በርካታ አሰልጣኞች በአጨዋወቱ ዘመናዊ አጥቂ እንደሆነ ይናገሩለታል፤ ተፈጥሮአዊ ተሰጥኦን ከጠንካራ ሥራ ያዋሃደ ኮከብ ነው፡፡ እንደ ፌራሪ በሚጋልበው ፍጥነቱም ይታወቃል፤ ፍጥነቱን ሳይቀንስ አቅጣጫን በድንገት የመቀየር ብቃቱ የተጋጣሚዎችን ሚዛን ያስታል፤ በተጋጣሚ የኋላ ክፍል ሽብር በመፍጠርም ይታወቃል። ግብ የማሽተት ብቃቱ እና በተጋጣሚ የግብ ክልል አደጋ የመፍጠር ብቃቱ ከፈተኛ ነው። እርሱ ለሴኔጋላውያን ተስፋ ነው፤ ለአፍሪካውያን ኩራትም ነው- ሴኔጋላዊው አጥቂ ሳዲዮ ማኔ።
ማኔ በታክቲካዊ ብስለት እና በሥራ ተነሳሽነት ወደር እንደሌለው አብረው የተጫወቱት ሁሉ ይመሰክራሉ፤ እግር ኳስን በጥበብ እና በውበት ይጫወታል፤ እንደ ወታደር ደግሞ በዲሲፕሊን የሚዋጋ ልዩ የፈጠራም ባለቤት ነው። ከምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻዎች ተነስቶ በዓለም ታላላቅ ስታዲየሞች የንግሥና ዙፋን ላይ እስከመቀመጥ የደረሰው ሳዲዮ ማኔ በሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሮ ታይቷል።
በሞሮኮ ሰማይ ስር የሳዲዮ ማኔን የመሪነት ጥግ እና ወደር የለሽ ትህትና ተመልክተናል። ከእግር ኳስ ክህሎቱ በላይ የመሪነት ተሰጥኦውን አጉልቶ አሳይቷል። የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ለሳዲዮ ማኔ ከወጣት ኮከብነት ወደ ታላቅ መሪነት (Statesman) የተሸጋገረበት እንደነበር የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አስነብቧል። በከባድ ፉክክር ወቅት እንኳን ለተጋጣሚ ቡድኖች የነበረው አክብሮት ለዳኞች የነበረው ትህትና እና ለደጋፊዎች የሰጠው ፍቅር እውነተኛ መሪ በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ምን መሆን እንዳለበት ያስተማረበት አጋጣሚ እንደነበር የካፍ ኦንላይን መረጃ ያስነብባል።
ማኔ የተወለደው እጅግ ድሃ ከሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቱ የመንደሩ “ኢማም” ነበሩ። እግር ኳስ በቤተሰቡ ዘንድ እንደ እርባና ቢስ ነበር የሚታየው፤ የልጅነት ህልሙን እውን ለማድረግ መጀመሪያ የራሱን ቤተሰብ መጋፈጥ ግድ እንዳልው ከካፍ ኦንላይን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል። ቤተሰቦቹ ትምህርቱን እንዲከታተል ቢፈልጉም የእርሱ ልብ ግን በእግር ኳስ ፍቅር ተማርኮ ነበር። በመጨረሻም ህልሙን ለመከተል ሲል ከቤት ጠፍቶ ወደ ዳካር ኮበለለ። ያኔ ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ነበር። በተቀደደ ጫማ እና ልብስ የእግር ኳስ ሙከራ ለማድረግ ወደ ሜዳ ሲገባ በትዝብት ዓይን ያዩት አሰልጣኙ ይሳካለታል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው ከዓመታት በኋላ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ ከምርጥ አፍሪካዊ ኮከቦች ተርታ መሰለፍ ችሏል።
የማኔ የእግር ኳስ ህይወት ከፈረንሳዩ ክለብ ሜትዝ ይጀምራል። በኦስትሪያው ሳልዝበርግ እና በሳውዝሃምፕተን ክለቦች ጎልብቶ በአንፊልድ ሮድ አንጸባርቋል። እ.አ.አ በ2015 ክለቡ ሳውዝሃምፕተን ከአስቶን ቪላ በነበረው ጨዋታ በሁለት ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ ውስጥ ሦስት ግቦችን (Hat-trick) በማስቆጠር በፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ክብረወሰን አስመዘግቧል። በዚህ ወቅት ነበር ማኔ በመረሲሳይዱ ክለብ የዝውውር ራዳር ውስጥ የገባው። እናም በ2016 እ.አ.አ ሴንት ሜሪን ለቆ አንፊልድ ሮድ ደርሷል። በአንፊልድም ከሞሀመድ ሳላህ እና ሮቤርቶ ፈርሚኖ ጋር ደንቅ ጥምረት በመፍጠር አስደናቂ ስድስት የውድድር ዘመን አሳልፏል። ሳዲዮ ማኔ በ2022 እ.አ.አ በጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርን ሙኒክ አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ወደ ሳውዲ አረቢያው አል ናስር በማቅናት አሁን በሳውዲ ፕሮ ሊግ እየተጫወተ ይገኛል።
እ.አ.አ በ2019 ሊቨርፑል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫ ሲያነሳ የሳዲዮ ማኔ አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር የስካይ ስፖርት መረጃ አስነብቧል። እንዲሁም በ2020 እ.አ.አ ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ሲያሳካ ማኔ የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ እንደነበር አይዘነጋም። ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ጠንካራ ከሚባሉ ሀገራት አንዷ የነበረች ቢሆንም እስከ እ.አ.አ 20121 ድረስ አንድም ዋንጫ አለማንሳቷን የታሪክ ማህደሯ ያስነብባል።
እ.አ.አ 2021 በሴኔጋላውያን ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረው ህልም የተሳካበት ወቅት ነው። በዚህ ዓመት ማኔ ሀገሩን ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቃበት እንደነበር የሚታወስ ነው። በወቅቱ በታላቁ የእግር ኳስ የግል ሽልማት ባሎን ዶር (Ballon d’Or) ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም፤ ይህም ከጆርጅ ዌሀ በኋላ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ አፍሪካዊ ተጫዋች እንዲሆን አስችሎታል።
ሳዲዮ ማኔ ከሌሎች ኮከቦች የሚለየው ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቱ እና ሰብዕናው መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ማኔ በዓለም ላይ ከፍተኛ ክፍያ ከሚከፈላቸው ተጫዋቾች አንዱ ቢሆንም እጅግ ቀላል እና የተረጋጋ ህይወት እንደሚመራ ይነገራል። ማኔ በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የተመሰከረለት በጎ አድራጊ ነው። ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለ አባቱ በድንገት ይታመማሉ። በወቅቱ በባምባሊ መንደር ውስጥ ሆስፒታል ስላልነበረ አባቱን ማትረፍ እንዳልቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ ክስተት በህጻኑ ማኔ ልብ ውስጥ የማይሽር ቁስል ጥሎ ያለፈ ሲሆን አሁን እየሰራ ላለው ታላቅ የበጎ አድራጎት ሥራ መሰረት ሆኖታል። “አባቴ የሞተው በህክምና እጦት ነው፤ እኔ ስቀየር ግን መንደሬ ትቀየራለች” የሚል ጽኑ እምነት በውስጡ ይዞ ማደጉን ይናገራል።
በአንድ ወቅት ስክሪኑ የተሰነጣጠቀ ስልክ ይዞ በካሜራ ዕይታ ውስጥ መግባቱ በማህበራዊ የትስስር ገጾች በሰፊው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በሚሊዮን ዶላር የሚከፈለው ታላቅ የእግር ኳስ ተጫዋች እንዴት በዚህ ስልክ ይጠቀማል? ተብሎ ሲጠየቅ የሰጠው ምላሽ የእርሱን ማንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
“ለምን ዐስር ፈራሪ መኪናዎች፣ ሃያ የዳይመንድ ሰዓቶች ወይም ሁለት የግል አውሮፕላኖች ያስፈልጉኛል? እነዚህ ቁሶች ለእኔም ሆነ ለዓለም ምን ያደርጋሉ?” በማለት የጠየቁትን ጋዜጠኞች መልሶ ጠይቋል። “የሚበላ አጥቼ ተርቤ አውቃለሁ፤ በባዶ እግሬ ኳስ ተጫውቻለሁ፤ በድህነት ምክንያት ትምህርት ቤትም መሄድ አልቻልኩም። ዛሬ በማገኘው ገንዘብ ግን ሕዝቤን እየረዳሁ ነው። ትምህርት ቤቶችን እገነባለሁ፤ ስታዲየምም እሰራለሁ። ልብስ፣ ጫማ እና ምግብ ለተቸገሩት አግዛለሁ። ለምቾት ብዬ ውድ ዕቃዎችን ከመግዛት ይልቅ ወገኖቼ የእኔን የተወሰነውን እድል ቢያገኙ እመርጣለሁ” ሲል በትህትና ተናግሯል።
በትውልድ መንደሩ አባቱ በህክምና እጦት በሞቱባት ባምባሊ ከተማ ዘመናዊ ሆስፒታል አስገንብቷል። ሆስፒታሉ ለባምባሊ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ለሚገኙ ከ30 በላይ መንደሮች ብቸኛው የህክምና ተቋም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በዚህም ነፍሰ ጡር እናቶች ለመውለድ ብዙ ኪሎሜትሮችን በስቃይ ይጓዙ የነበረውን ድካም አስቀርቷል። ከሆስፒታሉ በተጨማሪ ዘመናዊ ትምህርት ቤት አስገንብቷል። ማኔ ባምባሊን ከተኛችበት በማንቃት ወደ ዘመናዊ ከተማነት እየቀየራት ይገኛል። የመንደሩ ወጣቶች ከዓለም ጋር እንዲገናኙ የአራተኛ ትውልድ (የ4G) ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጠቀሙ አድርጓል። በትውልድ መንደሩ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ እንዲሁም የፖስታ ቤት አገልግሎት ሥራ አስጀምሯል።
በድህነት ለሚኖሩ የመንደሩ ቤተሰቦች በየወሩ የገንዘብ ድጋፍም ያደርጋል። ለእርሱ ሀብት እና ስኬት ማለት በባንክ ሂሳብ ውስጥ ያለ የገንዘብ ቁጥር ሳይሆን በሰዎች ፊት ላይ የሚታይ ፈገግታ እንደሆነ ቢቢሲ ስፖርት ያስረዳል። በትውልድ መንደሩ እና በሰፊው የሴኔጋል ሕዝብ ዘንድ ሳዲዮ ማለት ከእግር ኳስ ተጫዋችነት በላይ የገዘፈ ትርጉም አለው። እርሱ የህይወት አድን፣ የተስፋ ብርሃን እና የለውጥ መሐንዲስ ነው።
ባምባሊ ዛሬ በሴኔጋል ካርታ ላይ ደምቃ የምትታየው በልማቷ ነው፤ የዚህ ልማት መሀንዲስ ደግሞ እግሩ ኳስን በጥበብ የሚጫወተው፣ እጁ ደግሞ ልግስናን የተለማመደው ሳዲዮ ማኔ ነው። ማኔ ዝና አፍንጫውን ያላሳበጠው፣ ገንዘብ ልቡን ያላደነደነው ሰው መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


