡ ስለሚችሉ ነው።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር በሀላባ ከተማ የመከላከል ጥበብ፣ በደሴ ከተማ የማጥቃት ኃይል እና በደብረ ብርሃን ከተማ የአቻ ውጤት የበዛበት ሆኖ አልፏል።  ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ ውድድር በታክቲክ፣ በጉልበት እና በስነ-ልቦና የበላይነት የሚወሰን ይሆናል፤ በሁለተኛው ዙር የደሴ ከተማ የግብ ማሽን የሀላባ ከተማን የብረት ግድግዳ ይሰብረው ይሆን?  ደብረ ብርሃን ከተማ ከአቻ ውጤት አዙሪት ወጥቶ መሪዎቹን ይቀላቀላል? የሚሉት ጥያቄዎች በሁለተኛው ዙር ምላሽ የሚያገኙ ይሆናል።

የሁለተኛ ዙር ውድድር የካቲት 22 እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል። ምድብ አንድ በጅማ፣ ምድብ ሁለት ደግሞ በሀዋሳ ከተሞች ቀጥሎ የሚደረግ ይሆናል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here