አይበገሬዉ

0
48

በቻይና ዢይጂያንግ ግዛት፣ ዚንቻንግ ከተማ በገበያ ማእከል ህንፃ አቅራቢያ በሚገኝ የጐዳና ዳር የመብራት ምሰሶ ስር የበቀለ ቀርከሃ፣ ከመሬት ከፍ ብሎ ባገኘው ክፍተት ገብቶ  ውስጥ ለውስጥ አድጐ ቅርንጫፉን በ “አምፓል” ማሰሪያው፣ ቀዳዳ አውጥቶ መለምለሙን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በቀጣናው ኗሪዎች “አይበገሬው ቀርከሃ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ተክል ከመብራት ምሰሶው ጥግ በቅሎ ከምሰሶው ግርጌ ባገኘው ክፍተት ገብቶ ስድስት ሜትር ርዝመት ማደግ ችሏል፡፡ ቀርከሃው በምሰሶው አናት “አምፖል” ማሰሪያው ላይ ባገኘው ክፍተት ቅርንጫፎቹን አውጥቶ መለምለሙን ድረ ገጹ አመላክቷል፡፡

ቀርቀሃውን የተመለከቱ ሙሉ በሙሉ በተዘጋ የመብራት ምሰሶ ያለ ፀሀይ ብርሃን እንዴት ሊያድግ ቻለ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ባለሙያዎች በበኩላቸው ቀርቀሃ በጨለማ ወይም ብርሃን በሌለበት የዳበረ የስር ስርዓቱን መሬት ውስጥ በማስረግ ንጥረ ነገሮችን በመምጠጥ የመጀመሪያ ደረጃ እድገቱን ማስቀጠል እንደሚችል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ያልተለመደውን የቀርቀሃ አበቃቀል እና እድገቱን ተመልክተው በቪዲዮ ቀርፀው በማህበራዊ ድረ ገጽ ያጋሩት ጂያ የተባሉ የአካባቢው ኗሪ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ግለሰቡ ልጆቻቸውን ይዘው በአካባቢው ሲያልፉ በተመለከቱት በመገረማቸው በቪዲዮ ቀርፀው ማጋራታቸውን ተናግረዋል፡፡ የተጋራው ቪዲዮም በአንድ ቀን በሚሊዮኖች መታየቱን አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው በአካል በቦታው በመገኘት  ቀርቀሃው ችግርን ስለ መቋቋም፣ ስለ ጥረት እና ፅናት ማስተማሪያ ማድረጋቸው ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here