በአሁኑ ጊዜ በሴቶች ላይ ሞትን ጨምሮ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት በሚያስደነግጥ ሁኔታ የተለመደ ሆኗል:: የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት(unwomen) በዮርዳኖስ፣ በሊባኖስ፣ በኔፓል፣ በፍልስጤም ግዛት እና በቱኒዚያ በሚገኙ የአካባቢ ምክር ቤቶች ውስጥ የቢሮ ሥራ ያላቸው ሴቶች ላይ የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል:: የጥናቱ ምላሽ ሰጪዎች የስነ-ልቦና ጥቃት በጣም የተስፋፋው በትንኮሳ መሆኑን ጠቁመዋል:: ከዚያም ወሲባዊ ጥቃት እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃት – ለምሳሌ እንደ ደመወዝ፣ የቢሮ ቦታ እና መሳሪያ ያሉ ሀብቶችን ማግኘት እንደሚከለከሉ ተናግረዋል:: ሴት የቢሮ ኃላፊዎች በሚሰሩባቸው የአካባቢ መስተዳድር ተቋማት ውስጥ ብዙ ጊዜ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸው ነው የተናገሩት:: ተጨማሪ ጥቃቶችም በማሕበረሰባቸው እና በቤት ውስጥ እንደሚያጋጥማቸው ነው ያስታወቁት::
በበርካታ ሀገራት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን እንደ መሪ እና እጩ ተወዳዳሪ አድርጎ ማካተትን የሚቃወሙ ናቸው:: እንዲሁም ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ለመወዳደር አስቸጋሪ የሚያደርጉ የምርጫ ሥርዓቶች ተጠቃሽ ናቸው:: ሴቶች የፋይናንስ እና የፖለቲካ ድጋፍን ያጣሉ:: በመሆኑም ለፓርቲ እጩ ለመሆን የሚያስችላቸውን የምርጫ ውድድር ግብአቶችን ለማግኘት ከወንዶች ያነሰ ተደራሽነት አላቸው:: በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች መጠነኛ የእጩ ምዝገባ ክፍያዎች እንኳን ሴቶች በምርጫ ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉ ሊከለክል ይችላል:: ከዚህም በላይ የፖለቲካ ፍላጎት ማጣት እነዚህን ጉዳዮች ያባብሰዋል:: እ.አ.አ. በ 2024 ሴቶች በብሔራዊ ፓርላማዎች ውስጥ 27 በመቶ መቀመጫዎችን እና በአካባቢ መስተዳድሮች ውስጥ 35 ነጥብ አምስት በመቶ መቀመጫዎችን ብቻ ነበር የያዙት::
ዩኤን ውሜን ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ሴቶች የተለያዩ ልምዶቻቸውን የሚያንፀባርቁ ፖሊሲዎችን በማስተዋወቅ፣ በማውጣት እና በወንዶች ችላ የሚባሉ ጉዳዮችን በመፍታት ረገድ በፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ:: በአመራር ቦታዎች መገኘታቸው በማሕበራዊ ጉዳዮች፣ በእኩልነት እና በማሕበረሰብ ደኅንነት ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችን እንዲቀረጹ ያደርጋሉ:: የሴት መሪዎች ለጤና አጠባበቅ፣ ለትምህርት እና ለቤተሰብ ደኅንነት ቅድሚያ ይሰጣሉ:: ይህም ጤናማ እና የበለፀገ ማሕበረሰቦችን ለመገንባት ይረዳል:: በተጨማሪም ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂ ልማት ልምዶችን ያበረታታሉ:: በፖለቲካ ውስጥ የሴቶች ውክልና እየጨመረ መምጣቱ ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የበለጠ ሁሉን አቀፍ እና ውጤታማ የአስተዳደር ስርዓትን ለማጎልበት ጠቃሚ እርምጃ ነው::
የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በጥሩ ሁኔታ ለሚሰራ ዴሞክራሲ ወሳኝ ነው:: ሴቶችን ማካተት የፍትሕ ጉዳይ እና የበለጠ ውጤታማ አስተዳደር ለመፍጠር ወሳኝ ነገር ነው:: በፖሊሲ አውጪዎች ውስጥ ብዙ ሴቶች መኖራቸው እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ የሕጻናት እንክብካቤ፣ መሠረተ ልማት እና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም እና ልጃገረዶች ከፍተኛ ትምህርት እና የሥራ እድሎችን እንዲያገኙ ያስችላል:: ሆኖም በሁሉም የዓለም ክልሎች የሴቶች ድምጽ ከውሳኔ አሰጣጥ የተገደበ ነው:: በአሁኑ ጊዜ በሴት የሚመሩት 27 ሀገራት ብቻ ሲሆኑ ይህም ከአስር ዓመታት በፊት ከነበረው 18 ሀገራት በትንሹ ከፍ ያለ ቢሆንም አሁንም 107 ሀገራት በታሪካቸው ሴት መሪ ኖሯቸው አያውቁም::
ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ 23 በመቶውን ብቻ የሚይዙ ሲሆን 15 ሀገሮች ብቻ እኩል ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ወንዶች ካቢኔዎች አሏቸው:: በ 141 ሀገሮች ውስጥ ሴቶች በካቢኔ ሚኒስትርነት ከአንድ ሦስተኛ በታች ናቸው:: ሰባት ሀገራት በካቢኔዎቻቸው ውስጥ ምንም አይነት ሴት የላቸውም:: አሁን ባለው ፍጥነት በካቢኔዎች ውስጥ ያለው የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ከ2077 በፊት አይደርስም:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች ከፓርላማ አባላት 27 በመቶውን ይይዛሉ::
በፖለቲካው ተሳትፎ ጥሩ የጾታ እኩልነት ካላቸው ሀገራት መካከል ሜክሲኮ እና ሩዋንዳ ይጠቀሳሉ:: እ.አ.አ. ጥር 2024 ጀምሮ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት ውስጥ ከ40 እስከ 49 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ሀገራት ሰባት ብቻ ናቸው:: እነሱም ኦስትሪያ፣ ቤላሩስ፣ ቤልጂየም፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሰሜን መቄዶንያ እና ደቡብ አፍሪካ ሲሆኑ – ስድስት ሀገራት ደግሞ ከአምስት እስከ ስምንት በመቶ ብቻ ተሳትፎ አላቸው:: ሀገራቱም ኢራን፣ ኪሪባቲ፣ ማልዲቭስ፣ ፓላው፣ ሰለሞን ደሴቶች እና ቱቫሉ ናቸው::
ሴቶችን ወደ ፖለቲካ ለማምጣት በሕግ የተደነገጉ የሥርዓተ-ፆታ ኮታዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው:: በዓለም ዙሪያ የሥርዓተ-ፆታ ኮታ ሕጎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠዋል:: የግዴታ የፓርላማ ኮታ ባለባቸው ሀገሮች ሴቶች በአማካይ 26 በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን ሲይዙ ኮታ በሌላቸው ሀገራት 21 በመቶው ነው:: በተመሳሳይም ለአካባቢ ምርጫ ሕጋዊ ኮታ ያላቸው ሀገራት ኮታ ከሌላቸው ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ የሴቶች ውክልና በአማካይ ሰባት በመቶ ጨምሯል::ነገር ግን የኮታዎች አቅም ብዙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እውን አይሆንም::
በኢትዮጵያ በመንግሥት እና በፓርላማ ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ ከበፊቱ አሁን ላይ በእጅጉ ተሻሽሏል:: (ለምሳሌ የካቢኔ ሚኒስትሮች መጠን) ነገር ግን በክልል እና በአካባቢ ደረጃ ገና ክፍተቶች ቢኖሩም ማለት ነው::
ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዳይሳተፉ ካደረጋቸው ምክንያቶች መካከል ማሕበራዊ አመለካከት አንዱ ሲሆን “ፖለቲካ የወንዶች ነው” የሚል አስተሳሰብ በአብዛኛው ማሕበረሰብ የሚንጸባረቅ ነው:: ሌላው የኢኮኖሚ እጥረት ነው:: ስለ ሴቶች ያልተገባ ንግግር (አትችልም፣ ሴት ወደማጀት…የሚሉ ንግግሮች፣የጊዜ ጫና፣ የቤት እና የማሕበራዊ ግዴታዎች ሴቶችን ወደ ፖለቲካው እንዳይመጡ አድርጓቸዋል::
በዓለም ላይ የበለጠ በፖለቲካው መስክ የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ የሚታይባቸውን ሀገራት ለአብነት ብናይ በመጀመሪያ ደረጃ ቀድማ የምትጠቀሰው አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ ናት::
በሁለተኛነት የምትጠራው ደግሞ የስካንድቪዋ ኖርዌይ ናት:: የፆታ እኩልነት ፖሊሲዎቿ በጣም ጠንካራ ሲሆኑ በፓርላማ እና በካቢኔ ውስጥ ከፍተኛ የሴቶች ተሳትፎ አለ:: ስዊድን ብዙ ዘመናት በካቢኔዋ የጾታ ስብጥሯ 50/50 ሲሆን ሴቶች በውሳኔ መስጠት ከወንዶች እኩል ናቸው:: በፊንላንድ በፖለቲካ ጉዳይ የሴቶች መሪነት መደበኛ ነገር ነው:: ሴት ፕሬዚዳንት እና ሴት ጠቅላይ ሚኒስትሮች አሏት:: ኒው ዚላንድ በፖለቲካዋ አካታችነትን ስለምትጠቀም ሴት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ነበሯት:: አይስላንድ በፆታ እኩልነት መመዘኛዎች ላይ ሁልጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ሴቶች በፕሬዚዳንት ቦታ ተቀምጠው ሀገሪቱን የመሩበት ሁኔታም በርካታ ነው:: በስፔን ካቢኔ ውስጥ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሴቶች ብዛት ከወንዶች በላይ ሆኗል:: እንደ ናሚቢያ፣ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ ሀገራትም ጠንካራ የፆታ ኮታ ሕጎች እና የሴቶች ንቅናቄ ያሏቸው ሀገራት ናቸው:: በነዚህ ሀገራት ጠንካራ የሕግ ተቋማት አሉ:: የማሕበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ በትምህርት እና በኢኮኖሚ እድል ተጠቃሚ አድርጓቸዋል::
ሴቶችን በፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ማድረግ በመጀመሪያ የዴሞክራሲን ሙሉነት ያረጋግጣል:: ሴቶችን በሰላም እና በግጭት መፍትሄ ሂደቶች ማሳተፉ ዘላቂ ሰላም ይጨምራል:: የአካባቢ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው:: በኢኮኖሚ ዘርፍም ተፅእኖው ግልፅ ነው:: ሴቶች በፖለቲካ ሲካተቱ የልማት ፖሊሲዎች በሰፊ እይታ ይዘጋጃሉ:: የድህነት ቅነሳ ይበረታል፣ የቤተሰብ እና የሀገር ኢኮኖሚ ይጠናከራል::
ሴቶችን በፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ማድረግ ለሴቶች ብቻ የሚጠቅም ጉዳይ አይደለም፤ ለዴሞክራሲ፣ ለሰላም እና ለዘላቂ ልማት የማይተካ መሠረት ነው:: የሀገር እድገት ሴቶችን ከፖለቲካ ውጭ በመተው ሊገኝ እንደማይችል ልብ ሊባል ይገባል::
ማናት
ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ (ዶ/ር) እ.አ.አ. ሰኔ 13/ 1954 በዴልታ ግዛት ናይጀሪያ ተወለዱ::
የዓለም ንግድ ድርጅትን (WTO) በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት እና አፍሪካዊ ናቸው:: በምጣኔ ሀብት ከሠላሳ ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ባለሙያ ናቸው::
የናይጄሪያ የገንዘብ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት እና የፋይናንስ ግልጽነትን በማሻሻል ጠቃሚ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አድርገዋል:: በዚህም የናይጄሪያን 18 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ እንዲሰረዝ አድርገዋል:: የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆናቸው በመላው አፍሪካ፣ ደቡብ እስያ እና አውሮፓ ሥራዎችን አስተዳድረዋል:: ኦኮንጆ-ኢዌላ ለአፍሪካ ሕብረት እና ለዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ልዩ መልዕክተኛ በመሆን እና ለአየር ንብረት ለውጥም ሥራዎችን በመስራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል:: እ.አ.አ. በ 2020 የፎርብስ መጽሔት የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተብለው ከተዘረዘሩ 100 የዓለም ኃያላን ሴቶች መካከልም ተካተዋል::
ምንጭ፡- answersafrica.com
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


