በየዓመቱ የሚያድገው ተራራ

0
145

የኤቨረስት ተራራ በምድር ላይ ካሉ ተራራዎች ሁሉ ረጅሙ ሲሆን፣ በሂማላያ የተራራ ሰንሰለት በማሃላንጉር ክፍል ውስጥ ይገኛል። የተራራው ጫፍ ከባህር ጠለል በላይ 8,848 ሜትር (29,029 ጫማ) ከፍታ ያለው ሲሆን፣ ከምድር እምብርት ደግሞ 5ኛው ርቆ የሚገኝ ቦታ ነው ። በቻይና እና በኔፓል መካከል ያለው ዓለም አቀፍ ድንበር የሚያልፈውም ልክ በዚህ የተራራው ጫፍ ላይ ነው። የተራራው ግዙፍ አካል እንደ ሎትሴ (8,516 ሜትር)፣ ኑፕትሴ (7,855 ሜትር) እና ቻንግትሴ (7,580 ሜትር) ያሉ አጎራባች ጫፎችን ያካትታል ።

የኤቨረስት ተራራ በርካታ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ተራራ ወጪዎች እንዲሁም ባለሙያ የጉዞ መሪዎችን ለመቅጠር ፈቃደኛ የሆኑ ብቁ ሰዎችን ይስባል። ወደ ተራራው ጫፍ ለመውጣት ሁለት ዋና መንገዶች አሉ፤ አንደኛው በኔፓል በኩል በደቡብ ምስራቅ (መደበኛው መንገድ) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በቲቤት በኩል በሰሜን አቅጣጫ ነው ። የኤቨረስት ጫፍ የምድር ገጽ ከባህር ጠለል በላይ ከፍተኛው ርቀት ላይ የሚደርስበት ቦታ ነው ።

ሂማላያ እና ታሪክ

ሂማላያ በሰሜን በኩል ያለውን የቲቤት አምባ እና በደቡብ በኩል ያለውን የህንድ ሜዳዎችን የሚለይ ታላቅ የእስያ የተራራ ስርዓት ነው ። ይህ ስርዓት ከ24,000 ጫማ (7,300 ሜትር) በላይ ከፍታ ያላቸው ከ110 በላይ ተራሮችን ይዟል። የኤቨረስት ተራራ በቲቤትኛ ቾሞሉንግማ፤ በቻይንኛ “ቆሞላንግማ ፌንግ”፣ በኔፓልኛ “ሳጋርማታ” ከእነዚህ ውስጥ ረጅሙ ነው።

ወደ ኤቨረስት ጫፍ በመውጣት የመጀመሪያው የተመዘገበ ታሪክ የኤድመንድ ሂላሪ (ከኒውዚላንድ የመጣ ተራራ ወጪ) እና የቲቤታውያን መሪው ቴንዚንግ ኖርጋይ ነው ። በ1945 ዓ.ም ተራራውን በመውጣት ክብረ ወሰኑን በጋራ ይዘዋል ። የተራራው ከፍታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበው ግን በ1848 ዓ.ም በብሪታንያ ቀያሾች አማካኝነት ነበር።

የሸርፓ (Sherpa) ህዝቦች

የሂማላያ ተራራዎች ለረጅም ጊዜ በሸለቆዎች ውስጥ ለሚኖሩ ተወላጆች መኖሪያ ናቸው። ከእነዚህም መካከል በጣም የታወቁት የሸርፓ ህዝቦች ናቸው ። “ሸርፓ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የተራራ መሪን ለማመልከት ጥቅም ላይ ቢውልም፣ ትክክለኛ ትርጉሙ ግን አንድን ብሄረሰብ ያመለክታል ። ሸርፓዎች በተራራ መውጣት ላይ ያላቸው ጠቃሚ ልምድ ለሌሎች ተራራ ወጪዎች ትልቅ እገዛ ያደርጋል ። አብዛኛው የኤቨረስት ጉዞ ያለ ሸርፓዎች የሎጂስቲክስ ድጋፍ እና እውቀት የማይታሰብ ነው ። ከዚህ በተጨማሪ ሸርፓዎች ዓመቱን ሙሉ በከፍተኛ ከፍታ ላይ ስለሚኖሩ፣ አነስተኛ የኦክስጅን መጠን ካለው አየር ጋር የተላመዱ ናቸው ።

አደጋዎች እና ተግዳሮቶች

የኤቨረስት ተራራን መውጣት ተወዳጅ ቢሆንም፣ በጣም አደገኛ ተግባር ነው ። ተራራውን ለመውጣት ከፍተኛ ልምድ፣ የጤና ምስክር ወረቀት፣ ትክክለኛ መሣሪያዎች እና የሰለጠነ የኔፓል መሪ ያስፈልጋል ። ተራራው ላይ ያለው በረዶ እንደ ናዳ (avalanches) ያሉ ገዳይ አደጋዎችን ይፈጥራል፤ እንዲሁም በመጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት ተራራውን መውጣት የሚቻለው በተወሰኑ ወቅቶች ብቻ ነው ።

ከሁሉም በላይ ግን ከፍታው ትልቁ አደጋ ነው ። ከ8,000 ሜትር (26,000 ጫማ) በላይ ያለው አካባቢ “የሞት ቀጠና” (death zone) ተብሎ ይጠራል ። በዚህ ቀጠና ውስጥ ረጅም ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች በከፍታ ህመም እና በአንጎል እብጠት ሊጠቁ ይችላሉ ።

ወቅታዊ ውዝግቦች

በአሁኑ ጊዜ የኤቨረስት ተራራ መውጣት ኢንዱስትሪ አወዛጋቢ እየሆነ መጥቷል። ተራራ ወጪዎች ወደ ጫፉ ለመድረስ በሞት ቀጠና ውስጥ ረጅም ጊዜ በመጠባበቅ ለከፍተኛ አደጋ ይጋለጣሉ። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ተራራ ወጪዎች የማይፈልጓቸውን ቁሳቁሶች በተራራው ላይ ጥለው ስለሚሄዱ ከፍተኛ ብክለት እየተፈጠረ ነው። የሸርፓ መሪዎች ዝቅተኛ ክፍያ እየተከፈላቸው ለማንኛውም የሥራ መስክ ሊያጋጥም የሚችል ከፍተኛ የሞት አደጋ ይጋረጥባቸዋል። ብዙ ተራራ ወጪዎች በመንገድ ላይ የሞቱ ሲሆን፣ አስከሬናቸውን መልሶ ማምጣት የማይቻል በመሆኑ ሌሎች ተራራ ወጪዎች በእነዚህ አስከሬኖች አጠገብ አልፈው መውጣት አለባቸው ።

ምንም እንኳን ኤቨረስት ከባህር ጠለል በላይ 8,849 ሜትር (29,032 ጫማ) በመሆን ከፍተኛው ነጥብ ቢሆንም፣ እንደ መለኪያው ሁኔታ ሌሎች ተቀናቃኞች አሉት፤ ለአብነት ከተራራው ግርጌ እስከ ጫፍ ከተለካ በሃዋይ የሚገኘው ማውና ኬያ ረጅሙ በሆነ ነበር። አብዛኛው አካሉ በፓስፊክ ውቅያኖስ ስር ስለሚገኝ፣ አጠቃላይ ቁመቱ ከ10,200 ሜትር በላይ ነው።

ተራራው አሁንም ቁመቱ እያደገ ነው። ኤቨረስት በየዓመቱ በጥቂቱ እያደገ ነው። ምክንያቱ ደግሞ በሕንድ እና በዩሬዢያ ቴክቶኒክ ሳህኖች (plates) መካከል በሚፈጠር ግጭት ምክንያት ተራራው ወደ ላይ ስለሚገፋ ነው። በመሆኑም ሳይንቲስቶች ተራራው በየዓመቱ በግምት 4 ሚሊ ሜትር ያድጋል ብለው ይገምታሉ።

ኔፓላዊው የከፍተኛ ቦታ መሪ ካሚ ሪታ ሼርፓ እስከ ግንቦት 2025 ድረስ ተራራውን 31 ጊዜ በመውጣት የዓለምን ክብረ ወሰን ይዟል። ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1994 የደረሰ ሲሆን፣ አሁን ላይ ሌሎች ተጓዦችን በጥሩ ሁኔታ የመምራት ስራን ይሰራል።

ተራራው ዕድሜን አይለይም፤ ሁለት አስገራሚ ሰዎች ይህን አረጋግጠዋል፤ ትንሹ ወጣት አሜሪካዊው ጆርዳን ሮሜሮ በ2002 ዓ.ም በ13 ዓመቱ ኤቨረስትን ወጥቷል። ሌላው ደግሞ አዛውንቱ ጃፓናዊ ዩቺሮ ሚዩራ በ2005 ዓ.ም በ80 ዓመቱ ተራራውን በመውጣት ትልቁ ሰው ሆኗል። አዛውንቱ ከጉዞው በፊት ሁለት የልብ ቀዶ ጥገናዎችን አድርጎም ነበር።

ያልተፈታው የ1916 ዓ.ምቱ ምስጢር ስለ ተራራው ከሚያስደንቁ እውነታዎች አንዱ ነው። ኤድመንድ ሂላሪ እና ቴንዚንግ ኖርጋይ በ1945 ዓ.ም ተራራውን በይፋ መውጣታቸው ይታወቃል። ነገር ግን ከ30 ዓመታት በፊት በ1916 ዓ.ም ጆርጅ ማሎሪ እና አንድሪው ኢርቪን ሙከራ አድርገው ነበር። ከጫፉ ጥቂት መቶ ሜትሮች ሲቀራቸው በደመና ተሸፍነው ጠፉ። የማሎሪ አስከሬን በ1991 ዓ.ም ተገኝቷል፣ ነገር ግን አብሯቸው የነበረው ካሜራ ባለመገኘቱ ጫፉ ላይ ደርሰው መሆን አለመሆኑ እስካሁን በምስጢር እንደተያዘ ነው።

“አረንጓዴ ጫማ” እና የሞት ቀጠና

በከፍተኛው የኤቨረስት ክፍል (ከ8,000 ሜትር በላይ) ያለው “የሞት ቀጠና” በጣም አደገኛ በመሆኑ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ማንሳት ፈጽሞ የማይቻል ነው።

በ1996 በደረሰ አውሎ ንፋስ የሞተው የሕንዳዊው ተራራ ወጪ (ቴዋንግ ፓልጆር) አስከሬን ለብዙ ዓመታት እንደ ምልክት ሆኖ አገልግሏል። በደማቅ አረንጓዴ ጫማው ምክንያት “አረንጓዴ ጫማ” በሚል ስያሜ ይታወቃል ።

የጉዞው መነሻ እና መስመር

አብዛኛው ተጓዥ ጉዞውን የሚጀምረው በሉክላ ከሚገኘው አደገኛ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ነው። መንገዱ በሳጋርማታ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚያልፍ ሲሆን፣ በኩምቡ ሸለቆ በኩል ይጓዛሉ። በጉዞው ወቅት እንደ ናምቼ ባዛር ባሉ መንደሮች በማረፍ ሰውነትዎ ከከፍታው ጋር እንዲላመድ ይደረጋል።

ተራራው በኔፓል “ሳጋርማታ” (የሰማይ አምላክ) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ለአካባቢው ነዋሪዎች ቅዱስ ቦታ ነው። በጉዞው ወቅት የቲቤት የጸሎት ባንዲራዎችን እና ለአካባቢው መንፈስ የሚቀርቡ ስጦታዎችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያያሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ተራራውን እንደ ጠባቂ እና ታላቅ መገኘት አድርገው ያከብሩታል።

የአካባቢው ሼርፓዎች ለጉዞው ስኬት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። እንደ ካሚ ሪታ ሼርፓ ያሉ መሪዎች ተራራውን በተደጋጋሚ በመውጣት (እስከ 31 ጊዜ) መንገዱን ለሌሎች ያመቻቻሉ። እነዚህ መሪዎች በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ያለውን አደገኛ ሁኔታ በመቋቋም ተጓዦችን በሰላም የመምራት ልምድ አላቸው።

አደገኛውን የኤቨረስት ተራራ ለመውጣት የተዘጋጁ ሰዎች በጉዟቸው በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥማቸው ልብ ይሏል። የከፍታ ሕመም አንዱ ነው፤ ቤዝ ካምፕ ለመድረስ ሰውነት ከኦክስጅን እጥረት ጋር መላመድ አለበት። እንዲሁም በድንገት የሚከሰቱ አውሎ ነፋሶች እና ቅዝቃዜ ጉዞውን አስቸጋሪ ሊያደርጉት ይችላሉ። አካላዊ ጥንካሬ የግድ ሲሆን፣ ምንም እንኳን ጉዞው የዕድሜ ገደብ ባይኖረውም ከፍተኛ የጽናት ደረጃን ይጠይቃል፡፡

 

አጭር እውነታ

 

ስለ ሂማሊያ አንዳንድ አጫጭር እውነታዎች

ሂማሊያ ተራራ ስርዓት በእስያ አህጉር ይገኛል።

የዓለም ከፍተኛው ተራራ ኤቨረስት (8,848.86 ሜትር) በሂማሊያ ውስጥ ይገኛል።

ሂማሊያ ከ5 አገሮች በላይ ይዘርጋል፤ ኔፓል፣ ህንድ፣ ቡታን፣ ቻይና እና ፓኪስታን።

ተራራው ከ 50 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በቴክቶኒክ ንቅናቄ ተፈጥሯል።

ሂማሊያ አሁንም በዓመት ጥቂት ሚሊሜትሮች ይጨምራል (እየከፋ ነው)።

ብዙ ትልቅ ወንዞች (ጋንጅ፣ ኢንዱስ፣ ብራማፑትራ) ከሂማሊያ ይጀምራሉ።

ለእስያ የዝናብ ዘመን (ሞንሱን) አስፈላጊ ሚና ይጫወታል።

በሂማሊያ የሚገኙ እንስሳት መካከል የበረዶ ነብር እና ያክ ይገኛሉ።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here