የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ እንደጻፉት ዘመነ መንግሥታቸው በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው:: አፍ ሞልቶ በክፉም በበጎም ማውሳቱ ያዳግታልና:: ‹‹አቤቶ›› እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ልጅ እያሱ፣ በአጭር የሥልጣን ዘመናቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለኝታን በማጠናከራቸው፣ ተራማጅ ሊባሉ የሚችሉ አንዳንድ እርምጃዎችን ወስደዋል::
የግል ንብረትን የማስከበርና ዐሥራትን በወቅቱ ከመሰብሰብ ደንብ በተጨማሪ፤ ከሳሽና ተከሳሽ አብረው እንዲማቅቁ ያደርግ የነበረውን የቁራኛ ሥርዓት ለመሻር እርምጃ ወስደዋል:: እንዲሁም ከፍትሕ ይልቅ ለቂም መወጫና ደካማ ማጥቂያነት የሚያገለግለውን የሌባ ሻይ ሥርዓት (አስክሮ ማወጣጣት) መልክ ለማስያዝ ሞክረዋል:: የመንግሥት ገንዘብን ባባከኑት ላይ እርምጃ በመውሰድም ልጅ እያሱ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሳይሆን አይቀርም::
ልጅ እያሱ ሚካኤል፣ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ፤ ንጉሠ ነገሥት ባይባሉም ከ1903 እስከ 1909 ዓ.ም የኢትዮጵያን ሥልጣን ጨብጠው ያስተዳደሩ መሪ ነበሩ::
በ1884 ዓ.ም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ የሆነችው ሸዋረጋ ከወሎው ገዢ ራስ ሚካኤል ጋር በተደረገ ትስስር የሰመረው ጋብቻ፤ ልጅ እያሱን አስገኘ:: እያሱ ያደጉት አያታቸው ከመጡበት የአንኮበር ከተማ ነበር:: ልዑሉ በዚህ ቦታ ተገልለው ቢቀመጡም የትምህርታቸው ክትትል መረጃ ግን በፎቶ ግራፍ አንሺዎች ይመዘገብ እንደነበር ፎቶ ግራፎች ያሳያሉ:: ከዚህ በተጨማሪም ልዑሉን በአእምሮና በአካል የጠነከሩ አድርጐ ለማብቃት መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ፣ ዳዊት ሲደግሙ፣ ፈረስ ሲጋልቡ፣ እንዲሁም የእጅ ጽሕፈት ሲማሩ መቆየታቸውን የሚያሳዩት ፎቶግራፎች ያነሷቸው ከዳግማዊ ምኒልክ በተላኩ የፎቶ ግራፍ አንሺዎች አማካይነት ነው::
ከሕፃንነት ዘመናቸው ጀምሮ ፎቶግራፍ የተነሡት ልጅ እያሱ፣ በፎቶግራፍ ጥበብ ተገልጸዋል:: ዘውድ ባይጭኑም የሥልጣን ተምሣሌቶችን ለራሳቸው መጠቀማቸው የቀረቡት ፎቶ ግራፎች ያመለክታሉ:: ይኸውም እንደ ጦረኛ፣ እንደ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ እንደ ዲፕሎማት ሆነው፤ ከመስቀል፣ ከአንበሳ፣ ከጦር መሣሪያ ጋር፣ ሜዳሊያ በማጥለቅም ተነሥተዋል:: ለብቻ ወይም በቡድን በመሆን በሚነሷቸው ፎቶግራፎቻቸው አማካይነትም ፖለቲካዊና ቤተሰባዊ ትስስርንና ጥምረትን ያሳዩ ነበር::
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ እያሱ ዘመነ መንግሥት” በተሰኘው መጽሐፍ ስለ ልጅ እያሱ እና አባታቸው ንጉሥ ሚካኤል ንግሥና የሚከተለውን ብለዋል “ከዐፄ ምኒልክ ሞት በኋላ በ1906 ዓ.ም. ሚኒስትሮችና መኳንንት በቆይታ ተመካክረው ለአቤቶ እያሱ የምክር ቃል አቀረቡ ሲባል ተሰማ:: የምክሩም ቃል ጃንሆይ አፄ ምኒልክ በሕይወታቸው ሳሉ አልጋ ወራሼ እያሱ ነው ብለው አስታወቁን፤ አሁን እሳቸው ዐረፉ፤ እንግዲህ ምን እስቲሆን እንጠብቃለን፤ የዘውድ በዓልዎ የሚደረግበትን ቀን እንወስንና ዘውድ ደፍተው በአባትዎ መንበረ ዳዊት ይቀመጡልን” የሚል ነው::
አቤቶ እያሱም “ምክራችሁ መልካም ነው፣ እኔም ሳላስብበት አልቀረሁም፤ ነገር ግን አባቴን ራስ ሚካኤልን በፊት ንጉሥ አሰኝቼ በኋላ ንጉሠ ነገሥት መሆን ይገባኛል” ብለው መለሱላቸው:: ሐሳባቸውን የፈጸሙት በዚያው ዓመት ከአዲስ አበባ ከዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ዘውድ፣ ሉል እና ልብሰ መንግሥት ወደ ደሴ በመላክ ራስ ሚካኤልን “ንጉሠ ወሎ ወ ትግሬ” አሰኝተው ግንቦት 23 ቀን 1906 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ደሴ ላይ አንግሠዋቸዋል::
የንጉሥ ሚካኤል መንገሥ የሸዋ መኳንንቶችን አላስደሰተም:: በሂደትም የልጅ እያሱን ስም ማጥፋት እና መዶለት ጀመሩ:: ከዱለታው አንዱ ልጅ እያሱ ሰለሙ ብሎ ማስወራት ነበር:: ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ክሱ በዚህ ስልት የተቀናበረው እያሱን በሕዝቡና በጦር ሀይሉ ዘንድ ለማስጠላት አመቺ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነው ይላሉ። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ልጅ እያሱ ቀጨኔ መድኃኒዓለምን የመሳሰሉ ደብሮችን እንዳልተከለ ሁሉ ከፍ ብሎ የሚወራው መስጊዶችን ማሰራቱ ነው። ለክሱ ማስረጃ አምጡ በሚባልበት ጊዜ “ድሮውንስ ከሙሐመድ ዓሊ ልጅ ምን ይጠበቅ ኖሯል?!” የሚል ቃለ አጋኖ ይነገር ነበር። “ይሁንና” ይላሉ ፕሮፌሰር ባህሩ “ለሸዋ መኳንንት የእያሱ አደገኛነት የፖለቲካ የበላይነታቸውን ከመፈታተኑ ላይ ነበር። ስለዚህ የመናፍቅነቱ ክስ የመነጨው ለሃይማኖት ከመጨነቅ ሳይሆን ለተፈጠረው የፖለቲካ ስጋት ርዕዮተ ዓለማዊ ሽፋን ሆኖ ለማገልገል ካለው አመቺነት ነው”::
በልጅ እያሱ ላይ የሚደረገው ዱለታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ልጅ እያሱ አባታቸውን “ንጉሥ ሚካኤል” በማለት በወሎና በትግሬ ላይ ባነገሡበት ጊዜ ነው። የሸዋ መኳንንት ራስ ሚካኤል ሰሜን ኢትዮጵያን በቀጥታ ሌላኛውን የኢትዮጵያ ክልል በልጁ በኩል መቆጣጠሩን አሰመሩበት። በመሆኑም የሸዋ መኳንንት “ይህ ወጣት ከቤተ መንግሥቱ ጠራርጎ ሳያስወጣን እንቅደመው” በማለት መሯሯጥ ጀመሩ። የዚህ አድማ ዋነኛ መሪና አቀናባሪ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ነበሩ።
ልጅ እያሱ የዕድሜ ልክ ባላንጣቸው ሊሆን የበቃውን ደጃች ተፈሪ መኮንንን በጋብቻ ጠልፎ ዝም ሊያሰኙት ሞክረው ነበር። ይሁንና ተፈሪ የእያሱ እህት ልጅ የሆነችውን ወ/ሮ መነን አስፋውን ቢያገባም ሁለቱ ወጣቶች ፍጹም ሊጣጣሙ አልቻሉም። ተፈሪ የዘመኑ ሀብታም ክፍለ ሀገር የነበረው ሀረርጌ የዕድሜ ልክ ግዛቴ ነው ብሎ ያስብ ነበር። እያሱ ደግሞ ተፈሪ በሀረር ሀብት መበልጸጉን አልወደደውም። በተለይም ደጃች ተፈሪ ከባቡር መስመር መዘርጋት ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱ መንግሥት ግምጃ ቤት አለኝታ ሊሆን የበቃውን የድሬዳዋ ጉምሩክ ገቢ በቀጥታ ሊቆጣጠረው መቻሉ ለልጅ እያሱ አልተዋጠለትም። ነገር ግን ከዚህ ክስተት በላይ እያሱን በተፈሪ ላይ ያነሳሳው የልጅ እያሱን ስም የሚያጠፋ ሚስጢራዊ ደብዳቤ ለእንግሊዝ መንግሥት ተጽፎ መገኘቱ ነው። ይህንን ደብዳቤ የጻፉት የደጃች ተፈሪ መኮንን ጸሐፊና አንድ ማንነቱ በውል ያልተገለጸ ሌላ ሰው ናቸው። ደብዳቤው በማን ትዕዛዝ እንደተጻፈ ግን የታሪክ ሰነዶች በይፋ የሚገልጹት ነገር የለም። ልጅ እያሱ “ትዕዛዙን ያስተላለፈው ተፈሪ መኮንን ነው” ባይ ነው። በዚህም ወደ አዲስ አበባ አስጠርተው ስለጉዳዩ ቢጠቁት ደጃች ተፈሪ ከነገሩ ንጹህ መሆኑን በመሀላ ገለጹለት። ቢሆንም እያሱ አላመኑም። በመሆኑም በሁለቱ መካከል የነበረው ቅራኔ በጣም ተባባሰ።
ነገሮች በዚህ ላይ እንዳሉ ልጅ እያሱ ተፈሪ መኮንን ወደ አዲስ አበባ አስጠርተው እርሱን ሳያነጋግሩ ወደ ሀረር ወረዱ። ከሀገሬው ሕዝብ ጋር ከተማከሩ በኋላም ደጃች ተፈሪ መኮንን ከሀረር ገዥነቱ ሻሩት። በምትኩም የከፋ ገዥ አድርገው ሾመው በአስቸኳይ ወደ ተሾመበት ክልል እንዲሄድ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጡት። የድሬ ዳዋ ጉምሩክንም ወዳጃቸው በነበረው ሶሪያዊው ሀሲብ ይዲልቢ ስር እንዲሆን አደረጉት።
የልጅ እያሱ እርምጃ ተፈሪን በጣም አስደነገጠው። “ይህ መስፍን ሊውጠኝ እያመቻቸኝ ነው” በማለት እንዲያስብም አደረገው። ስለዚህ ደጃች ተፈሪ ወደ ከፋ መሄዱን ተወና አዲስ አበባ ሆኖ የሚበጀውን መንገድ ማፈላለግ ጀመረ። ልጅ እያሱ በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ ቢያዥጎደጉድለትም ደጃች ተፈሪ ልዩ ልዩ ሰበቦችን እያመካኘ በዋና ከተማይቱ ሰነበተ። የእያሱንም ልብ ለማቀዝቀዝ የስጋ ዘመዱ የሆነውን ቀኛዝማች እምሩ ኃይለ ሥላሴን (የኋለኛው ራስ እምሩ) የቃልና የጽሑፍ መልዕክት አስጨብጦ ልጅ እያሱ ወደሚገኝበት ድሬዳዋ ላከው። እያሱም የተፈሪን መልዕክት ከሰማ በኋላ እንዲህ አለ። “ደጃች ተፈሪ አሳቡ ሁሉ ሌላ ነው። ያንዳንድ ወስላቶች ነገር እየሰማ ወዲያ ወዲህ ቢል ብርቱ ነገር ያገኘዋል። የአዲስ አበባ ወስላታ ሁሉ ፍሬ ያለው መስሎታል።” (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ”፣ በኢትኦጵ መጽሔት የቀረበ ጽሑፍ፣ ጥቅምት 1993)
ይህ የልጅ እያሱ አነጋገር በሁለቱ ልዑላን መካከል የነበረው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል። የእያሱ ንግግር ለደጃች ተፈሪ ጆሮ ከደረሰው በኋላ ተፈሪ በስውር ማድባቱን ትቶ እያሱን ከስልጣን ለመፈንገል የሚዶልቱትን መኳንንት በይፋ ተቀላቀለ። በአስገራሚ ፍጥነትም የዱለታውን መሪነት ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እጅ ወሰደው። የሁለቱ ወጣቶች መገፋፋት ይፋ ሆኗል። ቀጣዩ ነገር “ማን ቀድሞ አጥቅቶ የአሸናፊነቱን ዘውድ ይቀዳጃል” የሚለው ብቻ ነበር። የሸዋና የምዕራብ ኢትዮጵያ ባላባቶች በተፈሪ ዙሪያ ተሰልፈዋል። የወሎ፣ የአፋር፣ የኦጋዴንና የሀረርጌ ባላባቶች የእያሱን ጎራ ተቀላቅለዋል። ቢሆንም ሁለቱ ጎራዎች በራሳቸው ወኔ ፍልሚያውን መጀመር አልቻሉም። የመጨረሻውን ፍልሚያ ለማስጀመር ሌላ ስውር እጅ አስፈልጓል። የዘመኑ ታላላቅ ቅኝ ገዥዎች እጅ!
የልጅ እያሱ ከስልጣን መውረድ ዜና የተሰማው እያሱ ጅጅጋ እያለ ነው። የዜናውን መሰማት ተከትሎ የእያሱ ደጋፊዎች በሚበዙባቸው ሀረርና ድሬዳዋ ታላቅ ረብሻ ተነሳ። የደጃች ተፈሪ መኮንን ደጋፊዎች የተባሉት እየተሳደዱ ተፈጁ። እያሱ በከተሞቹ ደርሶ ሁኔታውን ካረጋጋ በኋላ በአሻጥር የተወሰደበትን ዙፋን ለማስመለስ ከከተሞቹ ነዋሪዎች ጋር ተማከረ። በዚህም የህዝቡን ድጋፍ ካገኝ በኋላ በሸዋ ላይ ለመዝመት መዘጋጀት ጀመረ። ይሁንና ዝግጅቱን ሳያጠናቅቅ እነ ራስ ተፈሪ የላኩት 15,000 ጦር ወደ ሀረርጌ እየመጣ መሆኑ ታወቀ። ልጅ እያሱም የሸዋውን ጦር ለመግጠም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ገሠገሠ። ሁለቱ ሀይሎች መኤሶ አጠገብ ተገናኙ። ትልቅ ውጊያም አደረጉ። በጦርነቱ የሸዋው ሀይል ድል ስለቀናው ልጅ እያሱ ወደ አፋር በረሃ ሸሸ። የልጅ እያሱ አባት (ራስ ሚካኤል) የልጁን ስልጣን ለማስመለስ 100,00 ጦር አስከትቶ ወደ ሸዋ ዘመተ። ነገር ግን እርሱም እንደ ልጁ ሰገሌ ላይ ተሸነፈ።
የልጅ እያሱ ውድቀት ከሦስት ዓመታት አስቸጋሪ ቆይታ በኋላ እውን ሆነ። ለሦስት ዓመታት የነገሠበትን አልጋ ከውጪና ከውስጥ በተሸረበበት ሴራ አጣ። መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጡ ደጃች ተፈሪ መኮንን “ራስ” ተብው የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ሆኑ። ይህ ሁሉ ሲከናወን ኢላማ የሌለው ተኩስ አልፎ አልፎ ከመሰማቱ በስተቀር አዲስ አበባ ሰላም ነበረች።
ልጅ እያሱ የሰገሌውን መርዶ ከሰማ በኋላ በሽሽት ነው የኖረው ለማለት ይቻላል። በመቅደላና በደሴ አነስተኛ ውጊያዎችን ቢያደርግም በለስ ሊቀናው አልቻለም። ከዚያም ወደ አውሳ በረሃ ሄዶ ከወዳጁ ከሱልጣን አቡበከር ጋር ለጥቂት ዓመታት ኖረ። ነገር ግን ጠላቶቹ እዚያም እንዲቆይ አልፈቀዱለትም። ከሀረርጌና ከወሎ ትልቅ ጦር ቢያዘምቱበት ወደ ትግራይ ሸሸ። በትግራይ ውስጥ ለጥቂት ወራት ከቆየ በኋላ በ1915 ዓ.ም ተያዘና ፍቼ ታሰረ። እዚያ እያለ የጎጃሙ ራስ ሀይሉ ተክለሀይማኖት እስር ቤቱን ሰብሮ ሊያስወስደው መሆኑ ስለተወራ ሌላ ቦታ እንዲዛወር ተወሰነ። በመሆኑም ወደ ሀረርጌ ተወስዶ ጋራ ሙለታ አምባ ላይ በተሰራለት እስር ቤት እንዲታሰር ተደረገ። በዚህ አምባ ላይም ለአስር ዓመታት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ ጥቅምት 1928 መሞቱ ይፋ ሆነ።
ሳምንቱ በታሪክ
ማዘጋጃ ቤቱ ተመረቀ
ጥር 26 ቀን 1957 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ተመረቀ። በሕንፃው መግቢያ ላይ የተለጠፈው ሰሌዳ እንዲህ ይላል “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመናገሻው ከተማ ለአዲስ አበባ ሕዝባቸው፣ ለማኅበራዊ ኑሮው፣ ለኢኮኖሜውና ለባህሉ ዕድገት አማካይ የአገልግሎት ቤት ይሆን ዘንድ ፈቅደው ያሠሩትን ይህን ሕንፃ፣ በሠላሳ አራተኛው ዘመነ መንግሥታቸው መርቀው ከፈቱ።”
የጠፋው ቦምብ
ጥር 28 ቀን 1950 ዓ.ም የአሜሪካ ኅብረት አየር ኃይል በሳቫና (ጆዮርጂያ) ጠረፍ አካባቢ አንድ የሃይድሮጅን ቦምብ ጠፍቶበት እስካሁን አልተገኘም። የጠፋው ቦምብ 7600 ፓውንድ ይመዝናል፡፡ ቦምቡም የጠፋው በሁለት ጀቶች ግጭት ምክንያት ሲሆን ቦምቡ ዋሶው ሳውን በሚባል ጥልቅ የውኃ አካል ውስጥ ገብቶ እንደጠፋ ይገመታል፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


