መግቢያ
የምርጥ ዘር ጥራት እና ደህንነት ለተሻለ የግብርና ምርት እድገት መሰረት ነው። ጥራቱን የጠበቀ ዘር በሽታ የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ፣ በፍጥነት የሚበቅል፣ ቶሎ የሚደርስ እና ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ ነዉ። ዘሩ ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ ዝርያው እንዳይበላሽ ርቀታቸውን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም በማደግ ላይ እያለ የባዕድ ዝርያዎችን ማስወገድ ማለትም ከዋናው ዝርያ የተለዩ ወይም በበሽታ የተጠቁ ሰብሎችን ለይቶ በማውጣት ምርጥ ዘሩን መጠበቅ ይገባል።
ይህም ዘሩ በሚሰበሰብበት ወቅት ንጹህ እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ያስችላል። ምርቱ ከተሰበሰበ በኋላ የሚከናወኑት የድህረ-ምርት ጥንቃቄዎች ለዘሩ ደህንነት ወሳኝ ሚና አላቸው። ዘሩ በሚወቃበት እና በሚጸዳበት ወቅትም ከሌሎች ሰብሎች ጋር እንዳይቀላቀል የመሣሪያዎችን ንጽሕና መጠበቅ ግዴታ ሲሆን ዘሩ ከመከዘኑ በፊት ያለውን የእርጥበት መጠን በአግባቡ ማድረቅም ለረጅም ጊዜ ያለብልሽት እንዲቆይ ይረዳልና በሚገባ መድረቁ ተረጋግጦ መቀመጥ አለበት። በመጋዘን ውስጥም ቢሆንም በተባይ፣ በአይጥ እና በፈንገስ እንዳይበላሽ እና እንዳይባክን መጋዝኑ ዉስጥ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር ማስተካከል እንዲሁም የቤቱን እና የቦታዉን ንጽሕና ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እነዚህን እና ሌሎች መሰል ጥንቃቄዎችን ማድረግ የተመረተዉ ዘር ወደ ገበያ እና ወደ አርሶ አደሩ ሲደርስ ከፍተኛ የመብቀል አቅም እና ምርታማነት እንዲኖረው ያግዛል።
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የጥራት ቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር ቁልፍ ተግባር መሆኑን ያስታወቀው ደግሞ የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ነው። ባለስልጣኑ በተለይም በምርጥ ዘር፣ በአፈር ማዳበሪያ፣ በችግኝ ጥራት እና በግብርና ኬሚካሎች (ፀረ አረም እና ፀረ ተባይ) ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አመላክቷል። የጥራት ክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች መጠናከርም የዘርፉን ዘላቂ እድገት ከማረጋገጥ ባሻገር በሰው፣ በእንስሳት እና በእፅዋት ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመከላከል እንደሚያስችልም ባለስልጣኑ አስታውቋል።
የአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማን በባሕር ዳር ከተማ ጥር 18 እና 19 ቀን 2018 ዓ.ም አካሂዷል:: በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ አቶ ፈንታሁን ስጦታው እንዳብራሩት የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይ በምርጥ ዘር ብዜት ላይ ከማሳ ጀምሮ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው:: በምርጥ ዘር ብዜት እና አቅርቦት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን ዘሩ በዳታቤዝ የተመዘገበ፣ በGPS የተለካ እና ተገቢውን የርቀት ክልል የጠበቀ መሆኑን በተገቢው መንገድ ክትትል ይደረጋል ብለዋል። የምርጥ ዘር ጥራት እና የላቦራቶሪ ፍተሻ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው ዘር እንዲቀርብ እየሠራ ነው። ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ከምርት ሂደት ጀምሮ በማጓጓዝ እና በክምችት ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የጥራት ጉድለት ለመፍታት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት። በዘርፉ የተጀመሩ ተግባራት አበረታች እንደሆኑ ኃላፊዉ አንስተው የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ከግብርና ኬሚካሎች ጋር በተያያዘም አጠቃቀማቸውን የሚመራ መመሪያ እየተዘጋጀ ሲሆን በባሕር ዳር እና በሌሎች ከተሞች ያሉ የኬሚካል መሸጫዎች የሰዎችን ጤና በማይጎዳ መልኩ በአንድ አካባቢ እንዲሆኑ ከከተማ አሥተዳደሮች ጋር ንግግር እየተደረገ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። ባለስልጣኑ አዲስ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ጥራት የመቆጣጠር ሥራ ለመጀመር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም 390 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርጥ ዘር የላቦራቶሪ ፍተሻ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን 109 ሺህ ኩንታል የከረመ ዘር ጥራቱ ተረጋግጦ ለስርጭት መዘጋጀቱ ተገልጿል። ባለስልጣኑ ወደ ክልሉ የሚገባውን ማዳበሪያ በፊዚካል ኢንስፔክሽን እና በላቦራቶሪ እየፈተሸ ይገኛል። እስካሁንም 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ የፊዚካል ኢንስፔክሽን መሠራቱን ተናግረዋል። ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ነው የጠቆሙት። የማዳበሪያ ሥርጭት በሥርዓት እንዲመራ መመሪያ ወጥቶ ወደ ሥራ ገብቷል፤ ለዚህም ከአጋር አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት::
የደረሱ ጉዳቶች እና የተወሰዱ ርምጃዎች
በዚህ ዓመት 10 ሺህ 783 ሄክታር መሬት በዘር ብዜት የተሸፈነ ሲሆን ጥራታቸውን (ደረጃቸውን) ያላሟሉ በ609 ሄክታር መሬት ላይ የተሸፈነ ዘር ከጥቅም ውጭ (ውድቅ) መደረጉን ሃላፊዉ አስታዉቀዋል። ይህም ጠንካራ ቁጥጥር እና ክትትል የተደረገ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ኃላፊው ጨምረዉ አብራርተዋል። የግለላ /ርቀት ባለመጠበቅ/፣ የዘር መቀላቀል፣ የበሽታ ክስተት፣ የአረም ቁጥጥር አናሳ መሆን፣ የቦታ አመራረጥ ችግር እና መሰል ጉዳዮች ለጥራት መጓደል ምክንያቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል። በሕገ ወጥ መንገድ ተዘዋውሮ የተሰራጨ ምርጥ ዘር በሁለት ሺህ አርሶ አደሮች ላይ ኪሳራ ማድረሱን የገለፁት ኃላፊው በእነዚህ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት እንዲቀጡ መደረጉንም ጠቁመዋል። በአሰራር ላይ ክፍተት በፈጠሩ በሶስት የዘር አምራች ድርጅቶች ላይ አስፈላጊውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ለአንድ ዓመት እንዲታገዱ የተደረገ ሲሆን ሁለት የዘር አምራች ድርጅቶች ላይም እርምጃ ለመውሰድ በሂደት ላይ ነው ብለዋል። በ33 የፀረ ተባይ ኬሚካል እና 69 የአፈር ማዳበሪያ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ሕጋዊ ቅጣት ተወስዷል- ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲመጡም ተደርጓል። በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ አንድ ሺህ 215 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ሁለት ሺህ 283 ሊትር የፀረ ተባይ ኬሚካል ውርስ መደረጉንም ገልጸዋል። ነጋዴዎች ሥርዓቱን እና ሕጉን ተከትለው በጥንቃቄ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው።
ያጋጠሙ ችግሮች
የበጀት እጥረት፣ የተሽከርካሪ እና የቢሮ እጥረት (ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች)፣ የአፈር ማዳበሪያ እና የፀረ ተባይ ኬሚካል ጥራት ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ በላብራቶሪ የተደገፈ አለመሆን፣ አገልግሎት የማይሰጡ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች በወቅቱ አለመወገዳቸው፣ የ“ኳራንታይን” ጣቢያ አናሳ መሆን እና መሰል ችግሮች ናቸው።
የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች
የሰው ኃይል ማሟላት፣ የአቅም ግንባታን ማሳደግ፣ በክልል ደረጃ ደረጃውን የጠበቀ የላቦራቶሪ ግንባታ እና ቁሳቁስ ማሟላት፣ የባለድርሻ እና አጋር አካላትን ቅንጅት ማጠናከር እና የዲጂታላይዜሽንን ሥራ ማጠናከር ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው።
በባለሥልጣኑ የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አውግቸው ተሾመ ምርጥ ዘር ከዝግጅቱ ጀምሮ ጥራቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል:: ዘር የሚባዛበት ማሳ ተስማሚ መሆኑን የመለየት ሥራ ቀድሞ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል። ጥራቱ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘር መሆኑን ይከታተላል፣ ትክክለኛው ዘር መዘራቱን ያረጋግጣል፣ ማሳው ላይ ባዕድ ነገሮች እንዳይቀላቀሉ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ችግር ያለበት ምርጥ ዘር ከዘር አገልግሎት ውጭ ሆኖ ለምግብነት እንዲውል ይደረጋል። ከዩኒየኖች እና ከአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ጋር በጋራ በመሆን ተግባራቱ እየተከናወነ ነው። የተሰበሰበውን ምርጥ ዘር የማዘጋጀት፣ የማበጠር፣ የላቦራቶሪ ፍተሻ ማድረግ፣ የማሸግ እና የመሳሰሉ ሥራዎች ተከናውነው ለአርሶ አደሩ ለዘር አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል። በዚህ ስድስት ወር ውስጥ አልፎ አልፎ የዝርያ መቀላቀል የነበረባቸው ላይ ምርመራ ተደርጎ ውድቅ ተደርገዋል።
ሌላው የደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ብርሃኔ ገብሬ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች የጥራት ጉድለት እንዳይኖር በትኩረት ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሕገ ወጥነትንም ለመቆጣጠር ግብረ ሐይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው። ከፍትህ ተቋማት፣ ከንግድ መምሪያ እና ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው። በዚህም የ31 ሕገ ወጥ የፀረ ተባይ ኬሚካል አዘዋዋሪዎች እንዲወረሱ ተደርጓል። 126 ሊትር ኬሚካል እና 137 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንዲወረስ ተደርጓል። ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የቅድመ ግንዛቤ ፈጠራም እየተሠራ ነው። ለሰብል ጥበቃ ባለሙያዎች በፀረ ተባይ አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው። 83 ለሚጠጉ የፀረ ተባይ እና ፀረ አረም ነጋዴዎች ስለ አጠቃቀሙ ግንዛቤ እየተሰጠ ነው። በወቅቱ የጥራት ቁጥጥር የማድረግ፣ የመለየት፣ በተገቢው ቦታ የማስቀመጥ እና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ ነው። የምርጥ ዘር ጥራትና ደህንነትን ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ተግባራት በመሆናቸው በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሐብታሙ (ዶ/ር) ባለስልጣኑ ለሀገር ወስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ትልቅ የግብርና አቅም ያለው መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ምርቶቹንም ዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሸጠ መሆኑን መስክረዋል። በመሆኑም ለምርት ለጥራት እና ደህንነት ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል። በ2017 እና 2018 በጀት ዓመት በአማራ ክልል ብቻ ቦለቄ፣ ሰሊጥ እና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ አንድ ሺህ 280 ድርጅቶች (ኩባንያዎች )የምርት ጥራት ማረጋገጫ መሰጠቱን አመልክተዋል። የሚወጡ አዋጆች፣ ሕጎች፣ መመሪያዎች እና ደንቦች ተፈፃሚ ማድረግ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል። የሰብል በሽታ እንዳይከሰትም ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ያስፈልጋል። ከምርምር እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል። በዘር፣ በኬሚካል፣ በአፈር ማዳበሪያ እና በሌሎች የግብርና ግብዓቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ወደ ውጭ በሚላኩ እና ሀገር ውስጥ በምንመገባቸው ምርቶች ላይ ጤንነታቸው እንዲረጋገጥ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዳሬክተሩ አዉስተዋል።
መረጃ
ዘርን ለመግዛት እና ለመጠቀም አርሶ አደሩ ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
1.ሕጋዊ አቅራቢዎችን መጠቀም፦ ዘርን በጎዳና ላይ ከሚሸጡ ነጋዴዎች ሳይሆን ፈቃድ ካላቸው የሕብረት ስራ ማሕበራት ወይም ድርጅቶች መግዛት።
- መለያውን መመልከት፦ ትክክለኛ ቀለም ያላቸውን የጥራት ማረጋገጫ ታግ (Tag) ዘሮችን ይምረጡ።
- አያያዝ፦ ዘሩን ቀጥታ ከፀሐይ ብርሃን እና ከእርጥበት በራቀ ቀዝቃዛ ቦታ ያስቀምጡ።
በተጨማሪም አርሶ አደሩ አይነቱን፣ የተመረተበትን ቀን፣ የአገልግሎት ማብቂያው እና የጥራት ማረጋገጫ ምልክት መኖሩን በማረጋገጥ መግዛት እና መጠቀም ይጠበቅበታል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


