የቴክኖሎጂ ሁለት ገፅታ

0
148

ቴክኖሎጂ የቴክኒክ፣የክህሎትና አሠራር ዘዴዎች ስብስብ የሆኑ ምርቶችን፣ አገልግሎቶችን፣ የሳይንሳዊ ምርምሮችን ዓላማ ማስፈጸም የሚያስችል መሣሪያ ነው። የሰው ልጅ መጀመሪያ እንጨቶችን ተጠቅሞ በማፋጨት እሳት ማግኘት ቻለ። ምግብን ድንጋይ ላይ በማብሰል ቀጠለ። ለመጓጓዣ ጋሪን በመገልገልም ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል ጀመረ። ቀስ በቀስም የህትመት መሣሪያዎች፣ ስልክ … እያለ የኢንተርኔት መፈጠር ላይ ደረሰ፤ ይህም በቴክኖሎጂ የመጠቀም ፍላጎት እና እድገት እንዲጨምር አስቻለ።

የአማራ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ በድረ ገጹ “የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንነትና ግንኙነት” በሚል ርዕስ ባስነበበው ፅሑፍ እንደገለጸው ቴክኖሎጂ የሚለው ቃል መታወቅ ከጀመረ 200 ዓመታት ተቆጥረዋል። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ግን ቴክኖሎጂ የሚለው ቃል “ጠቃሚ ጥበባት” በሚለው ነበር የሚታወቀው።

ቴክኖሎጂ የሚለው ቃል በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ጋር የተፈጠረ ነው። በ1930ዎቹ ቴክኖሎጂ የኢንዱስትሪ ጥበባትን ማጥናት ብቻ ሳይሆን ራሳቸው የኢንዱስትሪ ጥበባት ቴክኖሎጂ መሆናቸው ተረጋገጠ።

ቴክኖሎጂ ሰፋ ባለ ሁኔታ ሲገለጽ አዕምሮአዊ እና አካላዊ ጥረት ተጣምረው ቁሳዊና ቁሳዊ ያልሆኑ ነገሮችን ጠቀሜታ ወዳላቸው ነገሮች መቀየር እና መጠቀም ነው። በዚህ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ የእውነተኛ ዓለም ችግሮችን ለመፍታት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሣሪያዎችና ማሽኖችን ያመለክተናል። ቴክኖሎጂ የሰዎችን ፍላጎትና ዓላማ ማሟላት የሚችል የቴክኒኮች ስብስብ(የቴክኒክ ዘዴዎች፣ ክህሎት፣ ሂደት፣ መሣሪያና ጥሬ ዕቃዎች)፣ የሰው ልጅ ዕውቀት ተሰባስበው እና ተዋህደው ተፈላጊ ውጤት የሚገኝበት፣ ችግሮች የሚፈቱበትና ፍላጎት ምላሽ የሚያገኝበት ነው።

ቴክኖሎጂ ባህልን የለወጠ ተግባር ነው ተብሎ ሊታይ ይችላል። ቴክኖሎጂ ሂሳብን፣ ሳይንስን እና ጥበብን መሠረት አድርጎ የህይወትን ጠቀሜታ ያረጋገጠ ነው። ለአብነት መገናኛ ቴክኖሎጂ የግንኙነት እንቅፋቶችን በማስወገድ ሰዎች እንዲቀራረቡ አድርጓል፤ በኢንተርኔት እና ኮምፒውተር ላይ ተመስርቶም አዲስ የሳይበር ባህል እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አብዛኛውን ጊዜ በመተካካት ጥቅም ላይ ይውላሉ፤ ነገር ግን የሳይንስ ግብ ዕውቀት ማሳደድ ሲሆን የቴክኖሎጂ ግብ ደግሞ ችግሮችን መፍታት፣ ምርት መፍጠር እና ለሰው ልጆች ህይወት መሻሻል አተኩሮ የሚሠራ ነው። በአጭር አነጋገር ቴክኖሎጂ የሳይንስ ማስፈፀሚያ መሣሪያ ነው።

አሁን ላይ ዓለማችን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በእጅጉ እየዘመነች ነው። ከበራሪ ጀት እና መንኮራኩሮች እስከ ረዥም ርቀት በሰዓት የሚጓዙ ባቡሮች፣ ረዥም ማይልስ አቋርጠው የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች  እውን እየሆኑባት፣ ዘመናዊ ገመድ አልባ ስልኮች፣ ሰማይ ጠቀስ ዘመናዊ የህንፃ ጥበብ እና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች እያበቡባት ነው።

ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ እውቀቱን ተጠቅሞ ችግሮችን የሚፈታበት እና ህይወቱን የሚያሻሽልበት ነው። ይሁን እንጂ የአጠቃቀም ችግሩ በርካታ መዘዞችን አስከትሏል። በሰው ልጅ ጤና ላይ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል ለምሳሌ ረዥም ሰዓት ስልክ ወይም ኮምፒውተር ላይ መቆየት የአይን ህመምን ያስከትላል። በእንቅልፍ እጦት ምክንያትም ለሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች ይዳርጋል።

ሥርዓት የሌለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምም ሱስን ያስከትላል። በዚህ የተነሳ የውጥረት/stress/ እንከን ይከሰታል። በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ይዘቶችን ተከትሎ ራስን ከሌሎች ጋር በማነፃፀር የራስን ውሳኔ ያዛባል። እነዚህም የአእምሮ እና ስነ ልቦና ጉዳቶች ናቸው።

የሰውን ልጅ የኑሮ ደረጃ በእጅጉ ሊያሻሽል የሚችልን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ካለመጠቀም በመነጨም የስነ ምግባር ጉዳቶች እየደረሱ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ የሚዘሩ የውሸት መረጃዎች /fake news/ መስፋፋት እና የጥላቻ ንግግሮች ለዚህ ተጠቃሽ አብነት ይሆናሉ። ይህን አስነዋሪ የሥነ ምግባር ጥሰት አለመፈጸም ደግሞ ብቸኛው መፍትሄ ነው።

ቴክኖሎጂን በአግባቡ አለመጠቀም በተለይ በህፃናት ጤና ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው። የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለልጆች የአዕምሮ እድገት ወሳኝ ጠቀሜታ ያላቸውን ያህል ጉዳታቸውም የከፋ መሆኑን የስነ ልቦና ምሁሩ ዶክተር ቪክቶሪያ ኤል ደንከሌይ ያስገነዝባሉ።

ልጆች ጌሞችን የሚጫወቱበትን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ምስል በስክሪን ላይ የሚመለከቱበትን ጊዜ መወሰን ካልተቻለ በልጆች አዕምሮ እድገት ላይ አሉታዊ ጫና ያስከትላል። በተለይም የማህበራዊ ትስስር ገፆች ጫና ልጆች ለረዥም ሰዓት ተቀምጠው እንዲያሳልፉ በማድረግ ውጥረት ያስከትላል። ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳያጠኑ እና በቂ የእንቅልፍ ጊዜ እንዳያገኙ ያደርጋል። ልጆች ለእነዚህ ችግሮች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ደግሞ ከቴክኖሎጂ ውጤት የሚያገኙትን ጠቀሜታ ታሳቢ ያደረገ የአጠቃቀም ስልትን ወላጆች ለልጆች ማስገንዘብ ቁልፍ መፍትሄ ይሆናል።

የቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ ዓለም አንድ መንደር እስከመምሰል ደርሳለች። ይህም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን አምጥቷል። ለአብነትም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዓለም አቀፍ የመረጃ፣ የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ፍሰትን አፋጥኗል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የባህል ማንነትን ማጣት/የባህል ጭፍለቃ/Loss of Cultural Identity/ እያስከተለ ነው። ይህ ችግር የምዕራባውያንን ወግ እና ባህል እንድንሸከም አስገድዷል። የአካባቢን ወጎች እና ባህላዊ ማንነቶች አደጋ ላይ ጥሏል። “የሰው ወርቅ አያደምቅ” ነውና ቴክኖሎጂ እያደረሰ ካው የባህል መበረዝ ወረርሽኝ ለመዳን የራስን ጠብቆ በማቆየት ከትውልድ ትውልድ ማሸጋገር ብቸኛ መዳኛ ነው።

ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር እየሆነ በመጣው የኤሌክትሮኒክስ ውጋጅ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው “ዌስት ኤሌክትሪካል ኤንድ ኢኩፕመንት (WEEE)” የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም እንደሚያስገነዝበው የቴክኖሎጂ ምጥቀቱን ተከትሎ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ውጋጅ ጉዳት እያስከተለ ነው።

የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰው በዘፈቀደ በየአካባቢው የሚጣሉ የኤሌክትሮኒክስ ውጋጆች በአፈር እና በከርሰ ምድር ውሃ ላይ ጎጂ ውጤቶችን እያስከተሉ ነው። ከዚህ ባለፈም በዓለማችን የአየር ብክለት ምጣኔ ላይም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ከዚህ አስከፊ ችግር ለመዳን ደግሞ ውጋጅ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን እንደገና ጥቅም ሊሰጡ ወደሚችሉበት ቀይሮ መገልገል ሁነኛ መፍትሄ ነው።

ቴክኖሎጂ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ያህል ጉዳቱም ዘርፈ ብዙ ነው። የጤና ጉዳቶች፣ ማህበራዊ ጉዳቶች፣ የአዕምሮ እና ስነ ልቦና ጉዳቶች፣ የሥራ እና ኢኮኖሚ ጉዳቶች፣ የደህንነትና የግላዊ ጉዳቶች፣ የስነ ምግባር ጉዳቶች … በማለት ቢዘረዘር ጉዳቱ የጠቀሜታውን አቻነት ይገዳደራል። በመሆኑም የቴክኖሎጂን ሁለት ገፅታ መገንዘብ ጉዳቱን ለመከላከል ይጠቅማል፤ ቸር ይግጠመን!

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here