እንደ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም መረጃ መሠረት በየቀኑ 66 ሚሊዮን የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ለረሀብ ይጋለጣሉ:: በሌላም በኩል ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 75 ሚሊዮን ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም:: ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ከሚመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የሚወጡት 59 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑም መረጃው ጠቁሟል::
ሀገራት በትምህርት ያላቸውን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ጥራት ባለው ትምህርት ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባን እንደ መውጫ እየተጠቀሙ ይገኛሉ:: እንደ ዓለማቀፉ የትምህርት ቤት ምገባ ጥምረት እ.አ.አ 2025 መረጃ ዓለም በአሁኑ ወቅት 466 ሚሊዮን ተማሪዎቿን በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ እያደረገች ነው:: እንደ ሕንድ፣ ብራዚል፣ ፊንላንድ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ ያሉ ሀገራት ደግሞ ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በአርአያነት የሚጠቀሱ ሀገራት ናቸው:: ምገባውን ከትምህርት ጥራት፣ ከጤና እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር መሥራታቸው ደግሞ ለውጤት እንዳበቃቸው ጥምረቱ ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል::
ሕንድ
ግሎባል ቻይልድ ኒውትሪሽን ፋውንዴሽን (GCNF) በምገባ ቀዳሚ እና ውጤታማ ሆነው ክፍለ ዘመናትን ከተሻገሩ ሀገራት መካከል ሕንድን ይጠቅሳል:: ምገባው የተጀመረዉ እ.አ.አ በ1920ዎቹ በታሚል ናዱ ግዛት (በቼናይ) በጥቂት ተማሪዎች ነው:: ከጊዜ በኋላም በሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው ምግብ ማቅረብ ጀመሩ:: በ98 ዓመት የምገባ ጉዟቸውም ከ120 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ አድርገዋል::
ሕንድ ምገባውን ተደራሽ እያደረገች ያለችው በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሆነም የግሎባል ቻይልድ ኒውትሪሽን ፋውንዴሽን መረጃ ያስረዳል:: በገጠራማ አካባቢዎች ምግቡ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ በሠራተኞች ወይም በአካባቢው እናቶች እንዲዘጋጅ የሚደረግበት መንገድ ቀዳሚ ነው:: ይህ ለእናቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠርም ባለፈ ተማሪዎች ትኩስ ምግብ እንዲገኙ የሚያስችል ነው::
ሁለተኛው የምግብ አቅርቦት አካሄድ በማዕከላዊ ወጥ ቤቶች አማካኝነት የሚቀርብ ነው:: በከተሞች ውስጥ ዘመናዊ እና ግዙፍ ወጥ ቤቶች የተገነቡ ሲሆን በልዩ ተሽከርካሪዎች ለትምህርት ቤቶች እንደሚዳረስ ፋውንዴሽኙ ጠቁሟል:: አክሻያ ፓትራ (Akshaya Patra) ደግሞ ይህንን ውጤታማ አድርጎ በማስቀጠል ተጠቃሽ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
ምገባው የሥርዓተ ምግብ ደረጃዎችን እንዲያልፍ ይደረጋል:: ይህም ምገባው ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ባለፈ ጤናቸው ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ከማሰብ ነው:: በዚህም ለእያንዳንዱ ተማሪ በቀን ቢያንስ 450 ካሎሪ እና 12 ግራም ፕሮቲን (ለአንደኛ ደረጃ) እንዲያገኝ ተደርጎ የታቀደ ነው። እንደ ብረት እና ፎሊክ አሲድ ያሉ ንጥረ ነገሮች በምግቡ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል።
ይሁን እንጂ ፕሮግራሙ ከአጀማመሩ ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩበት ፋውንዴሽኑ በግልጽ ዘርዝሯል:: ምግቡ የሚዘጋጅባቸው ቦታዎች ንጽሕና መጓደል አልፎ አልፎ ለምግብ መመረዝ አደጋዎች ምክንያት ሆኗል። በብዙ ገጠራማ አካባቢዎች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ ዘመናዊ የወጥ ቤት ቁሳቁሶች እና የምግብ ማከማቻ መጋዘኖች እጥረት ተጠቃሾች ናቸው:: ለምገባ የተመደበው እህል ለሌላ ዓላማ መዋል ወይም ጥራቱ የወረደ እህል መቅረብ ሌላኛው ተግዳሮት ነው:: በአንዳንድ አካባቢዎች ከዝቅተኛ ጎሳ የተውጣጡ ሰዎች ያበሰሉትን ምግብ አንበላም የሚሉ ማኅበራዊ ግጭቶች እንቅፋት ሆነውም ነበር።
የሕንድ ምገባ ፈተናዎች ሳያሸንፉት ዘመናትን እንዲሻገር የሆነው በጠንካራ የሕግ መዋቅር፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ ምክንያት ለመሆኑ የግሎባል ቻይልድ ኒውትሪሽን ፋውንዴሽን መረጃ ዋቢ ነው:: ተጠያቂነትን ወደ ታች (ወደ ወላጆች) መውረዱ እና ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ እንዲሆን መደረጉ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል::
በከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር እየተመራ ያለው የተማሪ ምገባ ለሀገሪቱ የትምህርት ተሳትፎ፣ ጥራት እና ተደራሽነት ያበረከተው አስተዋጽኦ በጥናት የተደገፈ ነው:: ተማሪዎች በተለይም ከዝቅተኛ ቤተሰብ የወጡ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የመምጣት ፍላጎታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የሴት ተማሪዎችን ምዝገባ እና በትምህርት የመቆየት ምጣኔን አሻሽሏል። የሕፃናትን የደም ማነስ (Anaemia) እና የክብደት መቀነስ ችግሮችን በመቀነስ ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ማገዙን በሀገሪቱ የተደረጉ ጥናቶች አስረጂወች ናቸው::
የተማሪዎችን የአእምሮ ንቃትና ትኩረት በመመለስ ውጤታማ ዜጋን ለመፍጠር አግዟል:: ረሃብ የተማሪዎችን ትኩረት የመሰብሰብ አቅም ይገድላል። ሕንድ ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተማሪዎች በቂ ምሳ በማግኘታቸው ከሰዓት በኋላ ባሉ ክፍለ-ጊዜዎች በንቃት መከታተል ችለዋል። ቀደም ሲል ተማሪዎች ከምሳ ሰዓት በኋላ በርክተው ትምህርት ያቋርጡ ነበር።
ምገባዉ የተማሪወችን የማስታወስ ችሎታቸውን እንዲሻሻል ማድረጉንም በጥናት ስለመረጋገጡ ተመላክቷል:: የተመጣጠነ ምግብ (ፕሮቲንና ቫይታሚን) ማግኘታቸው የተማሪዎችን የመረዳትና የመመራመር ብቃት ከ20 በመቶ በላይ እንዳሻሻለው ይገመታል።
ፕሮግራሙ ከክፍል ውስጥ ትምህርት ባለፈ ማኅበራዊ እኩልነትን አስተምሯል:: የተለያዩ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸውና የተለያዩ ጎሳ ያላቸው ተማሪዎች በአንድ ላይ ተቀምጠው እንዲመገቡ በማድረጉ ተማሪዎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እንዲረሱ እና በጋራ የመማር ስሜታቸው እንዲዳብር እንዳደረገ ጽሁፉ ጠቁሟል::
ብራዚል – ከገበሬው ለተማሪው
ብራዚል በተማሪ ምገባ ታሪክ 70 ዓመታትን አስቆጥራለች:: በአሁኑ ወቅትም 40 ሚሊዮን ተማሪዎች እየመገበች ትገኛለች::
ግሎባል ቻይልድ ኒውትሪሽን ፋውንዴሽን (GCNF) የብራዚልን የተማሪዎች ምገባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወርቃማው ሞዴል ሲል ይጠራዋል:: ምግብን ከማቅረብ ባለፈ የሀገር ውስጥ ግብርናን በማነቃቃት እና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን አንስቷል::
የብራዚልን የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባ ምን ነገሮች ይለዩታል ለሚለውም የድረ ገጹ ጽሁፍ ምላሽ ይሰጣል:: በብራዚል ምግብ ማግኘት እንደ ማንኛውም ዜጋ ሰብአዊ መብት በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገ ነው:: መርሃ-ግብሩ ሁሉንም የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች (ከመዋለ ሕፃናት እስከ ጎልማሶች ትምህርት) ያካተተ መሆኑንም ከጽሁፉ መረዳት ይቻላል::
በጀቱም በሕግ የተጠበቀ በመሆኑ በፖለቲካዊ ለውጦች ወይም በመንግሥት መቀያየር ምክንያት አይቋረጥም። በሕግ ደረጃ ለምገባ የሚመደበው በጀት ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነው ግብዓት መገዛት ያለበት ከአነስተኛ የአካባቢው ገበሬዎች መሆኑ ከሌሎች ሀገራት ለየት ያለ አሠራር ለመኖራቸው ማስመስከሪያ ነው:: ይህም ገበሬዎች ቋሚ ገበያ ያገኛሉ፤ ተማሪዎች ደግሞ ትኩስ እና ኦርጋኒክ የሆኑ ምግቦችን (አትክልት፣ ፍራፍሬና እህል) እንዲያገኙ ይረዳል:: በገጠር አካባቢዎች የገንዘብ ዝውውር እንዲጨምርና የከተማ ፍልሰት እንዲቀንስ ያገዘ ሞዴል ተደርጎ ይወሰዳል ሲል ጽሁፉ አክሏል::
በብራዚል የትምህርት ቤት ምገባ የምግቡን ጤናማነት የሚቆጣጠሩ የሥርዓተ-ምግብ ባለሙያዎች እንዲኖሩት ከማስገደደም ባለፈ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች፣ የታሸጉ ጭማቂዎች እና ከረሜላዎች በትምህርት ቤት ውስጥ በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው። እንደ መረጃው ከሆነ 70 በመቶ የሚሆነው ምግብ ትኩስ እና ያልተቀነባበረ መሆን ይኖርበታል የሚል ዉሳኔ አለ::
የምገባ ሥርዓቱን ከሙስና የጸዳ ለማድረግ፣ በጀቱን በትክክል ለምግብ ለማዋል እና የምግቡን ጥራት በየቀኑ ለመቆጣጠር ከወላጆች፣ ከመምህራን እና ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ የምገባ ምክር ቤቶች ተቋቁመዋል::
ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ የተማሪዎች ምገባ መነሻው ከመሰረታዊ የርሃብ ችግር ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ:: ምገባው በአሁኑ ወቅት ወደ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና ወደ ማኅበራዊ ደኅንነት ዋስትና ሥርዓትነት እያደገ መጥቷል:: ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የምገባ ሥርዓቱን በሥርዓተ ትምህርቷ በማካተት ለትውልድ ግንባታ በትኩረት እየሠራች ነው:: ምሁራንም ለፕሮግራሙ መስፋት እና መዝለቅ በዕውቀታቸው እየሠሩ ይገኛሉ::
ወይዘሮ ምስራቅ ፈይሳ እ.ኤ.አ በ2018 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በነበሩበት ወቅት በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚተገበረውን የተማሪ ምገባ ፕሮግራም ፋይዳ መነሻ በማድረግ ጥናት አካሂደው ነበር:: እንደ ጥናት ውጤቱ ከሆነ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት የሚቀሩባቸውን ቀናት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል:: ጥናቱ የምገባ መርሃ-ግብሩ ተማሪዎች በባዶ ሆድ እንዳይማሩ በማድረጉ በትምህርት ክፍለ ጊዜ ያላቸውን ትኩረት እና ንቃት ጨምሯል። ተማሪዎች ትምህርት ቤትን እንዲወዱ እና በቋሚነት እንዲገኙ ማድረጉን ጠቁመዋል:: የክፍል ውጤት መሻሻል ላይም ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን የጥናት ግኝቱ አረጋግጧል:: የተማሪዎች አማካይ ውጤትም ከ67 ነጥብ 61 በመቶ ወደ 69 ነጥብ ሁለት ከፍ ብሏል::
ጥናቱ የምገባ ፕሮግራሙን ይበልጥ ለማሻሻል ያግዛሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችንም ጠቁሟል:: መርሃ-ግብሩ ሁሉንም ችግረኛ ተማሪዎች እንዲያካትት ተደራሽነቱን ማስፋፋት፣ የሚቀርበው ምግብ የተመጣጠነ ይዘት ያለው መሆኑን በጤና ባለሙያዎች በየጊዜው መፈተሽ፣ የተማሪዎችን ውጤት እና ጤና የሚከታተል ወጥ የሆነ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በትምህርት ቤቶች ውስጥ መዘርጋትን በዋናነት ጠቁሟል::
በተሞክሮነት ካየናቸው ሀገራት በርካታ የማጠናከሪያ መፍትሄዎችን መቅሰም ይቻላል:: የመጀመሪያው መንግሥት ብቻውን ከመሸከም ይልቅ የግሉ ዘርፍ በማኅበራዊ ኃላፊነት ስም ድጋፍ እንዲያደርጉ ማድረግ ነው:: ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩበትን መንገድ (የጓሮ አትክልት ልማት) ማበረታታትም ይመከራል:: ትምህርት ቤቶች ደረጃውን የጠበቀ ወጥ ቤት እና የመመገቢያ አዳራሽ እንዲኖራቸው ቅድሚያ መስጠት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችን ማስፋፋት ጤናን ለማረጋገጥ እንደ መፍትሄነት ልንወስድ እና ምገባን በወጥነት በማስቀጠል የትምህርትን ዉጤታማነት ማሳደግ ይገባል::
መረጃ
የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ፋይዳዎች በዋናነት በሦስት ዘርፎች (በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ) ሊጠቃለሉ ይችላሉ፡፡
በትምህርት ዘርፍ
የትምህርት ተሳትፎን በእጅጉ ይጨምራል፡፡
የትምህርት ማቋረጥን ይቀንሰዋል፡፡ (
የማስታወስ እና የመረዳት አቅምን ያሳድጋል፡፡
በጤና እና በሥርዓተ-ምግብ
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመከላከል ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የዕድገት ደረጃ እንዲገኙ ያግዛል፡፡
መቀንጨርን በመቀነስ ሕፃናት በአካላዊ እና በአእምሯዊ ዕድገታቸው ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ይረዳል።
በሽታ የመቋቋም አቅማቸው የዳበረ እና ጤናማ ዜጎችን ለማፍራት መሠረት ይሆናል።
በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ለልጆች ምሳ የሚወጣውን ወጪና ጊዜ ለሌላ የቤት ውስጥ ፍላጎት እንዲያውሉት ይረዳል።
የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ማኅበራዊ እኩልነት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡
https://schoolmealscoalition.org/
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


